ኢራን በእስራኤል ጥቃት የተገደሉባትን የጦር አዛዦች እና የኒውክሌር ሳይንቲስቶች የቀብር ስነ ስርዓት በዛሬው ዕለት ፈፅማለች።
በቴህራን አደባባይ የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናትና በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢራናዉያን በተገኙበትም ህይወታቸው ላለፉት የጦር አዛዦች እና የኒውክሌር ሳይንቲስቶች የሽኝት ስነ ስርዓት መከናወኑ ተገልጿል፡፡
ከወታደራዊ አዛዦች እና የኒውክሌር ሳይንቲስቶች በተጨማሪም 60 ለሚሆኑ ሰዎች መንግስታዊ የቀብር ስነ ስርዓት መፈፀሙን ቢቢሲ ዘግቧል።
በስነ ስርዓቱ ላይ ጥቁር ልብስ የለበሱ በርካታ ሰዎች መፈክሮችን በማሰማት የኢራንን ባንዲራ በማውለብለብ እና የተገደሉትን ሰዎች ምስል በማሳየት ሀዘናቸውን ሲገልፁ እንደነበርም ነው የተዘገበው።
ለ12 ቀናት ከዘለቀው የኢራን እና እስራኤል ጦርነት በኋላ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተከናነው የተኩስ አቁም ስምምነት አራተኛ ቀኑን አስቆጥሯል።
