ታህሳስ 24 ቀን 2018(መናኸሪያ ሬዲዮ)የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ለሚያካሂደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ፣ በጊዜ ሰሌዳው መሠረት የተለያዩ የቅድመ-ምርጫ ተግባራትን በማከናወን ላይ ይገኛል።
በዚህም መሠረት ቦርዱ ታኅሣሥ 21 እና 22 ቀን 2018 ዓ.ም ለዋና አሠልጣኞችና ለምርጫ ክልል አስተባባሪዎች የሥራ ትውውቅ ሥልጠና ሰጥቷል።
የሥልጠናውን መክፈቻ ንግግር ያደረጉት የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ፤ ቦርዱ ከሥልጠናው በፊት ያከናወናቸውን የቅድመ-ምርጫ ተግባራት አብራርተዋል።
ለተከታታይ ሁለት ቀናት የሚሰጠው ይህ ሥልጠና ከቅድመ-ምርጫ ተግባራት መካከል አንዱና ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ሰብሳቢዋ፤ ሥልጠናው ውጤታማ የሚባለውም ትምህርቱ በተዋረድ ለምርጫ ክልል አስፈጻሚዎች ሲደርስ የመረጃው ጥሬ ሀቅ ሳይዛነፍ መድረስ ሲችል መሆኑን በአጽንዖት አሳስበዋል።
ሥልጠናው በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫና ቦርዱ እሱን ተከትሎ ባከናወናቸው ምርጫዎች በዋና አሠልጣኝነት ተሳትፈው የተሻለ አፈጻጸም ያሳዩ አሠልጣኞችንና የቦርዱን የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ባለሙያዎችን ያካተተ ነው።
በሥልጠናውም የምርጫ ፅንሰ-ሐሳብና መርሆች፣ የኢትዮጵያ የምርጫ አስተዳደር ባህሪያት፣ የምርጫ ክልል ጽሕፈት ቤቶች አወቃቀር፣ ሥልጣንና ተግባራት፣ እንዲሁም የምርጫ ጣቢያ አስፈጻሚዎች አመላመልና የቅጥር ሂደት ተዳስሰዋል።
በተጨማሪም አካታች የሆነ የምርጫ ምዝገባ ባህሪያት፣ የአቤቱታና የቅሬታ አፈታት ሥነ-ዘዴዎች፣ እንዲሁም ከድምፅ አሰጣጥ እስከ ውጤት አገላለጽ ድረስ ያሉት አጠቃላይ ቅደም-ተከተሎች በሥልጠናው ከተሸፈኑ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል።
የቦርዱ የሥልጠና ሥራ ክፍል ኃላፊ አቶ መልሰው ክብረት በማጠቃለያ ንግግራቸው፤ ሥልጠናው በቀጣዮቹ ቀናት በተዋረድ በ22 ማዕከላት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።
ሥልጠናው በሚሰጥበት ጊዜም ሕገ-መንግሥቱንና የቦርዱን አዋጆች መሠረት አድርጎ የተዘጋጀው የሥልጠና ማንዋል መረጃዎች፣ እንዲሁም የተሰጡ መሠረታዊ የግንዛቤ ማስጨበጫዎች ሳይጓደሉ ለሠልጣኞች እንዲደርሱ ማድረግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
