ከዓለም ባንክ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ በተፈጥሮና ሰው ሰራሸ ምክንያቶች ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎችን ለመደገፍ እና መሠረታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን አቅም ለማሳደግ የሚያስችል (Response – Recovery – Resilience for Conflict Affected Communities in Ethiopia) የተሰኘ ፕሮጀክት፤ በ5 ክልሎች ላይ ተግባራዊ እየተደረገ እንደሚገኝ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ለአሐዱ አስታውቋል።
አጋር አካላትን በማስተባበር በአማራ፣ በትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ አፋር እና ቤኒሻንጉል ክልሎች በተለያዩ ግጭቶች ውድመት የተከሰተባቸው አካባቢዎች ላይ የተለያዩ ድጋፎችን በሰፊው ተደራሽ ለማድረግ ሲሰራ መቆየቱን፤ በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የሴቶች መብት ጥበቃና ምላሽ መሪ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ዘካሪያስ ደሳለኝ ገልጸዋል።
በዚህም በፕሮጀክት አማካኝነት በተለያዩ ግጭቶች ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች መልሶ የማቋቋምና የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራበት መሆኑን ተናግረዋል።
ችግሩ ሰፋ ያለ በመሆኑም እስከ ዞንና ወረዳ ድረስ በመሄድ የገቢ ማስገኛ ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ እና ራሳቸውን መቀየር በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ የተለያዩ የክህሎትና ሥነ-ልቦና ስልጠናዎች ሲሰጥ መቆየቱን አንስተዋል።
በዚህ ሂደትም ቢያንስ ከ30 ሺሕ በላይ ለሚሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች ስልጠናውን ተደራሽ ማድረግ መቻሉን መሪ ሥራ አስፈፃሚው ለአሐዱ ገልጸዋል።
የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ሴቶች በአንድ ላይ እርስ በእርስ የሚወያዩበትና ልምድ የሚለዋወጡበት አግባብ መፈጠሩንም አክለዋል።
ሕጻናቱንም መልሶ የማቋቋም ላይ እንደሚሰራ አንስተው፤ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ላይ ደግሞ የጤና፣ የሥነ-ልቦና እንዲሁም ሌሎች ዘርፈ ብዙ የድጋፍ አገልግሎቶች ይሰጣል ብለዋል።
በተጨማሪም ጊዜያዊ የመጠለያ ቦታዎችን በማዘጋጀት ለተወሰነ ጊዜ ቆይተው የሚወጡበትን መንገድ እንደሚመቻች ገልጸዋል።
ከዚህ ሌላ ደግሞ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ሁሉንም አይነት አገልግሎት በአንድ ቦታ ማግኘት የሚያስችላቸውን የአንድ ማዕከል አገልግሎት በክልሎች ላይ የማስፋፉት ሥራ መሰራቱን መሪ ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።
(አሐዱ ሬዲዮ)
