የጃፓን መንግሥትና የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) በሰኔ ወር 2018 ዓ.ም. ለሚካሄደው 7ኛው የኢትዮጵያ አገራዊ ምርጫ የሚውል የ3 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፍ ስምምነት በአዲስ አበባ ተፈራርመዋል።
ይህ ስምምነት “የኢትዮጵያን ምርጫ ለዲሞክራሲያዊ ዘላቂነት ማጠናከር” (SEEDS II) የተሰኘውንና በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚተገበረውን ፕሮጀክት በገንዘብ ለማገዝ የሚያስችል ሲሆን፣ ዋና ዓላማውም የምርጫውን ተአማኒነት፣ አሳታፊነትና ሰላማዊነት ማረጋገጥ እንደሆነ ተገልጿል።
በምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት በተካሄደው የፊርማ ሥነ-ሥርዓት ላይ እንደተገለጸው፣ የጃፓን መንግሥት ድጋፍ ቦርዱ በብሔራዊና በንዑስ ብሔራዊ ደረጃ ያለውን የአፈጻጸም አቅም ለማሳደግ ይውላል። ከዚህም በተጨማሪ ለሴቶች፣ ለወጣቶችና ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጠውን የመራጮች ትምህርት ለማስፋፋትና የምርጫ ሂደቱን በዲጂታል ቴክኖሎጂ በማዘመን ግጭቶችን ለመከላከል ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል።
በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ክቡር ሺባታ ሂሮኖሪ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፣ ጃፓን በኢትዮጵያ ግልጽ፣ አሳታፊና ሰላማዊ ምርጫ እንዲካሄድ ፍላጎቷ መሆኑን ገልጸው፣ መንግሥታቸው ሂደቱን በቅርበት እንደሚከታተልና ድጋፉን እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ የተደረገው ድጋፍ ለ7ኛው አገራዊ ምርጫ ዝግጅት ብቻ ሳይሆን ለተቋሙ ዘላቂ ሙያዊ ብቃትና ተቋማዊ ጥንካሬ ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ ምስጋናውን አቅርቧል።
የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ተወካይ ሳሙኤል ዶ በበኩላቸው፣ የጃፓን ድጋፍ በምርጫ ሂደት ውስጥ ተጠያቂነትንና ግልጽነትን ለማስፈን ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል። የSEEDS II ፕሮጀክት ከምርጫው በፊት፣ በምርጫው ወቅትና ከምርጫው በኋላ ያሉትን ሂደቶች በሙሉ የሚያካትት በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ምርጫ በሀገር በቀል ዕውቀትና አመራር እንዲመራ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር በስምምነቱ ወቅት ተመልክቷል።
