የአዲስ አበባ ንግድና የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት “ዘላቂ ንግድ፤ የንግድ ተወዳዳሪነት በኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው 27ኛው አዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ ንግድ ትርኢት ከሚያዝያ 15 እስከ 17 ቀን 2018 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ይካሄዳል።
ለሦስት ቀናት በሚቆየው በዚህ መድረክ ላይ ከተለያዩ የንግድ ዘርፎች የተወጣጡ 150 የአገር ውስጥና የውጭ ሀገር ተሳታፊዎች ምርትና አገልግሎታቸውን እንደሚያስተዋውቁ ምክር ቤቱ ገልጿል።
የንግድ ትርኢቱ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ሚያዝያ 15 ቀን 2018 ዓ.ም. ከ7፡00 ሰዓት ጀምሮ በኤግዚቢሽን ማዕከል ይከናወናል ተብሏል።
በመድረኩ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ አምባሳደሮች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወካዮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ ይጠበቃልል።
ይህ ንግድ ትርኢት ተሳታፊዎች የንግድ ለንግድ ግንኙነት እንዲፈጥሩ፣ ልምድ እንዲቀዋወጡና ለድንበር ተሻጋሪ ሽርክና ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ተገልጾአል።
ምክር ቤቱ መሰል ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢቶችን ማዘጋጀቱ በሀገሪቱ የንግድና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዲስፋፋ በማድረግ ለኢኮኖሚ መነቃቃት የላቀ ፋይዳ እንዳለው አስታውቋል።
ተቋሙ የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማገዝ የሚያከናውናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራት አካል የሆነው ይህ ዝግጅት፣ ለፈጠራና ለዘላቂ የንግድ ተወዳዳሪነት ልዩ መድረክ እንደሚሆንም ተገልጿል፡፡
