የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ዋና ፀሐፊ ዋምኬሌ ሜኔ እንደገለጹት፤ እ.ኤ.አ በ2025 ከተመዘገበው 220 ቢሊዮን ዶላር በመነሳት፣ በያዝነው የ2026 ፈረንጆች ዓመት በአፍሪካ ሀገራት መካከል የሚደረገውን የርስ በርስ ንግድ ልውውጥ 250 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ታቅዶ እየተሰራ ይገኛል።
በአሁኑ ወቅት 50 የአፍሪካ ሀገራት ስምምነቱን ተግባራዊ ማድረግ መጀመራቸውንና ለንግድ ትስስሩ መደላደል የሚሆኑ መሠረታዊ ፕሮቶኮሎች በሙሉ በስኬት መጠናቀቃቸውን ዋና ፀሐፊው ይፋ አድርገዋል።
ወቅታዊው የዓለም የኢኮኖሚ ቀውስ አፍሪካ ወደ ውጭ የምትልካቸውን ምርቶች ገበያ እየገደበው መሆኑን የጠቀሱት ዋና ፀሐፊው፤ እንደ ኮቪድ-19፣ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት እና የመካከለኛው ምስራቅ ውጥረት ያሉ ውጫዊ ተፅዕኖዎች አህጉሪቱ በዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለት ላይ ያላትን ጥገኝነት ስላሳዩ፣ ጠንካራ የአህጉር ውስጥ ገበያ መገንባት ለወደፊቱ መቋቋም አቅም ወሳኝ መሆኑን አሳስበዋል።
በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የንግድ ፋይናንስ ወጪ፣ ደካማ የትራንስፖርት መሠረተ ልማት እና የሰዎች ዝውውር መገደብ ለአህጉራዊ ንግድ ዕድገት ዋነኛ ማነቆዎች መሆናቸውን ሜኔ ጠቁመዋል።
ለምሳሌ ያህል ዕቃዎችን ከሌጎስ ወደ ሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ለማጓጓዝ በኬላዎችና በድንበር ፈተናዎች ምክንያት እስከ 17 ቀናት ሊወስድ እንደሚችል አስረድተዋል።
በመሆኑም የንግድ እንቅስቃሴን ለማቀላጠፍ እንደ ናይጄሪያ፣ ጋና፣ ሩዋንዳ እና ኬንያ ያሉ ሀገራት የቪዛ ገደቦችን ለማቅለል የወሰዱትን እርምጃ በማንሳት፣ ሌሎች ሀገራትም ከቪዛ ነፃ ወይም ድንበር ላይ የሚሰጥ የቪዛ አሰራርን እንዲያሰፉ ጥሪ አቅርበዋል።
