አሜሪካ እና እስራኤል የሚፈጽሙትን ጥቃት አጠናክረው በቀጠሉበት በአሁኑ ጊዜ የኢራን ባለሥልጣናት የጠቅላይ መሪያቸውን አያቶላህ አሊ ኻሜኒን የቀብር ሥነ ሥርዓት ወደ ሌላ ጊዜ አስተላለፉ።
የኢራን እስላማዊ የፕሮፓጋንዳ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ኃላፊ የሆኑት ሰይድ ሞህሴን ታስኒም ለተባለው ዜና ወኪል እንደተናገሩት የቀብር ሥነ ሥርዓቱ “አመቺ ጊዜ አስኪፈጠር ድረስ” እንዲዘገይ መደረጉን ገልጸዋል።
ረቡዕ ዕለት ተጀምሮ ለሦስት ቀናት ይቆያል ተብሎ የነበረው የአያቶላህ ኻሜኒ ቀብር እንዲዘገይ የተደረገው በርካታ ሕዝብ መሪውን ለመሰናበት ባለው ፍላጎት ለታዳሚው የሚበቃ የጸሎት ስፍራ ለማዘጋጀት እንደሆነ አንድ ባለሥልጣን ተናግረዋል።
የኻሜኒን ቀብር ተከትሎ ተተኪያቸው ይፋ እንደሚሆን እየተጠበቀ ሲሆን፣ በመሪው ምርጫ ላይ ውሳኔ የሚሰጠው ከፍተኛው የሃይማኖት እና ፖለቲካዊ ምክር ቤት የሚሰበሰቡባቸው ስፍራዎች ጥቃት እንደተፈጸመባቸው ተዘግቧል።
ነገር ግን አንድ የምክር ቤቱ አባል ጉባዔው የአያቶላህ ኻሜኒን ተተኪ ለመወሰን “ተቃርቧል” በማለት ተናግረዋል።
ባለፈው ቅዳሜ ቴህራን ውስጥ በአሜሪካ እና በእስራኤል በተፈጸሙ ከባድ ጥቃቶች የኢራን ጠቅላይ መሪን ጨምሮ በርካታ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተገድለዋል።
ለስድስተኛ ቀን ዛሬ በቀጠለው ጦርነት ኢራን እስራኤልን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ሚሳዔሎችን እያስወነጨፈች ሲሆን፣ አሜሪካ እና እስራኤልም በኢራን ላይ የሚፈጽሙትን ጥቃት ቀጥለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢራን የብሔራዊ ደኅንነት ጠቅላይ ምክር ቤት ዋና ፀሐፊ የሆኑት አሊ ላሪጃኒ፣ ፕሬዝዳንት ትራምፕ “የአሜሪካንን ሕዝብ ፍትሐዊ ወዳልሆነ ጦርነት ጎትተው አስገብተዋል ሲሉ” ወቅሰዋል።
