ዓርብ፣ ነሐሴ 01 ቀን 2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ፌደራል ፍርድ ቤቶች፣ በአማራ ክልል ባህር ዳር እና በኦሮሚያ ክልል አዳማ ደግሞ በክልል ፍርድ ቤቶች በተፋጠነ የወንጀል ፍርድ ሂደት ላይ ግልፅ እና ወጥነት የሌለው አሰራር መኖሩን የጠቆመው የፌደራል ህግ እና ፍትሕ ኢንስቲትዩት ጥናት፤ በሂደቱ የታዩ ወንጀሎች እና መዛግብት የሚቀርቡበት መስፈርት በግልፅ ባለመታወቁ ምክንያት የፍትህ አካላት ሂደቱን ለማስፈራሪያ፣ ለግል በቀል እና ተከሳሽ በዋስትና እንዲያመልጥ መጠቀሚያ በማድረግ ለሙስና ክፍተት መፍጠሩን ይፋ አደረገ።
የፌደራል ህግ እና ፍትሕ ኢንስቲትዩት በአዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ ክልል አዳማ እና በአማራ ክልል ባህር ዳር በሚገኙ ፍርድ ቤቶች ላይ የተፋጠነ የወንጀል ፍርድ ሂደት አተገባበር ላይ ግልፅነት እና ወጥነት የጎደለው የፍርድ ቤት አሠራር ክፍተቶች መኖራቸውን ባካሄደው ጥናት አመልክቷል።
ጥናቱ አክሎም፤ የተፋጠነ የወንጀል ፍርድ ሂደት “ፈጣንና እዚያው የሚጠናቀቅ” በመሆኑ ለሙስና እና ለድርድር ጊዜና ክፍተት አይሰጥም የሚል እምነት ያለው ቢሆንም፣ ነገር ግን በሂደቱ የታዩ ወንጀሎች እንዲሁም መዛግብት የሚቀርቡበት መስፈርት በግልፅ ባለመታወቁ ምክንያት “የፍትህ አካላት ሂደቱን ለማስፈራሪያ፤ ለግል በቀል እና ተከሳሽ በዋስትና እንዲያመልጥ መጠቀሚያ በማድረግ ለሙስና ክፍተት ፈጥሯል” ሲል አመልክቷል።
ኢንስቲትዩቱ ለጥናቱ መካሄድ እንደ ምክንያት የጠቀሳቸው ደግሞ የፍርድ ሂደቱ ወጥና ግልጽ የሆነ ሕጋዊ የአሠራር ማዕቀፍ የሌለው መሆኑ፣ በሥርዓቱ የሚስተናገዱ የወንጀል ዓይነቶችና የጊዜ ገደቦች በግልጽ አለመቀመጣቸው፣ እንዲሁም በፌዴራልና በክልል ፍርድ ቤቶች መካከል ተገማችና አንድ ዓይነት አሠራር ባለመኖሩ ተመሳሳይ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች በተለያዩ መንገዶች የሚስተናገዱበት ሁኔታ መፈጠሩን ነው።
በተጨማሪም ይህ አሠራር የተከሳሾችን ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ያጠብባል የሚሉ ቅሬታዎች መበራከታቸው በጥናቱ እንደ ዋና ዋና ችግሮች ተለይተዋል።
ይህ ጥናት በትናንትናው ዕለት ኢንስቲትዩቱ ካቀረባቸው አምስት ጥናቶች ውስጥ አንዱ ሲሆን፣ በተፋጠነ የወንጀል ፍርድ ሂደት ላይ በኢትዮጵያ ህጋዊ መሰረት እና የአተገባበር ማዕቀፍ በሚል ያጠናው ነው።
ጥናቱ በተጠቀሱት ቦታዎች ላይ በተፋጠነ የወንጀል ፍርድ ሂደት ላይ ሕጋዊ ማዕቀፍና የወጥነት እጦት አለበት ብሏል። አክሎም ሂደቱ ወጥ የሆነና ግልጽ የሕግ ማዕቀፍ የሌለው በመሆኑ በፌዴራል እና በክልል ፍርድ ቤቶች መካከል በሚታዩ የወንጀል ዓይነቶችና የጊዜ ገደብ አተረጓጎም ላይ አለመጣጣም ፈጥሯል ብሏል።
እንዲሁም የፍርድ ሂደቱ ከፍትሐዊነት ይልቅ ቅልጥፍና ላይ በማተኮሩ የተከሳሾችን የመስማት፣ የመከላከል፣ የሕግ ጠበቃ የማግኘት እና በዋስ የመፈታት ሕገ-መንግሥታዊ መብቶች ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል ብሏል።
በሂደቱ የሚታዩ ወንጀሎች እንዲሁም መዝገቦች የሚቀርቡበት መስፈርት እና ዓይነት በግልጽ ባለመቀመጣቸው ሂደቱ ለአስገዳጅነት፣ ለግል በቀል፣ ተከሳሾች በዋስትና እንዳይወጡ ለማድረግና ለሙስና አሠራር በር ከፍቷል።
የተፋጠነ የወንጀል ፍርድ ሂደት ቀለል ያሉ ወንጀሎችን ለማስተናገድ ታስቦ የተዘረጋ ቢሆንም፣ በተግባር እንደ ሰው መግደል፣ አስገድዶ መድፈር እና ከባድ የአካል ጉዳት ያሉ ከባድ ወንጀሎችም በዚሁ ሂደት ሲታዩ ተስተውለዋል ብሏል።
በተጨማሪም ግልፅ መመሪያ ባለመኖሩ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 18 ዓመት የሆኑ ወጣቶች እና የአእምሮ ሕመምተኞች በዚህ ሂደት ቀርበዋል።
በዚህ ጥናት ላይ 712 መዝገቦች የታዩ ሲሆን፣ 378 ተከሳሾች በ30 ቀን ውስጥ፣ 476 ጉዳዮች የሚሆኑት ደግሞ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ ማግኘታቸውን ሪፖርቱ ያመለክታል።
አክሎም አጠቃላይ ጥናቱ ከታዩት መዝገቦች 75.6 በመቶ የሚሆኑት ተከሳሾች ያለ ጠበቃ ሂደቱን የተከታተሉ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ደግሞ የራሳቸውን መከላከያ ማስረጃ ማቅረብ የቻሉት ናቸው ተብሏል።
እንዲሁም 10 በመቶ የሚሆኑት መዝገቦች ደግሞ በምስክሮች አለመገኘት፣ በሂደት ውስብስብነት እንዲሁም በጠፉ ተከሳሾች ምክንያት ውሳኔ ለማግኘት ከ1 ዓመት በላይ ፈጅቷል ያለ ሲሆን፤ ይህም ከተፋጠነ የወንጀል ፍርድ ሂደት ይልቅ የመደበኛ የወንጀል ፍርድ ሂደትን ባህሪ እንዲይዝ አድርጎታል ብሏል።
ተመራማሪዎቹ ጥናቱ የቆዩ መረጃዎችን ያካተተ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ አሁናዊ ገጽታን ላይወክል እንደሚችል የጠቆሙ ቢሆንም፣ ሂደቱን ፍትሐዊ ለማድረግ የመዝገብ ልየታ፣ የወንጀል ዓይነቶች እና ወንጀሉ የተፈጸመበት የጊዜ ገደብ ላይ ወጥ የሆነ መመዘኛ እና የሕግ ማዕቀፍ በአስቸኳይ መዘርጋት እንዳለበት አሳስበዋል።
ይህ ጥናት በቆዩ የ2017 ዓ.ም እና ከዚያ በፊት የነበሩ የወንጀል ጉዳዮችን መሰረት በማድረግ በ2018 ዓ.ም የቀረበ ነው።
አዲስ ማለዳ
