የአፍሪካ ኢንሹራንስ ድርጅት አቶ ያሬድ ሞላን በፕሬዚዳንትነት ሾመ

Date:

 

አፍሪካ ኢንሹራንስ ድርጅት የኒያላ ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ያሬድ ሞላን የድርጅቱ ፕሬዚዳንት አድርጎ ሾመ፡፡

መቀመጫውን በካሜሩን ዋና ከተማ ያውንዴ ያደረገው የመላው አፍሪካ ኢንሹራንስ ድርጅት፣ ሰሞኑን በአዲስ አበባ 51ኛውን ኮንፈረንስና ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ከተጠናቀቀ በኋላ ባካሄደው ምርጫ አቶ ያሬድ የድርጅቱ ፕሬዚዳንት ሆነው እንዲያገለግሉ መርጧቸዋል፡፡ 

የአፍሪካ አገሮች የዕዳ ጫና በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ላይ በሚያደርሰው ጉዳትና የመፍትሔ ሐሳቦች ላይ ሲያካሂድ መቆየቱ የሚታወስ ነው፡፡ የመዝጊያውን ሥነ ሥርዓት ባለፈው ሐሙስ ምሽት በሸራተን አዲስ ባከናወነበት ወቅት አቶ ያሬድም አዲሱ ሥራቸውን በይፋ ተረክበዋል፡፡ 

አቶ ያሬድ በአሁኑ ጊዜ ከኒያላ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር ከዋና ሥራ አስፈጻሚነታቸው ባሻገር፣ የኢትዮጵያ መድን ሰጪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ሆነው በማገልገል ላይም ናቸው፡፡ ባለፈው ዓመት በናሚቢያ ርዕሰ መዲና ዊንድሆክ በተካሄደው 50ኛው የድርጅቱ ኮንፈረንስና ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተመርጠው ድርጅቱን በምክትል ፕሬዚዳንት ሲመሩ እንደነበርም ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ 

አቶ ያሬድ ከናሚቢያዊቷ ሚስ ፓቲ ማርቲን የፕሬዚዳንትነት ኃላፊነታቸውን በተረከቡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር የመላው አፍሪካ ኢንሹራንስ ድርጅት ለዚህ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊነት ስለመረጣቸው ልባዊ ምሥጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በድርጅቱ ውስጥ በሚኖራቸው የቆይታ ጊዜ በትጋትና በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ በተለይም የአፍሪካ አገሮች በኢንሹራንሱ ዘርፍ ያላቸው ዕድገት ከዓለም አገሮች ጋር ሲነፃፀር እጅግ ደካማ በመሆኑ፣ ይህን ታሪክ ለመቀየር የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት እንደሚጥሩ ቃል ገብተዋል፡፡ 


በተለይም በፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው ሦስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሠሩም ገልጸዋል፡፡

በኃላፊነት ዘመናቸው እሠራዋለሁ ብለው በቅድሚያ የጠቀሱት ኢንሹራንስ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያካተተ እንዲሆንና በአገሮች ኢኮኖሚ ላይ ያለው አስተዋጽኦ የጎላ እንዲሆን፣ በተለይም ኢንሹራንስ በሚገባ ባልተዳረሰባቸውና አነስተኛ ገቢ ባላቸው የኅብረተሰብ ክፍል ላይ አኅጉሩ ትኩረት እንዲያደርግ የሚል ነው፡፡


የኢንሹራንስ ሬጉሌሽንና የኢንሹራንስ ሙያና ባለሙያ የማሳደግና የማጠናከር ሥራ፣ እንዲሁም ኢንሹራንስን ያማከለ ፈጠራና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ማሳደግና ማስፋፋት ሌላው ትኩረት የሚያደርጉበት ሥራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ 


አቶ አቶ ያሬድ በኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው ላይም ከ30 ዓመታት በላይ የካበተ ልምድ አላቸው፡፡ አቶ ያሬድን በተመለከተ ከኒያላ ኢንሹራንስ ያገኘነው ተጨማሪ መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በስትራቴጂክ የሥራ አመራር፣ በሥጋት አመራርና በገበያ ልማት ሥራዎቻቸው ተጠቃሽ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪን ለማዘመን፣ ብቃት ያለው የኢንሹራንስ ባለሙያ እንዲኖር፣ በተለይም ኢንዱስትሪው ራሱን ችሎ እንዲመራ የሚመለከታቸውን አካላት ሁሉ በማግባባት የማኅበረሰቡን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ አዳዲስ የኢንሹራንስ አገልግሎቶች እንዲስፋፉ ሲደረጉ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡ 


በአፍሪካ ኢንሹራንስ ድርጅት የ53 ዓመታት ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ93 አገሮች ቁጥራቸው 1,900 የሚሆን ከመላው አፍሪካ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅ፣ ከአውሮፓና ከሌሎች ዓለማት የመጡ የኢንሹራንስ ባለሙያዎች፣ የፋይናንሺያል ኢንዱስትሪ ኤክስፐርቶች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የቴክኖሎጂ አጋሮችና ኢንሹርቴኮች የተሳተፉ ሲሆን፣ በኢንሹራንስ ዘርፍ የተደረጉ ጥናቶችና የምርምር ውጤቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡


የአፍሪካ ኢንሹራንስ ድርጅት እ.ኤ.አ. በ1972 ዓ.ም. የተመሠረተ መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ሲሆን፣ ዋና ግቡም በመላው አፍሪካ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪው በውድድር ላይ የተመሠረተ ጤናማ ዕድገት እንዲያስመዘግብ አስተዋጽኦ ማድረግ ነው፡፡


በመዝጊያ ፕሮግራሙ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ፣ የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ለመቀየር የተለያዩ ሥራዎችን እየተሠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዕለቱም የውጭ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆንም ጠቅሰዋል፡፡ 

ከሪፖርተር ጋዜጣ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በአዲስ አበባ የታክስ ዕዳ ምህረት አሰጣጥን የሚያስተዳድር አዲስ ረቂቅ መመሪያ ወጣ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ቢሮ፣ በተለያዩ ከግብር ከፋዮች...

እግዚአብሔር የሰጠኝን ተልዕኮዎች ፈጽሜያለሁ የአዛዥነት ዘመኔ እያበቃ ነው

የኡጋንዳ የመከላከያ ኃይሎች አዛዥ (CDF) ጄነራል ሙሁዚ ካይኔሩጋባ ከወታደራዊ...

አሐዱ ባንክ 1ነጥብ 07 ቢሊዮን ብር አተረፈ

ባንኩ በተጠናቀቀው የሂሳብ ዓመት ከ3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር...

በጋምቤላ ከምሽት አንድ ሰዓት በኋላ ነዋሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ ተከለከለ

ከጋምቤላ ክልል ዋና ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ በሚገኘው ጋምቤላ...