በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ታጣቂዎች ህጻናትና ሴቶችን ጨምሮ በርካታ ንጹሃንን ገድለዋል።
የንጹሃን ግድያ ተደጋግሞ በተሰማበት በምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ ሃሎዲንቂ ቀበሌ እሁድ ምሽት በግምት ሁለት ሰዓት ግድም የታጠቁ አካላት ባደረሱት ጥቃት ከ20 በላይ ሰዎች ወዲያው መገደላቸውን ተጎጂዎች እና የአከባቢው ነዋሪዎች ለዶቼ ቨለ ተናግረዋል፡፡
ነዋሪዎቹ ምን አሉ ?
” ጥቃቱ እሁድ ምሽት ነው የተፈጸመው።
አገር ሰላም ብለው እንደወትሮው ወደ ቤታቸው በገቡ ንጹሃን የኖኖ ወረዳ ሃሎዲንቂ ቀበሌ ነዋሪዎች ላይ ነው የተፈጸመው።
በአጎራባች የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ጉራጌ ዞን ወረዳዎች የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ወሰን ተሻግረው ነው ጥቃቱን ያደረሱት።
ምንም ያልታጠቁ ሰላማዊ ዜጎች ላይ ዘግናኝ ግድያ ነው የተፈጸመው። ጥቃቱን ያደረሱት ደግሞ በአከባቢው የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ የተባሉ ታጣቂዎች ናቸው።
በእሁድ ምሽቱ ድንገተኛ ጥቃት 22 ሰዎች ወዲያው ተገድለዋል።
ዳርጌ በሚባል ስፍራ ምሽት ከአንድ እስከ ሁለት ሰዓት ግድም በተወሰደው በዚህ ጥቃት ህጻናት እና ሴቶች በስፋት ተጠቂ ሆነዋል። ” ብለዋል።
ቤተሰቦቻቸው የጥቃቱ ሰለባ የሆኑባቸውና ለደህንነታቸው ስማቸውን መናገር ያልፈለጉ አንድ ነዋሪ ” ሰላማዊ ዜጎችን በጭለማ ገብተው ነው የፈጁዋቸው፡፡ አሁን በእሁድ ምሽቱ በዚህ ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 29 ደርሰዋል ” ሲሉ ተናግረዋል።
” 22 ሰዎች ወዲያው መገደላቸው ሲረጋገጥ ቀሪዎቹ አስከሬናቸው በየጥሻው የወደቁና በሆስፒታል ህይወታቸው ያለፉ ናቸው ” ብለዋል፡፡
ነዋሪዎቹ የተገደሉትን ለመለየት ሰኞ እስከ ምሽት የአስከሬን አሰሳ በአከባቢው ሲደረግ እንደነበር ጠቁመዋል።
ከሟቾች አባወራ የሆኑ ትልልቅ ሰዎች ከስድስት የማያልፉ ሲሆን ቀሪዎቹ ህጻናት እና አብዛኛው ደግሞ ታዳጊ ተማሪዎች እና ሴቶች ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
የኖኖ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ወንዳፍራሽ ሉሌሳ ፥ ” የተገደሉት 22 ናቸው የሚባለው ውሸት ነው። 12 ናቸው የተገደሉት። ከ22 በላይ የተገደሉት ከታጣቂዎቹ ወገን ነው ” ብለዋል።
ጥቃቱ ከተፈጸመ በኋላ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በአካባቢው ተሰማርተው እርምጃ መውሰዳቸውን ገልጸዋል።
በዚህ ወረዳ ተመሳሳይ ጥቃት ለምን ተደጋገመ ?
ነዋሪዎች እንደሚሉት በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን አጎራባች በሆነው የጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ ውስጥ ወታደራዊ ስልጠና የሚወስዱ ታጣቂዎች አሉ።
እኚህ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ እየገቡ ህጻናትን ጨምሮ ያገኙትን በምንም ፖለቲካ ውስጥ የሌሉ ሰላማዊ ሰዎችን እያጠቁ ይመለሳሉ፡፡
” እነዚህ ሟቾች ምንም ውስጥ የሌሉና ምንም ጥፋት የሌለባቸው ናቸው ” የሚሉት ነዋሪዎቹ ፥ ጥላቻ እና ማንነት ላይ የሚያተኩር ጥቃት እንደሆነ ገልጸዋል።
ይህ ካልሆነ ከሶስት ዓመት እስከ 14 ዓመት እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ህጻናት ምን ውስጥ ይሆናሉ ተብሎ ይታሰባል ? ሲሉ ጠይቀዋል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች የሚንቀሳቀሱ ጥቃት አድራሾቹ በምዕራብ ሸዋ ዞን ኖኖ ወረዳ በተለያዩ ጊዜያት በተፈጠረ ግጭት ቤተሰቦቻቸውን ይዘው የተፈናቀሉም እንደሚገኙባቸው ገልጸዋል፡፡
” ወደ ጉራጌ ዞን የሄዱት ሰዎች የኦሮሞ ነጻነት ጦር የሚፈጽመውን ጥቃት እንዲሁም በአካባቢው አስተዳደር ከመሬት ይዞታ ጋር በተያያዘ በወጣ አዲስ አሠራር ምክንያት ነው ” ሲሉ ነዋሪዎች አመልክተዋል።
” አሁን ላይ ጥቃት ከሚያደርሱ ታጣቂዎቹ አብዛኞቹ በ2016 ዓ.ም. በአንድ ሰርግ ላይ ቦምብ ተጥሎ 36 ሰዎች ግድም መገደላቸውን ተከትሎ ከአከባቢው የተፈናቀሉ ናቸው ” ብለዋል።
ሰኔ ወር 2016 ዓ.ም. በዚሁ ኖኖ ወረዳ ቆንዳላ ቀበሌ በአንድ ሰርግ ቤት ላይ ቦምብ ተጥሎ ሙሽሮችን ጨምሮ 36 ሰዎች ከተገደሉ በኋላ ተደጋጋሚ የንጹሃን ጥቃቶች እና የግድያ ዜናዎች ከዚህ አከባቢ ተለይቶ አያውቅም፡፡
በቅርቡ 2017 ዓ.ም. ሰኔ ወር ላይ ዳግም በንጹሃን ላይ ባነጣጠረው የዚሁ አከባቢ ጥቃት ከአንድ ቤት የተገደሉ ስድስት የቤተሰብ አባላትን ጨምሮ 14 ሰላማዊ ነዋሪዎች አልቀዋል።
የጸጥታ ስጋቱ በተደጋገመበት የኖኖ ወረዳ አዋሳኝ ቀበሌያት አከባቢ የነዋሪዎቹ ስጋት ከጊዜ ወደ ጊዜ ዘላቂ እልባት ከማግኘት ይልቅ እያደር እየከፋና እየተባባሰ መምጣቱን የአከባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
የኖኖ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ወንድአፍራሽ ሉሌሳ ጥቃት የሚያደርሱት ወገኖች ፤ የመንግሥት የፀጥታ አካላት የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ላይ ሲዘምት በሚያገኙት አጋጣሚ ጥቃት እንደሚፈጽም ይናግራሉ።
” ዓላማቸው በሕገ ወጥ መንገድ ሰፍረው መሬት በመውረር ግብር የማይከፍሉበት መሬት ማግኘት ነው። ‘ ከመሬቱ ተፈናቅለናል አሁን መመለስ አለብን ‘ በሚል ነው ጥቃት የፈጸሙት። ይህ ግን ሕልም ነው ” ብለዋል።
ይህ መረጃ ባለቤትነቱ የዶቼ ቨለ ሬድዮ ጣቢያ እና ቢቢሲ አማርኛ ነው።
