በዚህ ዓመት የሚሰጠውን የ2018 የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ሀገር አቀፍ ፈተና መቶ በመቶ በበይነ መረብ ለመስጠት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ” በዚህ ዓመት የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ፈተና መቶ በመቶ በበይነ መረብ ይሰጣል ” ሲሉ ተናግረዋል።
ይህን ያሉት በአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ የግማሽ ዓመት አፈፃፀም መድረክ ላይ ተገኝተው ነው።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ፈተናው በወረቀትና በበይነ መረብ ሲሰጥ እንደነበር አንስተው፥ በዚህ ዓመት የሚሰጠውን ማጠናቀቂያ ፈተና ሙሉ በሙሉ በበይነ መረብ ለመስጠት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ ጠቁመዋል።
ለዚህም የተለያዩ ግብዓቶች ለክልሎች ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰው በፈተና ጣቢያዎች በቂ የኢንተርኔት አቅርቦት እንዲኖር ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመነጋገር ይሰራል ብለዋል።
ክልሎች በዚህ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮች እንዳይኖሩ በቂ ኮምፒዩተር ፣ ኔትዎርክና አማራጭ የሀይል አቅርቦት እንዲኖር ልዩ ትኩረት ሰጥተው መዘጋጀት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ለተማሪዎችም በቂ ሥልጠና መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
