ሰኔ 16/2017 (አሐዱ ሬዲዮ) ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ የኮሌራ ወረርሽኝ ሰፋ ባለ ሁኔታ እንደተከሰተባቸው ከተገለጹ ክልሎች ውስጥ አንዱ የሆነው የጋምቤላ ክልል፤ በአሁኑ ወቅት ኮሌራ አሳሳቢ ወደማይሆንበት ደረጃ ማድረሱን ለአሐዱ አስታውቋል።
የኮሌራ ወረርሽኝ በክልሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተው በአኮቦ ወረዳ እና በአዋሳኝ አካባቢዎች እንደሆነ የገለጹት የክልሉ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኦጁሉ ጊሎ ናቸው።
በመሆኑም የክልሉ መንግሥትና ጤና ቢሮ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ሙሉ አቅማቸውን ወረርሽኙ በተከሰተበት ቦታ ላይ በማድረግ የቅድመ መከላከል ሥራ መሰራቱን ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት በአሁኑ ወቅት የኮሌራ ወረርሽኝ በእጅጉ መቀነሱንና አሳሳቢ አለመሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሀይሌ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ የኮሌራ ወረርሽኝን ለመከላከል ከተለያዩ አጋር አካላት ጋር በመሆን ዘርፈ ብዙ ሥራዎች መሰራታቸውን ለአሐዱ ተናግረዋል።
አስቀድሞ ለመከላከል ከተሰሩ ሥራዎች ውስጥም በጋምቤላ ክልል እስካሁን ባለው ጊዜ ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጋ የኮሌራ መከላከያ ክትባት መሰጠቱን አንስተዋል።
በተጨማሪም ተጋላጭነታቸው ከፍ የሚሉባቸው እና ተደራሽ ያልሆኑባቸው ቦታዎች ካሉ አሁንም ተጨማሪ ክትባት እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ከኮሌራ ውጪ በክልሉ ‘ሊያጋጥሙ ይችላሉ’ ተብለው የሚታሰቡ ተላላፊ በሽታዎችን ለመቆጣጠርና ለመከላከል እየተሰራ እንደሚገኝ የጋምቤላ ክልል የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ገልጸዋል።
በጋምቤላ ክልል ከየካቲት ወር 2017 ዓ.ም. ጀምሮ የኮሌራ በሽታ በወረርሽኝ ተከስቶ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ ወረርሽኑ በተከሰተባቸው ወረዳዎች 16 ጊዜያዊ የኮሌራ ማከሚያ ማዕከላት ተቋቁመው በሽታውን የመከላከል እና ክትባት የመስጠት ሥራ ሲሰራ መቆየቱ ተገልጿል፡፡
