በፈረንሳይ እና በተለያዩ የአውሮፓ ክፍሎች የተከሰተው ከፍተኛ የሙቀት ማዕበል ተከትሎ፣ በሀገሪቱ “ከተለመደው የሞት መጠን” በላይ የ1,000 ሰዎች ተጨማሪ ህይወት ማለፉን የፈረንሳይ የህዝብ ጤና ኤጀንሲ ሲገለጽ የዓለም ጤና ድርጂት ዋና ዳይሬክተር ደግሞ በመላው አውሮፓ 1300 ሰዎች መሞታቸውን አስታወቀ።
እንደ ጤና ባለሙያዎች ገለጻ ከሳምንት በፊት የጀመረው ይህ እጅግ አስከፊ ነው የተባለው የሙቀት ማዕበል በአውሮፓ ታሪክ ከተመዘገቡት የከፋው ተብሏል።
በዚህም ሳቢያ በፈረንሳይ ከተመዘገበው ተጨማሪ የሞት አደጋ ውስጥ 85 በመቶ ያህሉ ዕድሜያቸው 65 እና ከዚያ በላይ የሆኑ አረጋውያን መሆናቸው ተገልጿል። በተለይም በፓሪስና በዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች በቤት ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ላይ የደረሰው የሞት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
የፈረንሳይ የጤና ሚኒስቴር ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደገለፀው ከሆነ ምንም እንኳ በአንዳንድ አካባቢዎች ላይ በአውሎ ነፋስና በከባድ ዝናብ የታጀበ ቅዝቃዜ መታየት ቢጀምርም፣ በሙቀቱ ምክንያት የሚመጣ የጤና ጉዳት አሁንም አላበቃም ብለዋል።
ሚኒስትሩ “ክስተቱ ገና አልተጠናቀቀም፤ የሙቀት ማዕበሉ ካለፈ በኋላም ቢሆን የጤናው ተፅዕኖ እስከ 10 ቀናት ሊቆይ ይችላል”ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም በበኩላቸው አውሮፓ በዓለም ላይ በከፍተኛ ፍጥነት እየሞቀች ያለች አህጉር መሆኗን በመግለጽ 1300 ሰዎች መሞታቸውን ገለፀች ።
በአሁኑ ወቅት ከ150 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ለከፍተኛ ሙቀት መጋለጣቸውንና የአውሮፓ መኖሪያ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶችና የሥራ ቦታዎች ለዚህ ዓይነቱ ከባድ ሙቀት ተስማሚ ሆነው አልተገነቡም ሲሉ መናገራቸው ተዘግቧል፡፡
ተመራማሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ይህን መሰል አስከፊ የሙቀት ማዕበል በሰው ልጅ ምክንያት ከሚመጣው የአየር ንብረት ለውጥ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ሲሆን፣ በተለይም ሌሊት ላይ የሚመዘገበው ከፍተኛ የሙቀት መጠን ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት ከነበረው ይልቅ አሁን ላይ የመከሰት ዕድሉ በ100 ጨምሯል።
በዚህ የሙቀት ሰላባ ተጠቂዋ ፈረንሳይ ብቻ ሳትሆን እንደ ጀርመን፣ ብሪታንያ እና ስዊዘርላንድ ያሉ ሀገራት ደግሞ በሰኔ ወር ውስጥ የምንጊዜም ከፍተኛውን የሙቀት መጠን ከ40 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ መመዝገባቸው ተገልጿል።
ይህ የአየር ሁኔታ በኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች፣ በባቡር መሠረተ ልማቶች እና በጤና ሥርዓቱ ላይ ከፍተኛ ጫና እያሳደረ ይገኛል ተብሏል ።
