የአውሮፓ ህብረት ቲክቶክ ተጠቃሚዎችን ሱስ በሚያስይዝ መልኩ የቀረጻቸውን የአሰራር ዲዛይኖች ካልቀየረ ከፍተኛ ቅጣት እንደሚጥልበት አስጠነቀቀ።
ህብረቱ ባደረገው ምርመራ መተግበሪያው እንደ “Autoplay” እና “Infinite Scroll” ያሉ ገጽታዎች በተጠቃሚዎች ላይ ስለሚያደርሱት ጉዳት በቂ ምዘና አላደረገም በሚል የኦንላይን ደንቡን መጣሱን ገልጿል።
ቲክቶክ ከቅጣት ለመዳን አልጎሪዝሙን እንዲቀይርና የስክሪን ጊዜ እፎይታን እንዲሰጥ የጠየቀው ህብረቱ፣ ኩባንያው ማሻሻያ የማያደርግ ከሆነ ከአመታዊ ዓለም አቀፍ ገቢው 6 በመቶ ያህሉን ሊቀጣው እንደሚችል አስታውቋል።
ቲክቶክ በቀረበበት ውንጀላ ላይ ተቃውሞውን ቢገልጽም፣ ህብረቱ ከዚህ ቀደም በኢሎን መስኩ ኤክስ (X) ላይ የ120 ሚሊዮን ዩሮ ቅጣት መጣሉ የሚታወስ በመሆኑ ኩባንያው ከባድ ጫና ውስጥ እንደሚወድቅ ተመላክቷል።
