መንግስት ከግብር የሚያገኘው ገቢ የቀነሰው ወይም ከሀገር ውስጥ አጠቃላይ ምርት (GDP) ጋር መጣጣም ያልቻለው ነጋዴውና ተቀጣሪው ሰራተኛ በቂ ግብር ስለማይከፍል ነው የሚለው አስተሳሰብ ስህተት እንደነበረ በተደጋጋሚ ጽፊያለሁ።
ለገቢ ግብር መቀነስ መንስኤው በብቸኝነት ግብር ከፋዮች በቂ ግብር አመክፈላቸው ወይም አለመፈለጋቸው እንዳልነበር ሰሞኑን በርካታ የገቢዎችና የጉምሩክ ሰራተኞች በከፍተኛ ሙስና ተጠርጥረው መታሰራቸው በቂ ገላጭ ነው።
የገቢዎችና የጉምሩክ ሙሰኞች በገሃድ ሲያካሂዱት የነበረው በግማሽ ቀንሼልህ 60% ለኔ 40% ለመንግስት አስገባ በሚል የትርፍ ግብርና ተእታ ሳይከፈልባቸው ወይም በድርድር ዝቅተኛ ግብርና ተእታ ተከፍሎባቸው ሀገር ውስጥ እንዲገቡ የሚያመቻቿቸው ሸቀጦችና አቅርቦቶች ለቸርቻሪው ሲተላለፉ የተእታ ደረሰኝ ሳይቆረጥባቸው መሸጣቸው ዋነኛው ፈተና እንደሆነ ጸሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው።
እነዚህ አካላት የመንግስት ገቢ ላይ የሚፈጠረውን ጫና ለማካካስ ሲሉ ከፍተኛ የግብር ክፍያ በሕጋዊ ነጋዴው ላይ በመጫን ሲፈጽሙት የነበረው ግፍ በአንድ በኩል ህጋዊ ነጋዴውን ለምሬትና ለኪሳራ በመዳረግ ሕዝቡን ለከፍተኛ የኑሮ ውድነት ያጋለጠ ከመሆኑም በላይ በተቃራኒው መንግስት በነጋዴውና በግብር ከፋዩ ላይ የተዛባ አቋምና አመለካከት እንዲይዝ ያደረገ ነው።
ቢዘገይም ዛሬ ላይ መንግስት አብዛኛው ነጋዴ ለሕጋዊ ትርፍ፣ በሕጋዊ መንገድ፣ ሕጋዊ ግብር መክፈል አይፈልግም የሚለውን ዘመናት የዘለቀና መፍትሔ ማምጣት ያልቻለው ትርክት የግብር ስርዓቱን ያወሳሰበና ከሀገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት (GDP) ጋር የሚጣጣም ግብር እንዳይሰበሰብ እንቅፋት መሆኑን “ተረድቶ” ችግሩን ከምንጩ ለመታገል እንቅፋት የሆኑ ሙሰኛ የገቢና የጉምሩክ ሰራተኞች ያጎለበቱትን “የመደራደር አቅም” ለመስበር ጓዳውን መፈተሹ ተገቢ ጅምር ነው የሚል እምነት አለኝ።
በዚሁ ልክ መንግስት ነጋዴውን ለሙስና ለማመቻቸት አቅደው የሚንቀሳቀሱና በጥቅም ሰንሰለት የተሳሰሩ የገቢዎች፣ የጉምሩክ፣ የፍትሕና የጸጥታ አስፈጻሚ አካላት በሚሰጡት የተዛባ መረጃና የተሳሳተ ትንታኔ ላይ ብቻ ተመስርቶ ነጋዴውንና ግብር ከፋዩን በማሸማቀቅ ወደ ሙሰኞች እቅፍ መግፋቱን ደጋግሞ ሊመረምረው የሚገባ ነገር እንደሆነም መጠቆም አፈልጋለሁ።
ሙሰኞችን የመታገሉ ዘመቻም ወሳኝ ለውጥ የሚያመጣው ጅምሩ አባይን በጭልፋ መሆኑን በመረዳት ሐይማኖት፣ ዘር፣ የፖለቲካ ዝንባሌንና ማንነትን ሳይመርጥ ምርመራው በሁሉም አካላት ላይ በሕቡዕና በገሃድ ተጠናክሮ ሲቀጥል ብቻ መሆኑን መንግስት አበክሮ ሊያሰመርበት እንደሚገባም ደጋግሜ ማሳሰብ አፈልጋለሁ
የአዲስ አበባ መስተዳድርም ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የወረዳና የክፍለ ከተማ ገቢ ሰራተኞቹን የአኗኗር ዘይቤና ከገቢያቸው በላይ ሃብት የማከማቸት ዝንባሌ በስውርና በጥልቀት መመርመርና እርምጃ መውሰድ መጀመር አለበት።
ለገቢ ግብር መቀነስ ሚስጥሩም ሆነ መፍትሔው የሚገኘው አብዛኛው ነጋዴ ጋር ሳይሆን እዛው በየወረዳውና በየክፍለ ከተማው በሚገኙ አስፈጻሚዎች ኪስ ውስጥ መሆኑን መቀበል ያስፈልጋል።
ከዚህ በተጨማሪ አጽንኦት ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ በተዛባ የንግድና የግብይት ስርዓት ላይ ተመስርቶ መንግስት የማስፈጸም አቅም ስላለው ብቻ በተጽእኖ ገቢውን ማሳደግ መቻሉንና ነጋዴውም በዚህ ጥልፍልፍ ሰበብ በሙሰኞች እጅ የተቀጣውን ጉቦ ሸማቹ ማህበረሰብ ጫንቃ ላይ በመጣል የሕዝብን ኑሮ እያናጉት ኑሮውን እያስወዱበት መሆኑን መረዳት ተገቢ ነው።
በጥቅሉ መንግስት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነገር ከግብር ጋር የተያያዘ ሙስና ከመንግስት ገቢ መቀነስ በላይ የሚያሳድረው አፍራሽ ተጽእኖ ነጋዴው ማህበረሰብ የመስራት አቅሙን አሟጦ ስራ ላይ እንዳያውል፣ የመፍጠር ክህሎቱን እንዳያዳብር፣ ሃብት የማፍራት፣ የስራ እድል የመፍጠር አቅሙን እንዳያጎለብት፣ ጊዜውንና አዕምሮውን በአግባቡ እንደይጠቀም ማድረጉ በገንዘብ ሊገመት የማይችል ሰፊ ሀገራዊ ኪሳራ መሆኑ ነው።
በመጨረሻም ሊነሳ የሚገባው ነገር ሙስናና ሙሰኞችን የሚታደጋቸው ተደጋጋፊ የሙስና ሰንሰለት መስፋፋቱ ወደፊትም ተጨማሪ ሙሰኞች ይበልጥ ተጠናክረው እንዲጎለብቱ ወሳኝ ሚና ስለሚጫወት ከዚህ ቀደም በሙስና ተጠርጥረው የታሰሩ ሙሰኞች የት ደረሱ የሚለው ጥያቄ መልስ ሊያገኝ ይገባል ?! ከፍትሕ ስርዓቱ ውሳኔ ባሻገር “Shaming and Naming ትርጉም እንዲኖረው የሙሰኞች የክስ ሂደትም በመገናኛ ብዙሃን በግልጽ መተላለፍ መጀመር አለበት።
ከአቶ ሙሼ ሰሙ
