ሲንቄ ባንክ 15 ቢሊዮን ብር የነበረዉን የባንኩ የተፈረመ ካፒታል ወደ 75 ቢሊዮን ብር እንዲያደግ የወሰነዉ በዛሬዉ ዕለት ባካሄደዉ የባለአክሲዮኖች 6ኛ መደበኛ እና 2ኛ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ነዉ ።
ይህም ባንኩ እስካሁን የነበረዉን የብድር አቅርቦት አቅም በብዙ እጥፍ የሚያሳድገዉና ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ እንዲሁም የስራ ዕድል የሚፈጥሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ጅምር የፈጠራ ስራዎችን ለማበራከት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረዉ የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ቶሎሳ ደገፋ መናገራቸውን ብስራት ሬዲዮ ሠምቷል ።
በተጨማሪም ባንኩ ከተለያዩ የዉጭ ባንኮች ጋር ያለዉን አጋርነት በማጠናከር የአገልግሎት አድማሱን ለማስፋት በሚያደርገዉ ጥረት ዉስጥ ጉልህ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሏል ።
የባንኩን አገልግሎት አድማስ ወደ ምስራቅ አፍሪካ ሀገራት በማስፋት ተወዳዳሪነቱን በእጅጉ እንደሚያጎለብተዉ ተገልጿል ።
የባንኩ ጠቅላላ ተቀማጭ ገንዘብ ወደ 135.7 ቢሊዮን ብር ያደገ ሲሆን ለደንበኞች ተደራሽ የተደረገው ጠቅላላ የብድር መጠን ወደ 56.43 ቢሊዮን ብር አድጓል ተብሏል ፡፡
ይህም ጠቅላላ የብድር መጠን ያለፉትን ወራት አፈጻጸም ጨምሮ ወደ 8ዐ ቢሊዮን ብር ከፍ ማለቱ ተገልጿል ፡፡ ከተሰጠው ጠቅላላ ብድር ውስጥ 38.4 ቢሊዮን ብር በማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎት በኩል ለግብርና ዘርፍ የተሰጠ መሆኑን ባንኩ አስታውቋል ።
