‹‹ያለ እውቀት በሚነገር ቃል፤ በጎውን ሥራ/ምክር የሚያጨልም ይህ ማነው?!››

Date:

ስለመቄዶንያው ብንያም በለጠ፡- ያየነውን እንመስክራለን፤ የሰማነውን እንናገራለን!!

ሰሞኑን በማኅበራዊ ትስስር መድረክ የመቄዶንያው መስራች ብንያም በለጠን በተመለከተ ምክርና ወቀሳ አዘል የሆኑ ጽሑፎች ሲዘዋወሩ ነበር፡፡ የጽሑፎቹ ሐሳብ ከታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ፤ ከመጽሐፈ ኢዮብ አንድ ኃይለ-ቃልን አስታወሰኝ፡፡ ቃሉ እንዲህ ይላል፤

‹‹ያለ እውቀት በሚነገር ቃል፤ በጎውን ሥራ የሚያጨልም ይህ ማነው?!››

ከዚሁ የሐሳብ ሰበዝ ሳልወጣ በመቄዶንያ የአረጋውያንና የአእምሮ ሕሙማን ማእከል በነበረኝ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ቆይታዬ የታዘብኩትን የግሌን ምስክርነት በጥቂቱ ላንሳ፡፡

ብንያምን የማውቀው ከዓመታት በፊት ኮተቤ በወላጆቹ ቤት 100 የሚሆኑ አረጋውያንና አእምሮ ሕሙማንን ሰብስቦ ሲረዳ ነው፡፡ በወቅቱ ማእከሉ ሙሉ በሙሉ ሥራውን ሲያካሂድ የነበረው በበጎ ፈቃደኛ አገልጋዮች ነበር፡፡ እናም አንድ ወቅት ላይ ከአንድ መነኩሴ አባት ጋር በመሆን በበጎ ፈቃደኝነት መቄዶንያን ለማገልግል አብረን ሄድን፡፡

ብንያም በትሕትና ከተቀበለን በኋላ የመጣንበትን ምክንያታችንን ገለጽንለት፡፡ ትሑት በሆነ መንፈስ ምስጋናውን ከገለጸልን በኋላ ፈቃዳችን ቢሆን ለተወሰኑ ጊዜያት እዛው ማእከሉ ውስጥ ከአረጋውያንና ከአእምሮ ሕሙማን ወገኖቻችን ጋር እየኖረን እንድናገለግል ጠየቀን፡፡ እኔም በዕድሜ አረጋዊ የሆኑትም መነኩሴ አባት በሐሳቡ ተስማማን፡፡

ብንያም ፈቃደኝነታችንን በአክብሮትና በምስጋና ከተቀበለ በኋላ በወላጆቹ ቪላ ቤት ውስጥ የአባቱና የእናቱን መኝታ ቤት ለጊዜው ማረፊያ ይሆነን ዘንድ ለእኔና ለመነኩሴው አባት እንዲሰጠን አደረገ፡፡ ልብ በሉ ብንያም ይህን ያማረውን የወላጆቹን መኝታ ቤት እኛ እንዳናርፍበት ሲሰጠን የእርሱ ማረፊያ ክፍል ግን በግቢው ውስጥ በጭቃ በተሠራ ሰርቪስ ቤት ውስጥ ነበር፡፡

ይህ ብቻ አይደለም በቆይታዬ እንደታዘብኩት፤ ብንያም አረጋውያኑ የበሉትን ይበላል፤ የለበሱትን ይለብሳል፤ አብሮአቸው ይውላል፤ አብሮአቸው ያድራል፡፡ እንደውም በማእከሉ ውስጥ ከእርሱ ይልቅ ልዩ እንክብካቤ የሚደረግላቸው አረጋውያን አባቶችና እናቶች ነበሩ፡፡

ይህን ገና ከጅምሩ የመቄዶንያ ቀኝ እጅ የሆነውና ሠርጉን ጭምር በመቄዶንያ ያደረገው ሰይፉ ፋንታሁን፤ አብረውት ይሠሩ የነበሩት ታዬ ወርቁ፣ ጋዜጠኛ ዕፀገነት/የኢቢኤሷ፣ የስፖርት ጋዜጠኛው ታደለ… ከተባበሩት መንግሥታት የምግብ ድ/ት ከጡረታ ከተገለሉ በኋላ የማእከሉ በጎ ፈቃደኛ የነበሩት ዶ/ር ጌታቸው ተድላ… በወቅቱ በማእከሉ አብረውን የነበሩ ሌሎች በጎ ፈቃደኞችና ማእከሉን ለመጎብኘት የሚመጡ ወገኖች ሁሉ የሚያውቁት፤ የሚመሰክሩት እውነታ ነው፡፡

በመጨረሻም፤

መቄዶንያ የሰዎች እንጂ የመላእክት ስብስብ ያለበት ቦታ አይለደም፡፡ እግር ጥሎት ለሄደም ሆነ በማእከሉ በቅርበት ለሚከታተል ሰው ሊታዘባቸው የሚችላቸው ጥቃቅንም ሆነ ጉልህ ችግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ የማእከሉ ዋና ግብ ግን የቀኑ ጸሐይ፣ የሌሊቱ ቁር የሚፈራረቅባቸውን አረጋውያን አባቶችና እናቶች ከጎዳና ላይ በማንሳት በቀሪ ጥቂት ዘመናቸውን እፎይ ብለው የሚያርፉበት መጠለያ፣ ምግብ፣ አልባሳትና ቤተሰባዊ እንክብካቤ ማሟላት ነው፡፡ ይህን ደግሞ መቄዶንያ ደጋግ ልብ ካላቸው ኢትዮጵያውያን ወገኖች ጋር በመሆን በስፋት እየሠራ ነው፡፡

ተቺዎቹ፤ ‹‹ብንያም አለባበሱን እንዲቀይር ከመምከርም ባሻገር ምስኪን መስሎ መታየት ምንድ ነው? ነቃ ነቃ በል እንጂ…›› በሚል ላነሱት አስተያየት ይህን ብዬ ጽሑፌን ልቋጭ፡፡

ህንዳውያን ‹‹ታላቁ ነፍስ›› በማለት የሚጠሯቸው የህንድ የነጻት አባት ማሕተመ ጋንዲ በሕይወት ዘመናቸው ልብሳቸው አንድና ተመሳሳይ ነበር፡፡ እኚህ ሰው ከህንዳውያኑ ተራ ዜጎች የተለየ አለባበስና አመጋገብ አልነበራቸውም፡፡ እርሳቸውን ለማግኘት/ለመጎብኘት ለሚመጡት ለታላላቅ የዓለማችን መሪዎች ሆነ ለምድራችን ምስኪኖችንና ጎስቋሎች የነበራቸው አቀባባል፤ የሚያሳዩት ክብር፣ የሚሰጡት ፍቅርና ትሕትና ተመሳሳይ ነበር፡፡

ጋንዲ በአለባበሳቸውም ሆነ በአኗኗራቸው ይህን ተራ መንገድ የተከተሉት ወደውና ፈቅደው እንጂ ገንዘብ ስለቸገራቸው አይደለም፡፡ እኚያ ታላቅ ሰው ባላቸው ተቀባይነት፣ ክብርና ዝና የተነሳ ወርቅ መልበስ፣ በወርቅ ሰሀን መብላት የሚያስችል ዕድል የነበራቸው ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡ ግን እርሳቸው ያን መንገድ አልፈለጉትም፡፡ ተራ መስለው ግን ደግሞ ታላቅ ሥራን ሠርተው ያለፉ የምድራችን ታላቅ ሰው ናቸው፡፡

እንደ መውጫ፤

መቄዶንያን/ብንያምን በተመለከተ ችግር አለ ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ የሚሏቸውን ችግሮች ለመቅረፍ ተባብሮ መስራት እንጂ ከውጪ ሆነ መተቸት ለውጥ ያመጣል ብዬ አላስብም፡

ታላቁ ቅዱስ መጽሐፍ፤ ‹‹ነገር ግን በጎ ሥራ ለሚያደርጉ ሁሉ ምስጋናና ክብር፤ ሰላምም ይሆንላቸዋል፤›› እንዲል፤ ወንድማችን ብንያም ስላደረገኸውና እያደረግኽ ስላለው የበጎነት ሥራ ከፈጣሪ ዘንድ ምስጋናና ክብር፤ የበዛ ሰላም ይሁንልህ!!  

ሰውን ለመርዳት ሰው መሆን በቂ ነው!!

በዲ/ን ተረፈ ወርቁ፤

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በከተማዋ ከ24 ሺህ በላይ ንቁ የግንባታ ፈቃድ ያላቸው ሳይቶች መኖራቸው ተገለፀ

በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚደርሰውን የህይወትና የንብረት ጉዳት ለመቀነስ የቁጥጥርና የግንዛቤ...

አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ለሕክምና በወሰደችው መድኃኒት ምክንያት ከውድድር ታገደች

የቀድሞዋ የሁለት ጊዜ የዓለየቀድሞዋፒዮኗ ኢትዮጵያዊቷ ጉዳፍ ፀጋይ ከውድድር በፊት...

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እውቅና ሊሰጣቸው ነዉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እውቅና የሚያገኙት የጎርጎርጎረሳዉያኑ 2026 በሞሮኮ...