የአዲስ አበባ ሆቴል እና ቱሪዝም ባለሙያዎች ማኅበር ሁለተኛውን የሆስፒታሊቲ እና ቱሪዝም እውቅና እና ሽልማት መርሐ ግብር ነሐሴ 23 ቀን 2018 ዓ.ም. እንደሚያካሂድ አስታወቀ። መርሃ-ግብሩ በካፒታል ሆቴል እና ስፓ ከቀኑ 9 ሰዓት ጀምሮ ይካሄዳል።
የማኅበሩ ፕሬዝዳንት አቶ አሸናፊ ሙሉጌታ እንደገለጹት፣ መርሃ-ግብሩ በኢንዱስትሪው ውስጥ የሚታዩ አበይት አፈጻጸሞችን ለማበረታታት እና የላቀ የአገልግሎት ብቃትን ለማረጋገጥ ያለመ ነው። መርሃ ግብሩ ከ25 በላይ ሽልማቶችን የያዙ 4 ዋና ዋና የዕውቅና ዘርፎች አሉት።
የግል ብቃት እና የላቀ ሙያዊ እውቅና የመጀመሪያው ዘርፍ ሲሆን፣ ሥራ አመራር እና ፋይናንስ አስተዳደርን ያካትታል። የምግብ እና መጠጥ ዝግጅት እንዲሁም የደንበኞች አገልግሎት ላሳዩ ባለሙያዎችም ሽልማት ይሰጣል።
ሁለተኛው ዘርፍ የድርጅቶች እና የሆቴሎች እውቅና ነው። ጥራት እና ፈጠራ አሠራር ላሳዩ ሆቴሎች፣ ሪዞርቶች እና አስጎብኚ ድርጅቶች ይሰጣል።
የተቋማት እና የማኅበረሰብ አገልግሎት እውቅና ሦስተኛው ዘርፍ ነው። ዘላቂ ቱሪዝም እና አካባቢ ጥበቃ ላይ ለተሰማሩ ተቋማት እውቅና ይሰጣል። አራተኛው ዘርፍ የሕይወት ዘመን የላቀ አገልግሎት ሽልማት ነው።
ምርጫው የአገልግሎት ጥራት እና የደንበኞች እርካታን መሠረት ያደረገ መሆኑ ተገልጿል። የሥራ አካባቢ ምቺት እና የሙያ ሥነ ምግባርም እንደተጤኑ ታውቋል።
