ቀጸላ ክፍሌ
ካለፉት ሃምሳና ስድሳ ዓመታት ወዲህ በአሀጉረ አፍሪካ መፈንቅለ መንግሥት ማድረግ ከዚያ ከፍ ሲልም መቋጫ አልባ የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ መዘፈቅ የተለመደ ተግባር ነው፡፡ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ይህ ተግባር በተለይ በምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ከዚህ አኳያ ከ1960ዎቹ ጀምሮ በዋናነት ሶማሊያ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ በእርስ በእርስ ጦርነት ሲታመሱ ኖረዋል፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ከፊል ሉዓላዊነቷን በትና ምንም እንኳን ለሃያ ሰባት ዓመታት ከዚህ አዙሪት ብትወጣም በዘላቂነት መላቀቅ አልቻለችም፡፡ በሶማሊያ ከጅምሩ ተፋፍሞ የነበረው የእርስ በእርስ ጦርነት አሁን ላይ በሦስትና በአራት ጎራ ተከፍሎ ተጧጡፎ ቀጥሏል፡፡ ሱዳንም እንዲሁም ሰሜን እና ደቡብ ተብላ ከተከፈለች በኋላም በየግላቸው እርስ በእርስ ከመታመስ ጋብ አላሉም፡፡ ኢትዮጵያችንም ከዓመታት ረፍት በኋላ ጎራውን ከተቀላቀለች ሦስት አራት ዓመቷን እያስቆጠረች ነው፡፡
በዚህ ዙሪያ እጅግ አሳዛኙ ነገር በፖለቲከኞች መተጋገል ውስጥ የሚፈሰው የንጹሐን ደም ነው፡፡ በሶማሊያው የእርስ በእርስ ጦርነት እልፍ ሰዎች አልቀዋል፡፡ ሱዳንም ለሁለት ስትከፈል በርካታ መቶሺህ ንጹሐን የሞት ጽዋን ተጎንጭተዋል፡፡ አሁንም በዚያው መንገድ ቀጥለውበታል፡፡ ኢትዮጵያችንም በደርጉ ዘመን የብዙ ሺሕ ንጹሐንን ሕይወት ስትቀማ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ደግሞ ከመቶ ሺሕ በላይ ልጆቿን አጥታለች፡፡ የአገራችን ብሂል የአሁኑ ይባስ እንደሚለው ባለፉት ሁለት ዓመታት ደግሞ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ልጆቿን በሰሜኑ ጦርነት ተቀምታለች፡፡ ችግሩ ግን በዚህ አላባራም፡፡ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ ዛሬም የሰሜኑ ሰንኮፍ እንዳለ ነው፡፡ የጦርነት ምንጭ የኾኑት ችግሮች አልተፈቱም፡፡ ምንም እንኳን መንግሥትና ህወሓት በእርቅ ጎዳና አብረው ቢፈሱም የትግራይ የአማራ እና የአፋር ክልል ግን እንደድሮው መኾን አልተቻላቸውም፡፡ ህወሓት ዛሬም ወልቃይትና ራያን በጦርነት ለመቀማት ወታደራዊ ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ይህን የሚያስረግጠው ደግሞ እንደአንዳንድ ምንጮች ገለጻ ሰሞኑን የህወሓት ታጣቂዎች ከወትሮው የተለየ እንቅስቃሴ እያደረጉ መታየታቸው ነው። ታጣቂዎቹ ትግራይንና ወልቃይት ጠገዴን ወደ ሚያዋስነው የተከዜ ወንዝ ተጠግተው መስፈራቸው ብቻ ሳይኾን የተለየ ዝግጅት እያደረጉ መኾናቸውም ሌላው ስጋት ነው፡፡ ከዚህ ከፍ ሲልም በዚሁ በህወሓት ቤትም የእርስ በእርስ ፍልሚያ እንደማይጠፋ አንዳንድ ማሳያዎች አሉ፡፡ ከዚህ አኳያ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት የኾኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ሰሞኑን በመቀሌ ከህወሓት አመራር ጋር በነበራቸው ስብሰባ ከባድ ተቋውሞ ደርሶባቸዋል። ከተሳታፊዎች መሐልም “አንተ አትወክለንም፤ ተላላኪ ነህ መሪዎቻችን ይመለሱልን” የሚሉ ንግግሮች ተስተናግደውበት እንደነበር ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው የክልሉ ፖለቲካ ለአጎራባች ክልሎች ብቻ ሳይኾን ለራሱ ለክልሉም ያልተገለጠ የቀውስ እሳት መኾኑን ነው፡፡
በሌላ በኩል ከሰኔ 2011 ዓ.ም ጀምሮ የባለሥልጣናት ግድያ የተጠናወተው የአማራ ክልል አሁን ላይ ሌላው የሰሜን ኢትዮጵያ የጦርነት አውድማ ወደመኾን የመጣ ይመስላል፡፡ ያለፉትን አራት ዓመታት ክልሉ ከሌሎች ክልሎች በተለየ መልኩ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የሚገደሉበት ክልል ኾኗል፡፡ መንግሥትም ገዳዮችን አጣርቶ ለፍርድ ከማቅረብ ይልቅ አድበስብሶ ማስቀረትና ከአንዱ ወደ አንዱ በማላከክ ጉዳዩን ሲያልፈው ይስተዋላል፡፡ በክልሉ ከሳምንት በፊት የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር የኾኑት አቶ ግርማ የሺጥላ መገደልን ተከትሎ የፌደራል መንግሥት ወንጀለኛውን ኃይል አጣርቶ ከማቅረብ ይልቅ በክልሉ ሁሉም አካባቢ ላይ “ሕግ ማስከበር” በሚል ዘመቻ ጀምሮ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ከዚህ ባለፈም የፌደራል መንግሥት “ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል ለማፍረስ ሲንቀሳቀሱ ነበር” በሚል በርካቶችን የእሥር ቤት ሲሳይ አድርጓቸዋል፡፡ ብዙዎችንም የእሥር ማዘዣ አውጥቶባቸው አሰሳውን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ይህ የእሥር ማዘዣ ከወጣባቸው አካላት ውስጥ ከፊሎቹ ከሀገር ውጪ በመኾናቸው በመንግሥትና በተከሳሾች መካከል ድንጋይ ውርዋሮው ተካሮ ሰንብቷል፡፡ ከዚህ አንጻር ዋነኞቹ ተከሳሾች ኾነው የቀረቡት በርካታ የሚዲያ ባለሙያዎችና ጥቂት ፖለቲከኞች መኾናቸውን የክስ መዝገባቸው ያስረዳል፡፡ በተለይ ከጋዜጠኞቹ እሥር ጋር በተያያዘ በአማራ ክልል ተነስቶ የነበረውን ውጥረት ተከትሎ ለእስር የተዳረጉ ሰባት ጋዜጠኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ ሲል አምኒስቲ ኢንተርናሽል ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ አሳስቧል።
በእርግጥ አሁን ላይ ታሳሪዎቹ በዕጥፍ የጨመሩ ቢኾኑም አምኒስቲ ባለው መረጃ ላይ ተንተርሶ እስሩን የፈጸመው የሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋዜጠኞቹ በፍጥነት እንዲፈታ እና የቀረበባቸውን ክስ እንዲያነሳ ጠይቋል፡፡ አምነስቲ ይህን መግለጫ ካወጣ በኋላም አፈናው ተጠንክሮ ቀጥሎ መንግሥት በሽብር ከሰስኳቸው ካላቸው ጋዜጠኞች ውስጥ አንዱ የኾነው ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ሰሞነኛው ታሳሪ ኾኗል፡፡ የጋዜጠኛውን እስር በተመለከተ መንግሥት “ከጅቡቲ በኢንተር ፖል አማካኝነት በቁጥጥር ሥር አዋልኩት” ቢልም ኢንተር ፖል ደግሞ በበኩሉ በጋዜጠኛው መያዝ ላይ እጁ እንደሌለበት ባወጣው መግለጫ አረጋግጧል፡፡
የኾኖ ኾኖ ሰሞነኛው የአማራ ክልል “ሕግ ማስከበር” ዘመቻ ለጊዜው ጋብ ያለ ቢመስልም በደቡቡ የሀገራችን ክፍል ግን ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ ከሳምንት በፊት ድርድር ላይ የሰነበቱት የኦሮሞ ታጣቂ ኃይሎች ወይም በተለምዷዊ አጠራሩ ኦነግ ሸኔና የፌደራል መንግሥት ዳግም ወደጦርነት መግባታቸው እየተነገረ ይገኛል፡፡ በዚህም ምንም እንኳን ከመንግሥት በኩል የተባለ ነገር ባይኖርም እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ኦነግ ሸኔ ከሚያዚያ 30 ቀን 2015 ዓ.ም ማለዳ ጀምሮ በመንግሥት ጦር አዲስ ጥቃት ተከፍቶብኛል ሲል በቃል አቀባዩ በኩል አስታውቋል። የቡድኑ ቃል አቀባይ አቶ ኦዳ ተርቢ እንደገለጹት፤ የመንግሥት ጦር በምዕራብ ሸዋ ዞን ጀልዱ እና በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ በኩል ጥቃት ተከፍቶብናል ብለዋል።
በአጠቃላይ ሀገሪቱ አሁን ላይ በበርካታ ተፋላሚዎች ኃይሎች አጣብቂኝ ውስጥ ትገኛለች፡፡ በሰሜንም ይሁን በደቡብ በምሥራቅም ይሁን በምዕራብ በሀገሪቱ ማዕቀፈ ካርታ ውስጥ ሰላም የሰፈነበትና የተረጋጋ ሕይወትን መምራት ከባድ እየኾነ መጥቷል፡፡ ሁኔታውን ከባድ ያደረገው ደግሞ ለጥቂት ዓመታትም ቢኾን (በዘመነ ኢህአዴግ) ጋብ ብሎ የነበረው የጠብመንጃ ፖለቲካ ዳግም ወደ አደባባይ በመምጣቱ ነው፡፡ ያለ ጠብመንጃ ሥልጣን ላይ የወጣው የብልጽግና መንግሥትም ለዚህ ችግር ትልቁ ምንጭ እንደኾነ በብዙዎች ይታማል፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ካለው ሰላም ማጣት ጋር ተያይዞ የፌደራል መንግሥት በለውጡ ወቅት በአካባቢው ከነትጥቃቸው የገቡ ኃይሎችን አይቶ እንዳላየ ማለፉ ዛሬ ላይ ሀገር ዋጋ አስከፍሏል፡፡ መንግሥት መልስ የሚያሻቸው የሕዝብ ጉዳዮችን ከማስተናገድ ይልቅ በሌሎች ጉዳዮች በመጠመዱ ችግሮች ችግሮችን እየወለዱ ሁሉም የሀገሪቱ ሕዝብ ወኪል የኾነው የልሂቃኑ ክንፍ የተወሳሰቡና የአንዱ ጥያቄ ከሌላው ጋር በማይጣጣም መልኩ ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎችን አንግቦ ለመፋጠጥ የተገደደ ይመስላል፡፡ አሁን ላይ ከሁሉም ብሔር የወጣው የኢትዮጵያ ልሂቅ ከልማት ጥያቄዎቹ ውጭ የሚያመሳስል የፖለቲካ ጥያቄ ያለው አይመስልም፡፡ ይህን ሂደት ደግሞ በሰላም ከመፍታት ይልቅ በነውጥና በጠመንጃ ለመፍታት መሞከር አሁነኛ ሁናቴ ኾኗል፡፡
