የአርትስ ቴሌቪዥን የሥራ ኃላፊዎች፣ ከድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) አዲስ አልበም ጋር በተያያዘ ከገቡት ሥምምነት አኳያ ማብራሪያ እንዲሰጡ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን መጠየቃቸው ተሰምቷል።
ማክሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ከምሽቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ ሊሰጥ የነበረው የቴዲ አፍሮ አዲስ አልበም “ኢቶሪካ” ጋዜጣዊ መግለጫ በይፋ ታግዷል።
ድምጻዊው ከተለያዩ ጋዜጠኞች ጋር የሚያደርገውን ይህንን መግለጫ በቀጥታ ስርጭት ለማስተላለፍ ከአርትስ ቴሌቪዥን ጋር አስቀድሞ ስምምነት ተፈራርሞ የነበረ ቢሆንም፣ ከመንግስት በቀረበ ጥብቅ እገዳ ምክንያት የቀጥታ ስርጭቱ እንዲቋረጥ ተገዷል።
ማክሰኞ ሚያዝያ 6 ቀን 2018 ዓ.ም ረፋዱ ላይ የቴሌቪዥን ጣቢያው ስራ አስፈፃሚን ጨምሮ የጣቢያው ስራ ኃላፊዎች በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ዋና መስሪያ ቤት በመገኘት ስለ ሥምምነቱ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን ከስምንት ዓመታት ቆይታ በኋላ ‘ኢቶሪካ’ የተሰኘውን አዲስ አልበሙን የፊታችን ሐሙስ ሚያዝያ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የሙዚቃ ማሰራጫ መተግበሪያዎች እና በዩቲዩብ ገጹ በኩል ለአድማጮች እንደሚያቀርብ ማስታወቁ ይታወሳል።
የመግለጫው መታገድ እና የቴሌቪዥን ጣቢያው ኃላፊዎች መጠራት በአልበሙ ይፋ መሆን ላይ ስለሚኖረው ተጽዕኖ እስካሁን በይፋ የተባለ ነገር የለም።
ዋዜማ
