ጤና ቢሮው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ ቁጥር 94/2019 ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ የተሰጠ ሥልጣንና ተግባር መሰረት ቀደም ሲል በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን አገልግሎት ሲሰጡ የነበሩት አራት ተግባራት ወደ ቢሮው መካተታቸውን በዛሬው እለት ተገልጻል፡፡
በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በዋናነት ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ ምግብ መድኃኒት ባለስልጣን ይሰጡ የነበሩት የጤና ባለሙያዎች የሙያ ፍቃድ ፤ የጤና ተቋት ብቃት ማረጋገጥ አገልግሎት እና የጤና ባለሙያዎች ሥነ-ምግባር እና የህክምና ስህተት የሚመረምር እና ውሳኔ የመስጠት አገልግሎት ከባለስልጣኑ ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ መተላለፋቸውን ገልፀዋል።
ከዚህ ቀደም ይሰጥ የነበረውን አገልግሎት በተሻሻለ ሁኔታ ለመስጠት እና ውጤታማ የቁጥጥርና ክትትል ስራን ለመስራት ተግባራዊ መደረጉን ተናግረዋል ።
የጤና ባለሙያዎች አዲስ ፈቃድ ማውጣትና ነባር ፈቃዳቸውን ማሳደስ በቴክኖሎጂ በታገዘ ሥርዓት እንዲከናወነ መሆኑን አብራርተዋል ።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምግብ መድሃኒት ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ትዕግሥት በዳዳ ከጥቅምት 18 2019 ጀምሮ አገልግሎቱ በጤና ቢሮ የሚጀምር መሆኑን ገልፀዋል ።
ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ምግብ መድሃኒት ባለስልጣን ይሰጡ የነበሩ የምግብ እና ጤና ነክ ጉዳይ ማረጋገጥ ፣ የጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ቁጥጥር እና ድህረ ገበያ ቅኝት ጨምሮ ሌሎችም በቀደመው አሰራር የሚቀጥሉ መሆኑን አስታውቀዋል ።
ሁለቱ ተቋማት በጋራ ሲሠሩ መቆየታቸውንና በቀጣይም ትብብራቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል ።
