የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከአገራቸው ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ጋር ሰኞ ዕለት ባደረጉት ቆይታ፣ “ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ ጦርነት እንዳወጀች” በመግለጽ ወነጀሉ፤ እንዲሁም በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ውጥረት ከቀይ ባሕር መውጫ ጋር የተያያዘ ተደርጎ የሚቀርብበትን መንገድ ውድቅ አደረጉ።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ስለ አሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሰፊ ንግግር ካደረጉ በኋላ፣ ከኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲ ጋር ስላላቸው እየሻከረ የመጣ ግንኙነት አንስተዋል። በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ውጥረት “ከቀይ ባሕር መውጫ ጋር የተያያዘ ነው” የሚሉትን ሀሳቦች ውድቅ ያደረጉ ሲሆን፣ “ኤርትራ እንዲህ ዓይነት ፍላጎት እንደሌላትም” ጠቁመዋል። “ለእኛ ጉዳዩ በቀጥታ ከቀይ ባሕር ጋር የተያያዘ አይደለም” ሲሉም ተናግረዋል።
የኤርትራው መሪ የኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲ የሆነው ብልጽግና “ሰፊ ወታደራዊ አጀንዳ እያካሄደ ነው” ሲሉ ወንጅለዋል።
“የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ቢፈረምም በመላ ሀገሪቱ በትጥቅ የታገዙ ግጭቶች እንደቀጠሉ” መሆናቸውን በመጥቀስ፤ “በአማራ ክልል ፋኖን ለማጥፋት ጦርነት ታውጇል። በትግራይ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ እና በሶማሊያ ጦርነት ታውጇል” ብለዋል።
አክለውም “ይህ ጨዋታ የብልጽግና አጀንዳ አይደለም። አጀንዳው የሌሎች ነው። ገንዘብ እየሰጡ እየደገፉት ያሉት ሌሎች ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አክለውም “ኢትዮጵያ ለጦርነት ዝግጅት ድሮኖችንና መሣሪያዎችን እያስገባች ነው” ሲሉ ከሰዋል። “የተቀናጀ የጦርነት ጥረት” ሲሉ ለገለጹት ድርጊት የገንዘብ ምንጩ እነማን እንደሆኑም ጥያቄ አንስተዋል። “ድሮኖቹን የሚያመጣው ማነው? እነዚህን ሁሉ መሣሪያዎች ከውጭ የሚገዛው ማነው? እነዚህን ሁሉ ሴራዎች በገንዘብ የሚደግፈው ማነው? ይሄ ሁሉ ገንዘብ ከየት ነው የሚመጣው?” ሲሉም ጠይቀዋል።
ፕሬዝዳንቱ በሰጡት ቃለ ምልልስ ውጥረቱን የሚያባብሱትን አካላት “ሰነፍ፣ የከሰረ፣ ፈሪ እና ስግብግብ ነው” በማለት ገልፀዋቸዋል።
ኤርትራ ጥቃት ቢሰነዘርባት እንኳ ከማንም አካል የውጭ ድጋፍ እንደማትፈልግ ተናግረዋል።
“ጦርነት ከታወጀብን መብታችንን ለማስጠበቅ ማንንም አንለምንም” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ ኤርትራ “የውሸት ማዕዳቸው” ባሉት ነገር ውስጥ ልትገባ እንደማይገባም አክለው ገልጸዋል።
የሱዳን ጉዳይን በተመለከተም ፕሬዝዳንት ኢሳያስ የሀገሪቱን ቀውስ ታሪካዊ መሠረት ያብራሩ ሲሆን፤ የሱዳን ሕዝብ ከዓመታት ትግል በኋላ የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ዑመር አል-በሽርን በ”ሕዝባዊ አመጽ” ከሥልጣን ማውረዱን ገልፀዋል።
የሱዳን ጦር ሀገሪቱን እንደ ሉዓላዊት ሀገር ለማስቀጠል ከሕዝብ ጎን ለመቆም የወሰነው ውሳኔ አዲስ የሽግግር ምዕራፍ መክፈቱንና ለጊዜያዊ የሽግግር ምክር ቤት ምስረታ መንገድ መጥረጉንም ተናግረዋል።
በሱዳን ያለውን ቀውስ ሀገር ውስጥ ባሉ ኃይሎች መካከል የሚደረግ የሥልጣን ሽኩቻ ነው ተብሎ የሚገለጸውን ውድቅ ያደረጉት ፕሬዝዳንቱ፤ “እስካሁን ድረስ በሱዳን ውስጥ የእርስ በእርስ ጦርነት የለም፣ በጄኔራሎች መካከልም ምንም ዓይነት ግጭትም ሆነ ፉክክር የለም” ብለዋል። ይልቁንም “የውጭ ኃይላት፣ በተለይም የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለሁኔታው መባባስ ዋነኛ ተዋናይ ናት” ሲሉ ከሰዋል።
እ.ኤ.አ. በ2011 ከነበረው የደቡብ ሱዳን መገንጠል ጋር በማነፃፀር፣ በወቅቱ የተፈጸመው ፖለቲካዊ ስህተት “አሁን በሱዳን ላይ ሊደገም አይገባም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። “የሱዳን ጦር ሊመሰገንና ሊደገፍ ይገባው ነበር” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ አሁን እየታዩ ያሉ ሁኔታዎች አዲስ እንዳልሆኑም አክለው ገልጸዋል።
“ለረጅም ጊዜ ስንከታተለው የነበረ ጉዳይ ነው። ትናንት የሆነውን ነገር አንቀበልም። አሁን እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ዓላማቸው ምንድን ነው?” ሲሉ ጠይቀዋል።
የሱዳንን ቀውስ ለመፍታት በግብፅ አነሳሽነት የተጀመረውን የጎረቤት ሀገራት ጉባኤ “ጥሩ ጅምር” ነበር ካሉ በኋላ፣ ሳይታሰብ በድንገት መክሸፉን ገልጸዋል። እንደ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ገለጻ፣ የሀገሪቱን ታሪካዊ አደራ ተሸክሟል ያሉት የሱዳን ጦር ሽግግሩን የመምራት ዕድል ሊሰጠው ይገባል፤ በሌላ በኩል ግን ለግጭቱ ድጋፍ የሚሰጡ አካላት “ለደረሰው ሞትና ችግር ሁሉ” ተጠያቂ መሆን እንዳለባቸው አሳስበዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች ላይ የሚደረገውን የውጭ ጣልቃ ገብነት በድጋሚ የነቀፉ ሲሆን፣ የቀጣናው አለመረጋጋት የሚቀሰቀሰው በውጭ ተዋናዮች መሆኑን ሞግተዋል። ይሁን እንጂ ኤርትራ ከሳውዲ አረቢያ ጋር የምታደርገው ግንኙነት በጣልቃ ገብነት ሳይሆን በምክክር ላይ የተመሠረተ የቀጠናውን መረጋጋት ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
ከሳውዲ አረቢያ ጋር ያለን የሁለትዮሽ ግንኙነት የጋራ መግባባትን ለመፍጠር ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ እንዲህ ያሉ ምክክሮች ቀጠናዊ ኃላፊነትን ለማጎልበት የታለሙ መሆናቸውን አክለው ገልጸዋል። እንዲሁም ግብፅን እና ሳውዲ አረቢያን ጨምሮ ቀጠናዊ ተዋናዮች ከፍተኛ ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ ያቀረቡ ሲሆን፣ በውጭ ኃይላት የበላይነት የሚመራ የደህንነት ጥምረትን ግን ውድቅ አድርገዋል።
“የባሕር ጠረፍህን ወይም የአየር ክልልህን በኃያላን የውጭ ሀገራት አማካኝነት ለመጠበቅ መሞከር አይሠራም፤” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ “የዚህን ቀጠናዊ መስመር ደህንነት ማረጋገጥ የሚችለው የእኛ [የቀጠናው ሀገራት] ጥምረት ብቻ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ የውጭ ጣልቃ ገብነት ለአፍሪካ ቀንድ ቀውስ መባባስ ምክንያት ነው ሲሉ ሲከሱ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። በህዳር ወር 2017 ዓ.ም ለግብፅ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ሰፊ ቃለ-መጠይቅ፣ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ በአፍሪካ ቀንድ፣ በቀይ ባሕር አካባቢና በአጠቃላይ በአህጉሪቱ ላይ ለሚታየው አለመረጋጋት ተጠያቂዎቹ የውጭ ኃይላት መሆናቸውን ገልፀው ነበር።
ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ “አል-ቃሂራ ኒውስ” ከተሰኘው መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ፣ በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ያሉ ግጭቶች “በተለያዩ ኃይላትና መንግሥታት ጣልቃ ገብነት ምክንያት ውስብስብ ሆነዋል” ብለዋል። ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያንና ደቡብ ሱዳንን እንደ ምሳሌ በመጥቀስ፣ በእነዚህ አገራት ያለው አለመረጋጋት “ውስጣዊ ብቻ ሳይሆን ቀጠናዊ አልፎ ተርፎም ዓለም አቀፋዊ ይዘት አለው” ሲሉ አበክረዋል።
“ሶማሊያ 3,300 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የባሕር ጠረፍ ያላት ሀገር ናት፤ ይህ በስትራቴጂካዊ ቦታ ላይ የሚገኝ ረጅም የባሕር ጠረፍ ደግሞ ሀገሪቱ መረጋጋት እንዳታገኝ አድርጓታል፤” ብለዋል። “የሶማሊያ ችግር ውስጣዊ ብቻ ሳይሆን ቀጠናዊና ዓለም አቀፋዊም ጭምር ነው” ሲሉም አክለዋል።
ወደ ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ጉዳይ ሲመለሱም፣“ባለፉት 30 ዓመታት የታዘብነው በብሔር መከፋፈልን፣ በጎሳ መበታተንን እና አለመረጋጋትን ነው” ያሉ ሲሆን ከሱዳን የተገነጠለችው ደቡብ ሱዳንም በእርስ በእርስ ጦርነት የምትታመስ ያልተረጋጋች ሀገር ሆናለች” ብለዋል። ቀጠናዊ ግጭቶችን ለመፍታት ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ የዓለም አቀፍ “ልዩ መልዕክተኞች” የሚሰማሩበትን መንገድም የነቀፉ ሲሆን፤ እንዲህ ያሉ ጣልቃ ገብነቶች “ሁኔታውን ይበልጥ ያወሳስቡታል እንጂ መፍትሔ አያመጡም” ሲሉ ተደምጠዋል።
“ኃላፊነቱ በመጀመሪያ የውስጥ ነው” ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ “ማንኛውም ድርጅት ትልቅም ይሁን ትንሽ፣ ቀጠናዊም ይሁን ዓለም አቀፋዊ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት አያስፈልገውም። ሆኖም ይህ ዓይነቱ ጣልቃ ገብነት ላለፉት 80 ዓመታት ቀጥሏል” ብለዋል። “የውጭ ተዋናዮች በእያንዳንዱ ሀገር ውስጥ ያሉትን የውስጥ እና የአካባቢ ሁኔታዎች ከማወሳሰብ ውጭ አስፈላጊ አይደሉም” ሲሉ ጠቁመዋል።
ከዚህ ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በጥቅምት ወር 2018 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት፤ ኢትዮጵያ እንዴት የቀይ ባሕር መውጫዋን እንዳጣች የሚያሳይ ምንም ዓይነት ይፋዊ መዝገብ ወይም ተቋማዊ ውሳኔ የለም ብለዋል። ጉዳዩንም በሰላማዊ ውይይት መፈታት ያለበት ሕጋዊ፣ ታሪካዊ እና የህልውና ጥያቄ ሲሉ ገልጸውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ጥቅምት 18 ቀን 2018 ዓ.ም. በተካሄደው በ6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር ያጣችው በሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ በፓርላማ ወይም በሕዝብ ይሁንታ በማንኛውም ሕጋዊና የምክክር ሂደት ተወስኖ አይደለም ብለዋል።
“ሕዝብ ካላወቀ፣ ፓርላማው ካላወቀ፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤትም ካላወቀ ታዲያ ኢትዮጵያን የባሕር በር አልባ ያደረጋት ውሳኔ በማን ተወሰነ?” ሲሉ የጠየቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ይህ እንዴት እንደተፈጸመ የሚያስረዳ አንድም ሰነድ ማግኘት አልቻልንም” ሲሉ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ የቀይ ባሕር መውጫ ጥያቄ “አዲስ ወይም ስሜታዊ ጉዳይ” ሳይሆን፣ ይልቁንም በታሪካዊና በኢኮኖሚያዊ አስፈላጊነት ላይ የተመሠረተ መሆኑን አስምረውበታል። ጉዳዩ እንደ ትንኮሳ ሊታይ እንደማይገባው ገልጸው፤ “የህልውና ጥያቄ፣ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። አስ
