በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ ውስጥ የሚገኘው የጆን ኤፍ ኬኔዲ መታሰቢያ ቤተ-መጻሕፍት የተመሠረተበትን 60ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉ በትላንትናው እለት ተከብሮለታል።
በበዓሉ አከባበር ወቅት የአሜሪካ ኤምባሲ ለቤተ-መጻሕፍቱ እድሳት የሚውል 235 ሺህ ዶላር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን፣ የእድሳት ሥራ በቅርብ ቀናት ውስጥ እንደሚጀምር ተናግሯል ።
ቤተ-መጻሕፍቱ ከእድሜ ብዛት የተነሳ የጣራ ማፍሰስ እና መጠነኛ ጉዳቶችን የደረሰበት በመሆኑ እድሳቱ የኤሌክትሪክ ዝርጋታን ጨምሮ ሙሉ በሙሉ እንደሚከናወን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቤተ-መጻሕፍት ዋና ኃላፊ ዶ/ር ለማ ለሣ ነግረውናል ።
እድሳቱ ስራ የሕንፃውን ነባር ዲዛይንና ታሪካዊ ገጽታ ሳይቀይር ባለበት ይከናወናል ተብሏል ።
ሙሉ የእድሳት ሥራው ከሁለት ዓመት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ እንደሚሆን ጠቁመዋል።
ከአሜሪካ ኤምባሲ የተገኘው የገንዘብ ድጋፍ ለሙሉ እድሳቱ በቂ ባለመሆኑ፣ የቤተ-መጻሕፍቱ እውቀት የቀሰሙ፣በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለዚህ በጎ ዓላማ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።
በ1958 ዓ.ም መሠረተ ድንጋዩ የተጣለውና የበርካታ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ትዝታ እንደሆነ የሚነገረው የጆን ኤፍ ኬኔዲ መታሰቢያ ቤተ-መጻሕፍት ፣ በወቅቱ በ5 ሚሊዮን ብር ወጪ በአሜሪካ መንግሥት ሙሉ ድጋፍ እንደተገነባ ዶ/ር ለማ አስታውሰዋል።
ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ ለበርካታ ትውልዶች የትምህርትና የምርምር አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው ቤተ መፅሃፍቱ ፣ አሁን ደግሞ ዘመኑን በሚመጥን መልኩ አገልግሎቱን ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ የማድረግ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነ ተጠቅሷል።
ይህ እድሳት አሮጌ ሕንፃን ከማደስ በላይ የብሔራዊ አካዳሚክ ቅርስን የመጠበቅና የወደፊቱን የከፍተኛ ትምህርት ዕጣ ፈንታ የማስቀጠል ትልቅ ዓላማ ያለው መሆኑ ተጠቁሟል።
ቤተ-መጻሕፍቱ መታደሱ ለሚመጡት ትውልዶች፣ ለምርምር፣ ለእውቀት ልውውጥና ለማህበረሰብ አገልግሎት የሚሰጠውን የጎላ አስተዋጽኦ አጠናክሮ እንዲቀጥል ያስችለዋል ተብሏል፡፡
ሸገር 102.1
