የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ በጋዛ ያለው ጦርነት እንዲቆም በዕንባ ተማፀኑ።
ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም ትናንት ሐሙስ የዓለም ጤና ድርጅት ዓመታዊ ጉባኤ ላይ በተደረገ ስብሰባ፣ ጦርነት ዘላቂ መፍትሄ አያመጣም፤ እስራኤልንም ይጎዳታል ብለዋል።
በአሁኑ ጊዜ በጋዛ ውስጥ ያሉ ሰዎች ምን እንደሚሰማቸው ይሰማኛል ያሉት ዶክተር ቴዎድሮስ፤ የጦርነትን አውዳሚነትና አስከፊነት አብራርተዋል። ምግብና የህክምና ቁሳቁስን እንደ ጦር መሣሪያ መጠቀም ልክ አይደለም ብለዋል።
መግባባት እንዲመጣ እጠይቃለሁ ያሉት ኃላፊው፤ ሰላም መውረዱ ለእስራኤልም ሆነ ለፍልስጤማውያን ጥሩ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት የድንገተኛ አደጋ ዳይሬክተር ማይክል ራያን በበኩላቸው፤ በጋዛ ውስጥ 2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሰዎች “በሞት አደጋ ላይ ናቸው” ብለዋል።
ረሀብን ማቆም አለብን ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የጤና ስርዓቱን ወደ ትክክለኛ ሁኔታው መመለስ ይገባል ሲሉም አክለዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት በጋዛ የሚገኙ ፍልስጤማውያን የምግብ፣ የውሃ፣ የህክምና አቅርቦቶች፣ የነዳጅና የመጠለያ እጦት እየተሰቃዩ ነው ብሏል።
በጋዛ ከሚገኙት 36 ሆስፒታሎች 19ኙ ብቻ ስራቸውን የቀጠሉ ሲሆን፤ ሰራተኞቻቸው “በማይቻል ሁኔታ” ውስጥ እየሰሩ መሆናቸውን የተባበሩት መንግስታት የጤና ኤጀንሲ በመግለጫው ተናግሯል ሲል ፍራንስ 24 ዘግቧል።
(ጋዜጣ+)
