- የድራማው ቀጣይነት ከበዓሉ በኋላ ይታስብበታል
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን 525 ያህል ክፍሎችን ያቀረበው ቤቶች ድራማ 13ኛ ዓመቱን በተለያዩ ዝግጅቶች ሊያከብር መሆኑ ተገልጿል። ከዚሁ በዓል በኋላ፣ የድራማው ቀጣይነት እንደሚታሰብበትም ተነግሯል።
የድራማው መሪ ተዋናይ እና የጥላሁን ጉግሳ ማስታወቂያና ኪነ ጥበባት ፕሮሞሽን ዋና ስራ አስኪያጅ አርቲስት ጥላሁን ጉግሳ እና የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የድራማ ክፍል ሃላፊ አቶ ሲራክ ጸጋዬ በዛሬው ዕለት በግራንድ ኤልያና ሆቴል በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። በመግለጫውም ላይ የቤቶች ድራማ ተዋንያን ተገኝተው ነበር።
ቤቶች ድራማ በ13 ዓመታት ቆይታው ያልዳሰሳቸው ማሕበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና አገራዊ ጉዳዮች እንደሌሉ አርቲስት ጥላሁን ጉግሳ ተናግሮ፣ “አዳዲስ ጀማሪ ተዋንያንን ማሳደግ እና ማውጣት ዓላማ አድርገን የተነሳን በመሆኑ ራሳቸውን ችለው ከእኛ የተለዩ ተዋንያንን ለመተካት የሄድንበት ርቀት የሰለጠኑ አገራት የፊልም ኢንዱስትሪ የተከተለውን መስመር ተከትለን ስለነበር ፈታኝ ሂደቶችን ለማለፍ ተገድደናል” ብሏል።
ከእነዚህም ሂደቶች መካከል የተዋናይት ሰብለ ተፈራ በድንገተኛ አደጋ ሕይወቷ ማለፍ አንደኛው መሆኑንና ይህንንም በድራማው አባላት በተደረጉ የተለያዩ ጥረቶች ሊቀረፍ መቻሉን አንስቷል።
“ሰብለ ምንጊዜም በልባችን ውስጥ ትኖራለች” ያለው አርቲስት ጥላሁን፣ ለእርሷ በርካታ የመታሰቢያ ዝግጅቶች መከናወናቸውን አንስቶ፣ ሕዳር 27 ቀን 2018 ዓ.ም. በሚከናወነው ክብረ በዓል ላይ እርሷ እንደምትታሰብም ጠቁሟል።
ሌሎች ከድራማው በፈቃዳቸው ራሳቸውን ስላገለሉ ተዋንያን የተናገረው አርቲስት ጥላሁን፣ “ከአሸናፊ ማሕሌት በስተቀር ሌሎች ተዋንያን ከድራማው የወጡት ምንም ነገር ሳያሳውቁ ነው። ይህን ክፍተት ለመቅረፍ በማሰብ የተተኩት ተዋንያን ከውጡት ተዋንያን ባልተናነሰ ሁኔታ ድራማውን ሰርተውታል” ብሏል።
“መንግስትን መተቸት በሚገባን ልክ እንተቻለን” ሲል የተናገረው አርቲስት ጥላሁን፣ ይህ ትችት የሚቀርበው ግን “ከጥላቻ በጸዳ እና በሚዛናዊነት” ስለመሆኑም ነው የጠቆመው። አክሎም፣ “ስራዎቻችንን ተመልክተው አስተያየት የሚሰጡን ባለስልጣናት አሉ” ቢልም፣ የባለስልጣናቱን ስም ከመጥቀስ ተቆጥቧል።
የቤቶች ድራማ ሃሳብ የተጸነሰው በ1996 ዓ.ም. መሆኑን እና በወቅቱ ለ14 ክፍሎች ያህል የሚያገለግል ስክሪፕት ተጽፎ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቢገባም፣ በወቅቱ በጣቢያው ዘንድ ተቀባይነት አለማግኘቱን አውስቷል፣ አርቲስት ጥላሁን። ከእነዚህ ክፍሎች መካከል፣ አራቱን በማቀናጀት በሲኒማ እንዲታይ መደረጉንም ገልጿል።
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የድራማ ክፍል ሃላፊ አቶ ሲራክ ጸጋዬ በበኩላቸው፣ “525 ክፍሎችን የሰራ ድራማ በዓለም ላይ ምንም የለም” ያሉ ሲሆን፣ ይህም በታሪክ ሊመዘገብ እንደሚገባው ተናግረዋል።
ድራማው ለስርጭት ከመብቃቱ ሁለት ዓመታት አስቀድሞ፣ አጠቃላይ ይዘቱን መልክ የማስያዝ ስራ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በኩል መሰራቱን በማንሳት፣ “ይህም ለድራማው የረዥም ጊዜ ቆይታ አጋዥ ሆኖታል” ብለዋል።
በመጪው ጊዜያት የድራማውን ቀጣይነት በተመለከተ ከዚሁ በዓል በኋላ እንደሚታሰብበት አርቲስት ጥላሁን ጉግሳ አስታውቆ፣ በቅርቡም በሌላ ዓይነት ዘውግ አዲስ ድራማ ለተመልካች ዕይታ ለማብቃት እየተሰራ እንደሚገኝ አስረድቷል።
ይህ ድራማ 25 ክፍሎች ያህል ተቀርጸውለት፣ የምስል እና ድምጽ ቅንብሩ ተጠናቅቆለት ለስርጭት ዝግጁ መሆኑን በመግለጽ፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በኩል እንደሚተላለፍም ጠቁሟል።
ከሕዳር 20 ቀን 2018 ዓ.ም. ጀምሮ፣ “የቤቶች ሳምንት” በተሰኘ ማዕቀፍ ስር የተለያዩ ዝግጅቶች ሲከናወኑ፤ ሕዳር 20 ድራማው በሚቀረጽበት መኖሪያ ቤት የፎቶግራፍ ዓውደ ርዕይ፤ ሕዳር 21 በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የሚተላለፍ እና የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ስራዎች የተካተቱበት “የቤቶች ምሽት” የተሰኘ ዝግጅት የሚተላለፍ ሲሆን፤ ሕዳር 24 በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ራስ መኮንን አዳራሽ የፓናል ውይይት እንደሚከናወን ተመላክቷል።
ሕዳር 27 በአድዋ ሙዚየም አዳራሽ የሚካሄደው የማጠቃለያ ዝግጅት ለሶስት ሰዓታት ያህል በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት ሽፋን ሲያገኝ፣ የተዋንያኑ ቀጥታ (Live) የመድረክ ቴአትር፤ ጭውውቶች እና ሌሎች ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች እንደሚቀርቡም ለማወቅ ተችሏል።
