የዶ/ር ፍቅሩ ማሩ የቀብር ስነ-ስርዓት በስዊድን ሀገር ይፈፀማል

Date:

በኢትዮጵያ በግል ህክምናው መስክ በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነው የአዲስ የልብ ህክምና ሆስፒታል እና ታዝማ የውስጥ ደዌ እና የቀዶ ልዩ ህክምና ማዕከል መስራች የሆኑት ካርዲዮሎጂስት ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ከዚህ አለም ድካም አርፈዋል።

በአዲስ አበባ ፈረንሳይ ለጋሲዮን በተለምዶ ጉራራ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሺ ዘጠኝ መቶ አርባ ሶስት ዓ.ም የተወለዱት ካርዲዮሎጂስት ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በኮከበ ፅባህ ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ት/ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም አሰላ በሚገኘው ራስ ዳርጌ ት/ቤት ተከታትለዋል።

በሺ ዘጠኝ መቶ ስልሳዎቹ መጀመሪያ ለሀገር ፍቅር ከነበራቸው ጥልቅ ስሜት በመነሳትም የኢትዮጵያ የአየር ኃይልነት ምልመላ ሲከናወን ትምህርታቸውን አቋርጠው የኢትዮጵያ አየር ኃይልን ተቀላቀሉ።

በወቅቱ አየር ኃይልን ለመቀላቀል ከተመለመሉ 27 እጩ አባላት መካከል በብቃት የአየር ኃይልነት ስልጠናን አጠናቀው በጀት አብራሪነት የተመረቁት 5 ብቻ ነበሩ፡፡ ከነዚህም ብቸኛው ጀት ስኳዶር ሆኖ የወጣው በዕድሜ ትንሹ የነበረው ፍቅሩ ማሩ ነበር።

በሺ ዘጠኝ መቶ ስልሳ ስድስት የአብዮቱን መፈንዳት ተከትሎ ደርግ ለስልጣኔ ስጋት ይሆናሉ ያላቸውን ግለሰቦች እያፈሰ ወደ እስር ቤት ማጋዝ ሲጀምር በሃገር ፍቅር ስሜት ተቆርቋሪነታቸው የሚታወቁትን የመቶ አለቃ ዶ/ር ፍቅሩንም ማሳደድ ይጀምራል፤ የህዝቦች እኩልነትና አንድነት ይረጋገጥ ዘንድ ይታገሉ የነበሩት ዶ/ር ፍቅሩም በደርግ እየታሰሱ መሆናቸውን ሲረዱ የሚወዱትን ሃገር ጥለው ወደ ሱዳን ይሰደዳሉ። ከዛም ወደ ስዊድን በመሻገር የስደት ህይወትን ይጀምራሉ። በወቅቱ እሳቸውን መያዝ ያልቻለው ደርግም ሁለት ወንድሞቻቸውን ይገድልባቸዋል።

በስዊድን ቆይታቸው በሃገራቸው የዲሞክራሲ ስርዓት እንዲገነባ በመላው አውሮፓ የሚገኙ የኢህአፓ የተማሪዎች ንቅናቄን በመምራት ጉልህ ሚናን ከመጫወታቸው በላይ በልብ ህክምናው ዘርፍ ስፔሻላይዝ በማድረግ በእስካንዴኔቪያን ሃገራት ጭምር አንቱታን ያተረፉ ካርዲዮሎጂስት ናቸው።

በሺ ዘጠኝ መቶ ዘጠናዎቹ መጀመሪያ የኤች አይ ቪ ቫይረስ ስርጭት እንደሃገር ስጋት በደቀነ ግዜ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ሃገራዊ ጥሪ ሲደረግ በስዊድን ያሉ አጋር ድርጅቶችን በማስተባበር ወደ ሃገር ቤት ቀድመው ከዘለቁ የሀገር ባለውለታ መካከል አንዱ ናቸው። ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ከሩብ ክፍለ ዘመን የስደት ህይወት በኋላ ወደ ሀገራቸው ሲመጡ በስፋት ያስተዋሉት ችግር በልብ ህክምና እጦት ምክንያት የሚሞቱ ህፃናትና ወጣቶች ቁጥር ማሻቀብ ነበር።

ያን ተከትሎ የችግሩን አሳሳቢነት የሚያሳይ አስፈላጊውን ጥናት በማድረግ ወደ ስዊድን ሃገር ተመልሰው የስዊድን መንግስትንና የስዊድን ፈንድ የመሳሰሉ አጋዥ ተቋማትን በማስተባበር ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ለሀገሪቱ ብቸኛ የነበረውን የልብ ህክምና ሆስፒታል ያቋቁማሉ።

ሰኔ ዘጠኝ ቀን ሺ ዘጠኝ መቶ ዘጠና ዘጠኝ ዓ.ም አዲስ የልብ ህክምና ማዕከል ተመሠረተ። ሆስፒታል ማቋቋም ብቻውን በዘርፉ ያለውን ችግር መቅረፍ እንደማይችል በማመን በርካታ የህክምና ባለ ሙያዎችን በራሳቸው /በዶ/ር ፍቅሩ/ ወጪ ስዊድን ድረስ በመላክ በልብ ህክምናው ስፔሻላይዝድ ያደረጉ እውቅ ሀኪሞችን በማፍራት የሰለጠነውን አለም የህክምና ሙያ ወደ ሀገር በማምጣት ለእውቀት ሽግግር ብርቱ ዋጋ ከፍለዋል። በዚህም በሰለጠነው አለም ብቻ ይሰጥ የነበረውን ውስብስብ የተባለ የልብ ህክምና ወደ ሀገራችን በማምጣት ጉልህ ሚና የተጫወቱ የሀገር ባለውለታ ናቸው, ካርዲዮሎጂስቱ ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ፡፡

ለወትሮው ህክምናውን ፍለጋ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወደ ውጪ ይደረግ የነበረውን ጉዞ በማስቀረት ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ሀገሪቱ ልታወጣ የምትችለውን የውጭ ምንዛሪ በማስቀረት አሻራቸውን ያኖሩት ዶ/ር ፍቅሩ፤ በአዲስ ካርዲያክ የማይሰጡ የልብ ህክምናዎች የሚደረግበትን ታዝማ የውስጥ ደዌ እና የቀዶ ልዩ ህክምና ማዕከልንም በመመስረትና አሁን ለደረሰበት ደረጃ በማብቃት ዛሬ በርካታ ህፃናትና ወጣቶችን በልብ ህክምና እጦት ምክንያት ከሚነጥቀው ሞት መታደግ የቻሉ ታላቅ የሃገር ባለውለታ ናቸው።

በጥቁር አንበሳ የሚሠጠውን የልብ ህክምና ለማዘመን ያላሰለሰ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩት ዶ/ር ፍቅሩ በተለያዩ ጊዜያት በውድ ዋጋ የሚገዙ አላቂ የህክምና መሳሪያዎችን በእርዳታ በማቅረብ በርካታ አስተዋፆ አበርክተዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሲመሠረት በወቅቱ በነበሩት የጤና ሚኒስቴር ተመርጠው በተጣለባቸው ሃገራዊ ኃላፊነት መሠረት የግል የጤና ተቋማትን በማስተባበር ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ እንዲሰበሰብ በማድረግ ደማቅ አሻራቸውንም አኑረዋል።

በጦርነቱ ወቅት የተጎዱ ት/ቤቶችንና ተቋማትን ለማገዝ በሚደረግ ርብርብ ውስጥ ሰፊ አበርክቶ የነበራቸውም ታላቅ ሰው ነበሩ።

”በሀገርና በህዝብ ቂም የለም” የዶ/ር ፍቅሩ ፅኑ እምነት ነው።

ለሃገራቸው ፅኑ ፍቅር ያላቸው ዶ/ር ፍቅሩ ባለፈው ስርዓት በተለያየ ወቅት ለእስር ተዳርገዋል፡፡ ታድያ ስርዓተ ለውጡን ተከትሎ ከእስር ቤት ሲወጡ ዜግነት ወዳላቸው ስዊድን ሀገር ለህክምና ይጓዛሉ። በዛን ወቅት ተመልሰው አይመጡም ተብሎ ብዙ ሲናፈስ እርሳቸው ግን በጥቂት ሳምንታት ነበር ወደ ሀገራቸው ተመልሰው የገቡት። ‘ይሄ ሁሉ በደል ደርሶብዎ እንዴት ወደ ሀገርዎ ሊመለሱ ቻሉ?’ ተብለው ሲጠየቁ ምላሻቸው አጭርና ግልፅ ነበር ” በሀገርና በህዝብ ቂም የለም” ነበር ምላሻቸው።

ላለፉት አስራ ዘጠኝ አመታት በኪራይ ቤት አገልግሎት ሲሰጥ የቆየውን አዲስ የልብ ህክምና በዘርፉ የሀገሪቱ የልህቀት ማዕከል ለማድረግ ከነበራቸው ጥልቅ ፍላጎት በመነሳት ለመኖሪያነት በገዙት መሬት ላይ ደረጃውን የጠበቀ ባለ ስምንት ወለል ህንፃ በመገንባት በቅርቡ ሆስፒታሉን ወደ አዲስ ምዕራፍ በማሸጋገር ሂደት ላይ ነበሩ።

ነገር ግን ባጋጠማቸው የጤና እክል ምክንያት በስዊድን ሀገር ህክምናቸውን ሲከታተሉ ቆይተው በተወለዱ በ74 አመታቸው ከዚህ አለም ድካም አርፈዋል።

ካርዲዮሎጂስት ዶ/ር ፍቅሩ ባለትዳርና የሁለት ሴት ልጆች አባት እንዲሁም የአራት የልጅ ልጆች አያት ነበሩ።

የዶ/ር ፍቅሩ ማሩ የቀብር ስነ-ስርዓት በስዊድን ሀገር የሚፈፀም ሲሆን በሀገር ውስጥ ሀዘን መካፈል ለሚፈልጉ አዲስ አበባ ጃክሮስ እግዚአብሔር አብ ቤተ-ክርስቲያን አጠገብ – ከቪዥን ት/ቤት ጀርባ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው መድረስ የሚችሉ መሆኑን እንገልፃለን፡፡

  • ቤተሰቦቻቸው
  • አዲስ የልብ ህክምና ሆስፒታል ማኔጅመንትና ሰራተኞች
  • ታዝማ የውስጥ ደዌ እና የቀዶ ልዩ ህክምና ማዕከል ማኔጅመንትና ሰራተኞች ለቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መፅናናትን ይመኛሉ፡፡

@HakimEthio

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ንባብ ለሕይወት ባዛር እየተካሄደ ነው !!!

በንባብ ለሕይወት ፕሮጀክትና በኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት አዘጋጅነት የሚካሄደው...

በኢራን የኤነርጂ መሠረተ ልማቶች ላይ ያነጣጠረ አዲስ መጠነ ሰፊ ጥቃት መታቀዱ ተሰማ

የአሜሪካ ጦር በዚህ ሳምንት መጨረሻ በኢራን ላይ አዲስ ጥቃት...

የብሔር ፌደራሊዝምን ለማስቀጠል “የቆረጡ” ተመካካሪዎች

በሀገራዊ የምክክር ጉባኤ 14ኛ ቀን ውሎ “ስልታዊ” ቡድኖች የአጀንዳ...

“የሩሲያ ክርስቲያኖች ከኢራን ሙስሊም ማህበረሰብ ጋር መልካም ግንኙነት አላቸው” ፓትርያርኩ

የሩሲያ ክርስቲያኖች ከኢራን ሙስሊም ማህበረሰብ ጋር መልካም ግንኙነት አላቸው...