የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) በአማራ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች በሚካሄዱ የትጥቅ ግጭቶችና ጥቃቶች ምክንያት የንጹሃን ዜጎች “በሕይወት የመኖርና” እና የመንቀሳቀስ መብት “በከፍተኛ ደረጃ” እየተጣሰ ነው ያለ ሲሆን በአስቸኳይ የመፍትሔ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቀረበ።
በሀገሪቱ “ታጥቀው በሚንቀሳቀሱ አካላት” በተለያዩ አካባቢዎች በሚከሰቱ ግጭቶች በየጊዜው ንጹሃን ዜጎች ለሞት፣ ለአካል ጉዳት፣ እገታ፣ ንብረት ውድመት እና ለመፈናቀል እየተዳረጉ ነው ብሏል።
ጉባኤው፤ ታጣቂዎች ከሚያደርሱት ጥቃት በተጨማሪ በመኖሪያ ቤቶች ላይ በሚተኮሱ ከባድ መሳሪያዎች የንፁሃን ህይወት እየተቀጠፈ ነው ብሏል።
አክሎም፤ የክልል እና የፌደራል መንግስት ዓለም ዓቀፍ የሀገሪቱ ህገ መንግስት የሚደንግገውን ማንኛውም ሰው በህይወት የመኖር መብት የማስጠበቅ ግደታ እና ኃላፊነታቸው እየተወጡ እንዳልሆነ ጠቁሞ፣ የሰዎችን ሰላምና ደኀንነት የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስቧል።
ኢሰመጉ ለዚህ እንደማሳያ የጠቀሰው በአማራ ክልል በዋግኽምራ ብሔረሰብ ዞን ሰቆጣ ከተማ መስከረም 15 ቀን 2019ዓ.ም በነበረ የትጥቅ ግጭት በከባድ መሳሪያ ምክንያት ሁለት የሰዎች የአካል ጉዳት እና የአንድ ንፁሃን ህይወት ማለፉን ነው።
በተጨማሪም መስከረም 26 ቀን በሰሜን ጎንደር ዞን ዳባት ወረዳ በመንግስት የጸጥታ አካላት እና በአካባቢው ታጥቀው በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በነበረ የትጥቅ ግጭት በተተኮሱ ከባድ መሳሪያዎች እና ተባራሪ ጥይቶች የሦስት ሰዎች ሕይወት ማለፉን አስታውቋል።
በተጨማሪም በኤርትራ ስደተኞች ካምፕ አካባቢ በተተኮሰ ከባድ መሳሪያ በሦስት ስደተኞች ላይ የአካል ጉዳት ደርሶ በዳባት በጎንደር ሆስፒታል ህክምና ላይ ናቸው ብሏል። ይህ ድርጊት የዜጎችን እንቅስቃሴ መገደቡን አስታውቋል።
ኢሰመጉ በጋምቤላ ክልል ደግሞ በአቦል ወረዳ በህዝብ ማመላለሻ ላይ በተከፈተ ተኩስ፣ በጋምቤላ ከተማ 04 ቀበሌ አራት ሰዎች ህይወታቸው እንዳለፈ እና አዲስ ሰፈር አካባቢ በተፈጸሙ ጥቃቶች በርካታ ንጹሃን መገደላቸውንና መቁሰላቸውን ገልጿል።
የሟች ቤተሰቦች ቅሬታቸውን ለማቅረብ ወደ ጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በሚሄዱበት ወቅት የመንግስት የጸጥታ ኃይሎችን እና ታጣቂዎች በፈጠሩት ግጭት አንድ ሰው ላይ የአካል ጉዳት እና የንብረት ውድመት ተከስቷል ብሏል።
በኦሮሚያ ክልል በወለጋ እና ምስራቅ አርሲ ዞኖች ግጭቶች ተጠናክረው መቀጠላቸውን፣ በጊዳ አያና ወረዳ ከግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች ያለ መጠለያ እና እርዳታ በከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደሚገኙ አመልክቷል። በዚሁ ክልል በተለያዩ ቦታዎች ዜጎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው እንደተገደበ እና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እየተፈፀመ መሆኑን እና ማህበረሰቡም ከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደወደቀ አንስቷል።
የሰብዓዊ መብቶች ተሟገች ድርጅቱ፤ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ ደግሞ የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር አምቡላንስ አሽከርካሪ በመደበኛ ስራው ላይ በነበረበት ወቅት መገደሉን፤ በማንቡክ ወረዳ አሽከርካሪዎች እና በአካባቢው በስራ ላይ የነበሩ ሰዎች በታጣቂዎች ታግተው እንደተወሰዱ እና ቤተሰቦቻቸውም የገንዘብ ጥያቄ እንደቀረበባቸው አጋልጧል።
ኢሰመጉ የኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥትና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች የዜጎችን በሕይወት የመኖርና ደኀንነት የመጠበቅ ግዴታ የመንግሥት መሆኑን በማስታወስ፤ የፌደራልና የክልል መንግስታት ጥቃቶችን እንዲያስቆሙ፣ ወንጀለኞችን ለሕግ እንዲያቀርቡ እና ለተፈናቀሉ ዜጎች በአስቸኳይ የሰብዓዊ እርዳታ እንዲያደርሱ አሳስቧል።
