የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ እና የግብፁ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ ካይሮ ውስጥ ባደረጉት ውይይት ያላቸውን የደኅንነት ትብብር በማጠናከር ላይ መስማማታቸው ተዘገበ።
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ወደ ካይሮ ያቀኑት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት፤ ከፕሬዝዳንት አልሲሲ ጋር በሰጡት የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ “የሶማሊያን አንድነት የሚጋፋ የትኛውንም ተግባር በጋራ እንቃወማለን” ብለዋል።
ግብፅ በበኩሏ በአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ የድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ ሥር ወታደሮቿን ለመላክ በያዘችው ዕቅድ መሠረት ተግባራዊ እንደምታደርግ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
የግብፁ ፕሬዝዳንት ጨምረውም የሶማሊያ መረጋጋት ለቀጣናው ልማት እና ደኅንነት “ወሳኝ ጉዳይ ነው” በማለት ሶማሊያን ለመደገፍ አገራቸው የሚጠበቅባትን ታደርጋለች ብለዋል።
ሶማሊያ የግዛቷ አካል እንደሆነች ለምትመለከታት ሶማሊላንድ እስራኤል የአገርነት ዕውቅና መስጠቷን ተከትሎ ግብፅ እና ሶማሊያ የጋራ አቋም ይዘው ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በአልጀዚራ ቴሌቪዥን ላይ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ሶማሊላንድ ከጋዛ የሚፈናቀሉ ፍልስጤማውያንን ለማስፈር እና ለእስራኤል ጦር ሰፈር ለመስጠት ተስማምታለች ማለታቸውን ሶማሊላንድ ወቅሳለች።
ፕሬዝዳንቱ በቃለ ምልልሱ ላይ እስራኤል በሶማሊላንድ ውስጥ የጦር ሰፈር የምትመሠርት ከሆነ “እራሳችንን ለመከላከል ባለን አቅም ሁሉ እንፋለማለን” ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተው ነበር።
ነገር ግን የሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ ሐሰን አደን በሰጡት ምላሽ ፕሬዝዳንቱ ያሉትን “እውነታ የሌለው ግልጽ ውሸት” በማለት ውድቅ አድርገውታል።
ቃል አቀባዩ ጨምረውም የሶማሊያ መሪ አስተያየት “በውስጡ የገጠመውን ውድቀት በሌሎች ላይ ለማንጸባረቅ የሚፈለግ የተለመደው ዓይነት ያልተሳካለት አመራር አካሄድ ነው” በማለት ሶማሊያ የራሷን ደኅንነት እንኳን መጠበቅ ያልቻለች ናት በማለት ተናግረዋል።
bbc Amharic
