የድምፃዊ ሰማኸኝ በለው (ሰሜ-ባላገሩ) አጭር የህይወት ታሪክ

Date:


“አፈር ለሚበላው ለሚበሰብሰው፣
ለዚህ ፈራሽ ገላ ቁምጣ መች አነሰው።”

መዝሙር 89፥48:
ሕያው ሆኖ የሚኖር፥ ሞትንስ የማያይ ማን ነው?
ነፍሱንስ ከሲኦል እጅ የሚያድን ማን ነው?

  1. ውልደት እና የልጅነት ዘመን

ድምፃዊ ሰማኸኝ በለው (በቅጽል ስሙ “ሰሜ-ባላገሩ”) ከአባቱ ከአቶ በለው ሹምየ እና ከእናቱ ከወይዘሮ እናትነሽ ቢልልኝ መስከረም 17 ቀን 1960 ዓ.ም. ውብ በሆነችው፣ የአባይ እና የጣና መፍለቂያ በምትባለው ባህር ዳር ከተማ ተወለደ።
ያደገውም በዚሁ ከተማ “ቀበሌ 03” (በተለምዶ አባ ፋሲሎ ትምህርት ቤት አካባቢ) በሚባለው ሰፈር ነው። ከልጅነቱ ጀምሮ ለድምፅና ለሙዚቃ ልዩ ፍቅርና ተፈጥሯዊ ተሰጥኦ የነበረው ሲሆን፣ በሰፈሩና በጓደኞቹ ዘንድ በማራኪ ድምፁ እና በደግነቱ እጅግ ይታወቅ ነበር። ገና በ14 ዓመት ታዳጊነቱ በባህር ዳር ሕጻናት ኪነት ቡድን ውስጥ በመሳተፍ የረጅም ዘመን የጥበብ ጅማሮውን መሠረት ጥሏል።

ሰሜ ድምፃዊ ብቻ ሳይሆን የግጥም፣ የዜማና የቲያትር ደራሲም የነበረ ሲሆን ቀልዶችንም በተፈጥሮአዊ ዘይቤ በማቅረብ ለኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ ደምቆ የሰራ ባለሙያ ነበር።

  1. የትምህርት ህይወት

የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በትውልድ ከተማው በባህር ዳር ያጠናቀቀ ሲሆን በትምህርት ቤት ቆይታውም በትምህርቱ ጎን ለጎን በኪነ-ጥበብ ክበባት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ነበር፦

  • አንደኛ ደረጃ፦ በሰርፀ ድንግል አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት
  • መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ፦ በአባ ፋሲሎ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት
  • ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ፦ በጣና ሃይቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሯል።
  1. ወደ ሙዚቃው ዓለም መግባትና የጥበብ እድገት

የሰማኸኝ የኪነ-ጥበብ ጅማሮ ከቀበሌና ከከፍተኛ ተነስቶ በወቅቱ የነበረውን የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ወጣቶች ማህበር (አኢወማ) ክፍለ ሀገሩን እስከመወከል የደረሰ ነበር። ለሙያው ያለው ልዩ ፍቅርና ታታሪነት በብዙዎች ዘንድ ግንዛቤ በማግኘቱ፣ ህዳር 11 ቀን 1978 ዓ.ም. በወጣትነት ዕድሜው የጎጃሙ ዝነኛ የኪነት ቡድን “ግሼ አባይ” አባል ለመሆን በቃ።

  • የኪነት ቡድን አሻራ፦
    በ”ግሼ አባይ” ውስጥ በርካታ ምርጥ ባህላዊ ስራዎችን ያቀረበ ሲሆን በተለይም ከታዋቂዎቹ ድምፃውያን ከነይሁኔ በላይ እና ከሀብቱ ንጋቱ (አንሙቴ) ጋር በመሆን ያቀረበውና ለአራት አስርተ ዓመታት ያህል በሕዝብ ልቦና ውስጥ ታትሞ የኖረው “አንቱየዋ” የተሰኘው አስደናቂ ሙዚቃዊ ድራማ በታሪኩ ትልቅ ቦታ አለው።
  • የሽግግር ወቅት (የአዲስ አበባ ህይወት ጅማሮ)፦
    በ1982 ዓ.ም. የከተማዋና የአካባቢው የኪነ-ጥበብ ስራዎች መቀዛቀዛቸውን ተከትሎ ሰማኸኝ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ከታዋቂው ታንጎ ሙዚቃ ቤት ጋር በመሆን የመጀመሪያውን የሙዚቃ አልበሙን አሳተመ። በመቀጠልም ከኤሌክትራና ከተለያዩ በዘመኑ አሉ ከተባሉ አሳታሚዎች ጋር ሰርቷል። ይህንንም ተከትሎ ኑሮውን በአዲስ አበባ አደረገ። ከዚህም በመቀጠል “ያዢኝ አላበድሁም” የሚለውንና ሌሎችንም በህዝብ ዘንድ እጅግ ተወዳጅ የሆኑ ሥራዎችን በተከታታይ ከሙያ አጋሮቹ ጋር በመሆን ለህዝብ አቅርቧል፤ ይህም ለሙያው ከፍተኛ ዝናን አጎናጥፎታል።
  • የምሽት ክለቦችና የካዛንችስ አሻራ፦
    ከ1983 ዓ.ም. ጀምሮ በሶስና የምሽት ክበብ፣ ከ1988-1989 ዓ.ም. በአይቤክስና በሸዋ ጌጥ የምሽት ክበባት ውስጥ በድምፃዊነት ካገለገለ በኋላ፣ በ1990 ዓ.ም. በካዛንችስ የራሱ የሆነውን የባህልና ዘመናዊ ምሽት ቤት በመክፈት በወቅቱ ደክሞ የነበረውን የጥበብ ስራ እንደገና እንዲጎመራ እና እንዲያንሰራራ ለማድረግ በግሉ ለኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።
  • በትያትር ዘርፍ የነበረው ተሳትፎ፦ ሰሜ ከሙዚቃውም ባሻገር በትያትር ዘርፍ ባለ ሙሉ ተሰጥኦ የነበረ ሲሆን፣ በብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ከፍተኛ ህዝባዊ ተቀባይነት ያገኘነውን “የባላገር ፍቅር” የተሰኘውን ተውኔት ጨምሮ በተለያዩ ልዩ ልዩ ሙዚቃዊ እና ተውኔታዊ ሥራዎች ላይ በቅንነትና በብቃት ተሳትፏል።
  • የሙዚቃ ስልቱ፦ ሰማኸኝ በተለይ የጎጃም ባህላዊ ዜማዎችን (ባቲ፣ አምባሰል፣ ትዝታ እና አንቺሆዬን) በመጨመር ከዘመናዊ የሙዚቃ ስልቶች (Modern Beats) ጋር አቀናጅቶ በማቅረብ አዲስ መንገድ የቀደደ ድምፃዊ ነው።
  1. ታዋቂ የሙዚቃ ስራዎቹ

ሰሜ ባላገሩ በረጅም ዓመታት የጥበብ ስራዎቹ የሀገር ባህል የሙዚቃ ዘርፍን ወጉን እና ስርዓቱን ጠብቆ በከፍተኛ ደረጃ ያስተዋወቀ የጥበብ ባለውለታ ነው።

ዋና ዋና አልበሞች እና ስራዎች

  • “ባላገር”፦
    ‘ባላገር’ የሚለው ቃል በከተሜው ማህበረሰብ ዘንድ እንደ ‘አልሰለጠነ’ ኋላቀርነት መገለጫ በሆነበት ዘመን፣ ይህንን ተገቢ ያልሆነ ትችትና ልማድ ለመቀየር በቁጭት በመነሳት በኪነ-ጥበባዊ ዘይቤ ‘ባላገር ነኝ’ በማለት በድፍረት ሰብሮታል። በሄደበትና ሙያውን ባስተዋወቀባቸው ዓለማትና መድረኮች ሁሉ እንደ አርሶ አደር በመልበስና የመገልገያ ዕቃዎችን በማስተዋወቅ፣ እራሱ አርሶ አደሩን በመሆን ጭምር ለባላገሩ ያለውን ፍቅር በክብር አሳይቷል። የአርሶ አደሩን ውብ እሴት፣ ባህልና ወግ በአድናቆት የዘከረበት ይህ ስራው የእውቅናው ሁለተኛውና ከአንቱየዋ ሊስተካከል የሚችል መጠሪያው ሆኗል። ከዚህ በኋላም ሰማኸኝ በለው መባሉ ቀርቶ ‘ሰሜ ባላገሩ’ እየተባለ መጠራት ጀምሯል።
  • “ውቧ ባህር ዳር” (ዲስካው)፦
    ለትውልድ ከተማው ያለውን ጥልቅ ፍቅርና ናፍቆት የገለጸበት ተወዳጅ ስራው ነው። በዚህ ሥራው ውቧን ባህር ዳር ከልጅነት መንደሩ እስከ አጠቃላይ ገፅታዋ የገለጠበት፣ ፍቅርን፣ ጨዋታን፣ የመንደሩን አኗኗር ዘይቤ፣ ቅይጥ ውበትንና በዚህ ውስጥ የትውልድ ከተማውን ለሁሉም አብሮ አደጎቹ በትዝታ አስቃኝቷል።
  • “ደቦት እንስራ”፦ የልጅነት ትዝታንና የገጠሩን ባህል በተለይ መስከረምን ተከትሎ ያሉትን ሃይማኖታዊ በዓላት (ከዘመን መለወጫ እስከ መስቀል) ያለውን በጣም አስደሳች እና ውብ በዓል በትዝታ ላለፍንበት የሚያስታውስ፣ ለማያውቁት ደግሞ መስከረም በመጣ ቁጥር ያለውን ውብ የፀደይ ወቅት ያሳየበት፣ መስከረምን በልዩ እንድንናፍቀው የሚያደርግ ውብ የኪነ-ጥበብ ሥራው ነው።
  • “ዘገኛ”፦
    በጥንተ ባህላዊ ትውፊት የተቃኜውን በፈጣን ውዝዋዜ የታጀበና በዓይነቱ ውብ የሆነ፣ ወደ ህዝብ ያልወጣን ባህል ደምቆ እንዲወጣ ያደረገበት ድንቅ የአዘፋፈን ስልት ነው።
    ሌሎች ተወዳጅ የባህልና የትዝታ ስራዎቹ

ተወዳጅ ዜማዎች

  • ኧረ ምኑን ሰጠሽ
  • እንቆቅልሽ
  • አውደ ዓመት
  • ማነሽ ማነሽ
  • አለሽ ነገር
  • የኔ አለም
  • ዝናቡ
  • አለም እንደምነሽ

ተጠቃሽ ናቸው።

ሰሜ ባላገሩ እነዚህንና ሌሎች ተወዳጅ ሥራዎቹን በተለያዩ ጊዜያት በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በእስራኤል እና በአረብ አገራት ለሚኖሩ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ባቀረባቸው ኮንሰርቶች አገራዊ ናፍቆትን በመወጣት ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል፤ ሀገራቸውን እንዳይረሱና በባህላቸው እንዲኮሩ የበኩሉን ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።

  1. ልዩ መገለጫው (የመድረክ ብቃቱ)
  • ደማቅ ፈገግታው፦ መድረክ ላይ ሲወጣ መቼም ቢሆን ከፊቱ የማይጠፋውና ተመልካችን ማራኪ በሆነ ኃይል የሚስበው ደማቅ ፈገግታው ልዩ መለያው (Signature) ነበር።
  • ያለ ድምፅ ማጉያ የመጫወት ብቃት፦ የድምፁ ጉልበት እና ጥራት እጅግ አስደናቂ ከመሆኑ የተነሳ ያለ ምንም የድምፅ ማጉያ (Mic) መድረክን የመሙላትና አድማጭን የመማረክ ልዩ ተሰጥኦ ነበረው።
  • የመድረክ አያያዝ (Performance)፦ ከተመልካች ጋር በቀላሉ የመቀራረብ፣ ሰውን የማስደሰትና መድረኩን ሙሉ በሙሉ የመቆጣጠር ልዩ ተፈጥሯዊ ስጦታም ነበረው።
  1. ለፍትህ የነበረው የፀና እምነት እና የማህበረሰብ ተፅዕኖ
    ‘ሰሜ ባላገሩ’ በ1991 ዓም በደረሰበት የመኪና አደጋ ምክንያት በወንጀል ተጠርጥሮ ፍርድ ቤት ሲመላለስ ቢቆይም፣ በመሃሉ ለሥራ ወደ አሜሪካ መሄድ ነበረበት። በሥራ ላይ እያለም በተጠረጠረበት ወንጀል የ4 ዓመት የእስር ፍርድ እንደተፈረደበት ሰማ።

ብዙዎቻችን እንኳንስ እስር ተወስኖብን፣ እንዲያውም ውጭ ናፋቂ በሆንበት ጊዜ ሰሜ ግን ፍትህንና ህግን በማክበር ሥራውን አቋርጦ ወደ ሀገሩ በመመለስ፣ ቤተሰቦቼንም ልይ ሳይል ቦሌ አውሮፕላን ጣቢያ ላይ እጁን ለፓሊስ በመስጠት ለህግ ተገዥነትን በተግባር አስተምሯል።

  • “ሰሜ ድልድይ”፦ ከዚሁ የመኪና አደጋ ጋር ተያይዞ አደጋው የተከሰተበት ድልድይ እሱን ለመዘከር ‘ሰሜ ድልድይ’ እየተባለ ቋሚ መጠሪያ ተሰጥቶታል።
  • “ሰሜ መንደር”፦ የመኖሪያ መንደሩ ከነዋሪው ቀድሞ የገባና ከነበሩት አርሶ አደሮች ጋር በነበረው ሰላማዊ ግንኙነት የተነሳ አካባቢው ‘ሰሜ መንደር’ እየተባለ እንዲጠራ ሆኗል።
  • የብርታት ተምሳሌት (ኖኪያ ሰሜ ባላገሩ)፦ በወቅቱ በሀገራችን ማህበረሰብ የተንቀሳቃሽ ስልክ መጠቀም በጀመረበት ወቅት የኖኪያ ስልክ ምርት (Nokia 3310) ‘ሰሜ ባላገር’ ተብሎ እስከማስጠራት የደረሰ ተፅዕኖ ፈጣሪ ነበር። ይህም ስልኩ ከነበረው ጥንካሬና ወድቆ አይሰበሬነት የተነሳ ከሰሜ የብርታትና የጥንካሬ ተምሳሌትነት ጋር ተያይዞ የተሰጠው ስያሜ ነበር።
  1. የቤተሰብ ህይወት

ሰሜ ባላገር ከተሰጥዎው ባሻገር በተገኘበት ቦታ ሁሉ ሳቅን የሚፈጥር እጅግ ተጫዋች እና ቀልድ አዋቂ ነበር። በአንድ ወቅት “ሦስት ነገር እወዳለሁ፤ ሀገሬን፣ ትዳሬን እና ሥራዬን” በማለት መርሁን የገለጸ ሲሆን ይህንንም በተግባር ያሳየና ቋሚዎች የሆንን ወዳጆቹ ሁሉ የምንመሰክርለት እውነት ነው።

ሰማኸኝ በጥበብ ህይወቱ ስኬታማ እንደነበረው ሁሉ በቤተሰብ ህይወቱም የተባረከ አባት እና ባል ነበር። በ1982 ዓ.ም. ከወይዘሮ ገበያነሽ አባተ ጋር የትዳር ህይወት የመሰረተ ሲሆን የአራት ታላላቅ ምሁራን ወንድ ልጆች አባት ለመሆን በቅቷል፦

  1. ኢንጂነር ቢኒያም ሰማኸኝ
  2. አርክቴክት እስራኤል ሰማኸኝ
  3. ኢንጂነር አብርሃም ሰማኸኝ
  4. አቤል ሰማኸኝ

ሰሜ የእነዚሁ የልጆቹን ፍሬ፣ የ4 የልጅ ልጆች ለማየት በመታደል በቤተሰቡና በልጆቹ ደስታ ይበልጥ የተባረከ አባት ለመሆን በቅቷል። ልጆቹን በጥሩ ስነ-ምግባርና እውቀት ኮትኩቶ በማሳደግ እንዲሁም ልዩ አባታዊ ፍቅርን በመስጠት ረገድ ለአካባቢው ማህበረሰብ ትልቅ አርአያና አስተማሪ የነበረ የቤተሰብ መሪ ነበር።

  1. ማህበራዊ ህይወት እና በጎ አድራጎት

ሰሜ በጥበቡ ብቻ ሳይሆን ማህበራዊ ህይወትን በመደገፍና በቸርነቱ የሚታወቅ ታላቅ ሰው ነበር፦

  • ጓደኝነት እና ታማኝነት፦ ከትውልድ ከተማው ከባህር ዳር ጀምሮ የልጅነት ጓደኞቹን፣ አብሮ አደጎቹን፣ የሙያ አጋሮቹን እና በልዩ ልዩ ሁኔታ የተወዳጃቸውን ወዳጆቹን መቼም ቢሆን የማይረሳ፣ ለታመሙት ደራሽና ጠያቂ ነበር። የጭንቅና የችግር ቀናት ሲከሰቱም የሙያና የገንዘብ እርዳታ ዝግጅቶችን ሙሉ በሙሉ በነፃ አገልግሎት በመስጠት ያግዝ ነበር።
  • የአባቶች እሴት እና እንግዳ ተቀባይነት፦
    ወደ ቤቱ ለዘለቀ እንግዳ የጥንቱን የአባቶች ሃይማኖታዊ እሴት በተላበሰ መልኩ የእንግዶችን እግር አጥቦ፣ አብልቶና አጠጥቶ፣ አልጋ ለቆ ለዘመድ አዝማድና ለእንግዳ የሚያሳየው ልዩ ወንድማዊ ፍቅር መቼም ቢሆን የሚረሳ አይደለም።
  • ለአረጋውያን ደራሽነት፦
    የአረጋውያን መርጃ ማህበር ስራዎች ላይ በጉልህ በመሳተፍ፣ አረጋውያንን በመደገፍና በመርዳት ትልቅ ማህበራዊ አርአያነት አሳይቷል፣ ግዴታውንም ተወጥቷል።
  • ለባህር ዳር ከተማ ያለው ውለታ፦
    በትውልድ ከተማው በባህር ዳር ልዩ ልዩ ማህበረሰብ አቀፍ ዝግጅቶች ሲኖሩም በነፃ አገልግሎት በመስጠት የከተማዋን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ያግዝ ነበር።
  • የመንፈሳዊ አገልግሎት አሻራ፦
    በአዲስ አበባ በሚኖርበት በቦሌ ቡልቡላ አካባቢ የሚገኘው ቡልቡላ መድኃኔዓለም ህንጻ ግንባታ ከመጀመሪያው ጀምሮ በልማት ኮሚቴነት ተመርጦ በንቃት አገልግሏል። ገቢ በማሰባሰብና አቅሙን፣ እውቀቱንና ጉልበቱን በሙሉ በመስጠት ያበረከተው በጎ አስተዋጽኦ ሁልጊዜም በቤተክርስቲያኗ ታሪክ ውስጥ የማይረሳ ትልቅ አሻራው ነው። በሰበካ ጉባኤ አባልነት ተመርጦ በቅንነት፣ በታማኝነትና በፍፁም ፍቅር ቤተክርስቲያንን አገልግሏል።
  • የቤተክርስቲያን ገቢ ማዳበር፦
    ቤተክርስቲያኗ ገቢዋ እንዲዳብርና ካህናት የተሻለ ደሞዝ እንዲያገኙ በማሰብ የብሎኬት ማምረቻ ማሽን ገዝቶ በነፃ አበርክቷል።
  • ለህዳሴው ግድብ ያበረከተው አስተዋጽኦ፦
    ለታላቁ የህዳሴ ግድብ ልዩ ዜማና ግጥም በመፍጠር ህብረተሰቡን በኪነ-ጥበባዊ መንገድ ድጋፍ እንዲያደርግ አነሳስቷል፤ ታሪካዊ ድርሻውንም ተወጥቶ አሻራውን አኑሯል።
  • የአገር ፍቅር እና ጀግንነት፦
    ሰሜ ባላገር በአገራዊ ጥሪዎች በሙሉ የተጣለበትን ኃላፊነት በቅንነት የተወጣ አገር ወዳድ ነበር። አገር በተወረረችበት ወቅትም እስከ ግንባር ድረስ በግንባር ቀደምትነት በመጓዝ ሰራዊቱን ያበረታታ፣ የቀሰቀሰ፣ ለሀገር ክብር የቆመና ግዳጁን በጀግንነት የተወጣ የጥበብ ሰው ነበር።
  1. ህልፈተ ህይወት

ሰሜ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከመደበኛ በላይ የሆነ ውፍረቱ ይህ ነው የተባለ የጤና ችግር እንዳልፈጠረበት ከአንድ አመት በፊት በመገናኛ ብዙሃን ተናግሮ ነበር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ውፍረቱን ለመቀነስ የተለያዩ የህክምና ዘዴዎችን ሲከታተል የቆየ ሲሆን ጥሩ ለውጥ እያመጣ መሆኑን በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲገልጽ ነበር።

በመጨረሻም፤ ሰኞ ሰኔ 8 ቀን 2018 ዓ.ም. ጠዋት የድካም ስሜት ተሰምቶት በልጆቹ አማካኝነት ወደ ሆስፒታል እየተወሰደ ሳለ በድንገት በመድከሙ፣ ሆስፒታል ደርሶም እርዳታ ቢደረግለትም ባለማገገሙ ብዙም ሳይቆይ ህይወቱ አልፏል።

ይህ ታላቅ ድምፃዊ በህይወቱ የመጨረሻዎቹ ወራት ላይ ከሙዚቃው ዓለም በመጠኑ ራቅ ብሎ የነበረ ቢሆንም በቅርቡ ግን የኢትዮጵያን አንድነትና ጀግንነት መሪ ለሆኑት ንጉስ ማስታወሻ የሚሆን “ቴዎድሮስ” የተሰኘች ድንቅ ነጠላ ዜማ ለህዝብ አድርሶ ነበር። ሰማኸኝ በገጠመው ድንገተኛ የድካም ስሜት ምክንያት በተወለደ በ58 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ህልፈቱ በኢትዮጵያ የሙዚቃ የትያትር እና የማህበራዊ አገልግሎት ዘርፍ ላይ ትልቅ ክፍተት የፈጠረ የሀዘን መርዶ ነው።

ማጠቃለያ እና መዝጊያ
ሰማኸኝ በለው (ሰሜ-ባላገሩ) ከባህር ዳር ሰርፀ ድንግል ተነስቶ በ”ግሼ አባይ” የኪነት ቡድን ውስጥ አልፎ በብሔራዊ ቴአትር መድረክ አብርቶ በብርቱ ትግል የኢትዮጵያን የሙዚቃና የትያትር ጥበብ በክብር ያገለገለ ባለብዙ መክሊት የጥበብ ሰው ነው። በቅንነቱ በእንግዳ ተቀባይነቱ በሀገር ፍቅሩ በማህበራዊ ህይወት ተሳትፎውና በበጎ አድራጎቱ የብዙዎችን ህይወት የባረከው ሰሜ ስሙ ታሪኩ እና የማይረሱት የጥበብ ስራዎቹ በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ሁልጊዜም በክብርና በናፍቆት ሲታወሱ ይኖራሉ።

ሰሜ በመጨረሻም የአምላክ ቃል በዘፍጥረት 3፥19 ላይ፦
“ወደ ወጣህበት መሬት እስክትመለስ ድረስ በፊትህ ወዝ እንጀራን ትበላለህ፤ አፈር ነህና፥ ወደ አፈርም ትመለሳለህና።”
እንዲል “ሰው በምድር ላይ ዘመኑን ፈጽሞ ወደ ዘላለም ቤቱ ይሄዳል። ሰው ከአፈር ተፈጥሮ ወደ አፈር ይመለሳል፤ ነገር ግን መልካም ሥራውና ፍቅሩ በሕይወት ይኖራል።” ነውና መልካሙን ሥራ አስቀምጦ ወደማይቀረው የሥጋ ሞት ሄዷል።

“ሞት የሥጋ መለየት እንጂ የመንፈስ መጥፋት አይደለም። ዛሬ ከእኛ ቢለይም በፍቅርና በትዝታ ሁሌ ከእኛ ጋር ይኖራል።”
ለሚወዱት ቤተሰቡ ለአብሮ አደግ ወዳጅ ዘመዶቹ እና ለመላው አድናቂዎቹ ቀጣይ የህይወት ስንቅ ነው።

ስርዓተ ቀብሩም ዛሬ ማክሰኞ ሰኔ 9 ቀን 2018 ዓ.ም. በቦሌ ቡልቡላ ደብረ መድኃኒት መድኃኒዓለም ቤተክርስቲያን በክብር ተፈፅሟል።

ፈጣሪ ነፍሱን በገነት ያሳርፋት!

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ዜጋዬ ተገድሏል ያለችው ጋና ከደቡብ አፍሪካ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ውዝግብ ውስጥ ገባች

አንድ ጋናዊ በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ ካለው ፀረ ስደተኞች ተቃውሞ...

«የማይናገረው ልዑል» መጽሐፍ በታላቅ ድምቀት ሊመረቅ ነው

ደራሲ መሠረት ክንፈ ኃይሌ ከኦቲዝም ጋር ከሚኖረው ልጇ ልዑል...

በኢትዮጵያ እና በኬንያ ድንበር የሚደረግ ንግድ በገንዘብ መጠን ተገደበ

የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር በኢትዮጵያ እና በኬንያ ድንበር የሚከናወነውን...

(IMF) ከ460 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብድር አፀደቀ

አዳዲስ ብድር በመውሰድ ረገድ ጥንቃቄ እንድታደርግ ኢትዮጵያን ያስጠነቀቀው IMF...