ከሶማሊያ በመነጠል ነጻነቷን ያወጀችው ሶማሌላንድ ለዩናይትድ ስቴትስ ማዕድንም ይሁን የጦር ሰፈር ለመስጠት ፍቃደኛ እንደሆነች አንድ የሶማሌላንድ ሚኒስትር ለፈረንሳዩ ዜና ምንጭ አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ተናገሩ።
“ለዩናይትድ ስቴትስ ብቻ የተወሰነ (የተፈጥሮ ሀብታችንን) ለመስጠት ፈቃደኞች ነን። እንዲሁም ለዩናይትድ ስቴትስ የጦር ሰፈር ለማቅረብ ዝግጁ ነን” ሲሉ ሚኒስትር ካዳር ሁሴን አብዲ ቅዳሜ ዕለት በሰጡት ቃለ ምልልስ ለአዣንስ ፍራንስ ፕረስ ተናግረዋል።
„ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ከስምምነት እንደርሳለን ብለንም እናምናለን።“ ብለዋል። የሶማሌላንድ ፕሬዝዳንት አብዱራህማን መሐመድ አብዱላሂ ከጥቂት ሳምንታት በፊት እስራኤል የሶማሌላንድ ማዕድን ሀብትን የማግኘት መብት እንዲኖራት ሀሳብ አቅርበው ነበር።
ሶማሌላንድ ከሶማሊያ በመነጠል ነጻነቷን ካወጀች 34 ዓመት ቢሆናትም እስካሁን ከእስራኤል በስተቀር ዕውቅና የሰጣት ሀገር የለም። እስራኤል ለሶማሌላንድ እውቅና የሰጠችው ባለፈው ታህሳስ ወር ነበር።
የአፍሪካ ህብረት እና በርካታ የአረብ ሀገራት ሶማሊያን በመደገፍ የእስራኤልን ርምጃ ሲያወግዙ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እስራኤል ለሶማሌላንድ እውቅና መስጠት መብቷ እንደሆነ በመግለፅ ለእስራኤል ተሟግተዋል። ፎቶ ከማህደር ፦በርበራ ወደብ ሶማሌላንድ
DW Amharic
