- በትግራይ ክልል የሚገኙ ወጣቶች የኋላቀር ቡድኑን የጦርነት ጉሰማ “በቃን” በሚል ድምፅ እየተቃወሙት መሆኑን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ ገለጹ።
አቶ ጌታቸው አዲስ አበባ የሚኖሩ የትግራይ ወጣቶች ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ ተገኝተው እንደተናገሩት፤ ትግራይ ውስጥ ያለው ወጣት አሁንም ጦርነት በቃን የሚል ድምፁን እያሰማ በመሆኑ፣ ጦርነት የሚሰብከውን ኋላቀር ቡድን “ሰላም” በሚል ቃል ልናሸንፈው ይገባል።
ባለፉት 30 ዓመታት ጦርነትን በመሸሽ የተጀመረው ስደት ወጣቶች ሀገራቸውን ጥለው እንዲሄዱ ማድረጉን ያስታወሱት አማካሪው፤ አሁን ባለው ሁኔታም በትግራይ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ተሰድደው ለማለቅ ሦስት ዓመት የሚፈጅባቸው እንደማይመስል በመግለጽ የሁኔታውን አሳሳቢነት አብራርተዋል።
ውይይት መፍትሔ ማስገኛ ዘዴ ቢሆንም ወደ ተግባር ካልተቀየረ ልምድ ሆኖ እንደሚቀር የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፤ የተደራጁ ሐሳቦችን ተግባራዊ በማድረግ በጦርነት ቀስቃሾች ላይ ተጽዕኖ መፍጠር እንደሚገባ አሳስበዋል።
አቶ ጌታቸው በውይይቱ ላይ የተሳተፉት ማንኛውንም ፓርቲ ወይም አደረጃጀትን ወክለው ሳይሆን፤ ትግራይን በማዳኑ ሂደት የሁሉም ድርሻ አስፈላጊ መሆኑን ስለሚያምኑ እንደሆነ ገልጸዋል።
ጦርነትን አንፈልግም የሚለው የወጣቶች ድምፅ መቐለ መሽጎ ጦርነት የሚሰብከውን ቡድን ሊያስደነግጠው እንደሚችል የገለጹት አማካሪው፤ ወጣቱ ድምፁን ይበልጥ ማሰማትና ለሰላም መደራጀት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
ጋዜጣ ፕላስ
