ኢንፊኒቲ ኃላፊነቱ የተወሠነ መሠረታዊ የቁጠባ እና ብድር ኀብረት ሥራ ማኀበር ለቤትና ለመኪና መግዣ ብድር እየሰጠ እንደሚገኝ በዛሬው እለት በአዲስ አበባ አሚር ኮሜርሻል ኮምፕሌክስ ህንፃ ላይ ዋና መስሪያ ቤቱን አስመልክቶ ባካሄደው የመክፈቻ መርሀግብር ላይ አስታውቋል።
ማኀበሩ ከ1ዐ ሚሊየን ብር በላይ በሆነ መነሻ ካፒታል ከፌደራል ኀብረት ስራ ኮሚሽን እውቅና በማግኘት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመ ሀገራዊ ተቋም ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ750 በላይ አባላት እንዳሉትና የካፒታል መጠኑም ከ20 ሚሊየን ብር በላይ ማደጉን የኢንፊኒቲ ኃላፊነቱ የተወሠነ መሠረታዊ የቁጠባ እና ብድር ኀብረት ሥራ ማኀበር የስራ አመራር ሰብሳቢ ዶክተር እስማኤል ሀሰን ተነግረዋል።
ዶክተር እስማኤል አክለውም ማኅበሩ አዲስ ያበለጸገውንና ደንበኞች ባሉበት በየትኛውም ቦታ ሆነው አባል መሆንና መቆጠብ እንዲሁም መበደር የሚችሉበትን እድል የያዘ ድረ ገጽ ማበልጸጉንም ገልጸዋል፡፡
በይፋዊ ስራ ማሥጀመሪያ ሥነ ስርዓቱም የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ተወካዮች፣ የማኅበሩ ባለ ድርሻ አባላት፣ የማኀበሩ ስራ አመራር እና ሠራተኞች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
ማኅበሩ ለመጀመሪያ ጊዜ በብድር መኪና ለገዛላቸው ደንበኞቹ የመኪና ቁልፍ ርክክብ ማካሄዱ ተገልጿል።
ማኅበሩ ከንብ ባንክ፣ ኢኮ ሞተርስ እንዲሁም ከአዲሲቷ ኢትዮጵያ ኃ/የተ/መሰራዊ ቁጠባ እና ብድር ኅብረት ስራ ማኅበር እና ግርማ የመኪና አስመጭ ኩባንያ ጋር በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡
ማኀበሩ ለመኪና፣ ለቤት መግዣ እንዲሁም ለሌሎች የቢዝነስ ሥራዎች እሥከ 4 ሚሊየን ብር ብድር እየሠጠ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በመክፈቻ ስነስርአቱ ላይ በአሁን ሰአት በሀገሪቱ ያሉ የቁጠባ እና ብድር ኀብረት ሥራ ማኀበራት ለ1.6 ሚሊየን ህዝብ ብድር አገልግሎት መስጠታቸው ተጠቁሟል::
ኢንፊኒቲ ኃላፊነቱ የተወሠነ መሠረታዊ የቁጠባ እና ብድር ኀብረት ሥራ ማኀበር ባለፈው የካቲት 30/2018 ዓ.ም በፌደራል ኀብረት ሥራ ኮሚሽን የምዝገባ ምሥክር ወረቀት የተሠጠው ሲሆን በቀጣይም በደሴና በወልቂጤ ቅርንጫፍን ለመክፈት በዝግጅት ላይ እንደሆነ ተገልጿል::
