ጋዜጠኞች የተሟላ የሕግ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ኢሰመኮ አሳሰበ

Date:

ሀሳብን በነጻነት መግለጽ መሠረታዊ እና በዘፈቀደ ገደብ የማይደረግበት ሰብአዊ መብት በመሆኑ እና ጋዜጠኞች የኅብረተሰቡን መረጃ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ በመሆናቸው “ጋዜጠኞች የተሟላ የሕግ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል” ሲል የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አሳሰበ። ጋዜጠኞች በበኩላቸው የሀገር እና የሕዝብ ደኅንነትን ከመጠበቅ አኳያ የተቀመጡ ግዴታዎችን በማክበር እንዲንቀሳቀሱ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።

ኮሚሽኑ ከኢንተርናሽናል ሚዲያ ሰፖርት ጋር በመተባበር በጋዜጠኞች የሕግ ጥበቃ (ከለላ) ላይ ጥቅምት 04 ቀን 2018 ዓ.ም በአርባ ምንጭ ከተማ ባካሄደው ውይይት የሲቪል፣ ፖለቲካ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር አብዲ ጅብሪል ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ዋናው ምሰሶ መረጃ የማግኘት መብት መሆኑን አመላክተዋል።

የመብቱ መጠበቅ መረጃን ተደራሽ ከማድረግ በተጨማሪ በኅብረተሰቡ ውስጥ የሚሰራጩ ሐሰተኛ መረጃዎችን ለማረም የሚያግዝ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

ከዚህ አኳያ “ጋዜጠኞች የኅብረተሰቡን መረጃ የማግኘት መብት ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ በመሆናቸው የተሟላ የሕግ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ከማእከላዊ ኢትዮጵያ፣ ከሲዳማ እና ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የሕግ አስፈጻሚ አካላት እና ከግልና ከመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት የተውጣጡ ባለሙያዎች በተሳተፉበት የአርባ ምንጩ ውይይት በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶች ላይ ውይይት ተደርጓል።

የጥላቻ ንግግርን እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን እንዲሁም የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጡ አዋጆችን ሽፋን በማድረግ የሚፈጸሙ ክልከላዎች እና ገደቦች፣ የመገናኛ ብዙኃን አባላት ስለመብታቸውና ግዴታቸው ያላቸው ግንዛቤ ማነስ እንዲሁም የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ለተወሰኑ የመገናኛ ብዙኃን ብቻ መረጃ የመስጠት አዝማሚያ በተለይም የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ኃላፊዎች ለግል መገናኛ ብዙኃን መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆን በዘርፉ የታዩ ክፍተቶች ሆነው ተነስተዋል።

የጥላቻ ንግግሮችን፣ ሐሰተኛ መረጃዎችን እንዲሁም ግጭት የሚቀሰቅሱ መልእክቶችን የሚያሰራጩ መገናኛ ብዙኃንን መቆጣጠር አለመቻሉ፣ በበይነ መረብ ላይ የሚጣሉ ገደቦች እና በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ተፈጽሟል በተባለ ወንጀል ጋዜጠኞች ከሕግ ውጭ እስራት የሚፈጸምባቸው መሆኑም በዘርፉ ከሚስተዋሉ ድክመቶች መካከል ተጠቅሰዋል።

በዞን እና በወረዳ ደረጃ በሚንቀሳቀሱና ሕግ ተላልፈዋል በሚል በሚጠረጠሩ ጋዜጠኞች እና የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ላይ የሚደረጉ ምርመራዎች መዘግየት፣ የመርማሪ ፖሊሶች ዐቅም ማነስ እንዲሁም መብቱን በተመለከተ በቂ ግንዛቤ አለመኖር በዘርፉ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች መሆናቸው በውይይቱ ተመላክቷል።

ችግሮችን ለመፍታት በክልል ደረጃ ስልጠና እና የዐቅም ግንባታ ሥራዎችን ማከናወን አስፈላጊ መሆኑንም ኮሚሽኑ ጠቁሟል።

በሌላ በኩል ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ከግዴታዎችና ኃላፊነቶች ጋር የሚመጣ መሆኑን በመገንዘብ ጋዜጠኞችም የሀገር እና የሕዝብ ደኅንነትን ከመጠበቅ አኳያ የተቀመጡ ግዴታዎችን በማክበር እንዲንቀሳቀሱ ኮሚሽኑ ጥሪ አቅርቧል።

(አዲስ_ማለዳ)

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በመንገድ የትራፊክ አደጋ የ6 ሰዎች ህይወት አለፈ

አደጋው የደረሰው ነሐሴ 18 ቀን 2018 ዓ/ም ከጠዋቱ...

ከ12ኛ ክፍል ተፈታኞች  565 ትምህርት ቤቶች አንድም ተማሪ አላሳለፉም

በዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና በተመዘገበው ውጤት...

የአማርኛ ቋንቋ እውነተኛ ምንጭ ቤተ መንግሥት ሳይሆን ሕዝብና ሠራዊት ነው

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአማርኛ ቋንቋ ማበልጸጊያ ተቋም አዘጋጅነት ከስድስት...