ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከስፖርታዊ ውድድርነት ባለፈ የሀገርን ገጽታ ከፍ ከማድረግ፣ የሕዝብ ጤናን ከማበረታታት፣ ቱሪዝምን ከማስተዋወቅና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን ከማነቃቃት አንጻር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑ ይታወቃል።
በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ተሳታፊዎችን የሚያሳትፈው ይህ ውድድር 26ኛው ዙር ኅዳር 12 እና 13 ቀን 2019 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ተገልጿል።
በውድድሩ እስከ 60 ሺህ የሚደርሱ ተሳታፊዎች ይገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የሽያጭ እና የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ሕሊና ንጉሤ ገልጸዋል።
የዘንድሮውን ውድድር ልዩ ከሚያደርጉት ጉዳዮች መካከል ለመጀመሪያ ጊዜ የቺፕ የጊዜ መቁጠሪያ ቴክኖሎጂን መጠቀማቸው መሆኑን እና ይህም በውድድሩ የሚሳተፉ ሯጮች ይፋዊ የሩጫ ሰዓታቸውን እንዲያውቁ የሚያግዝ መሆኑን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም ዕድሜያቸው 17 እና 18 ዓመት የሆኑ፣ ከ20 ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ 3 ሺህ ታዳጊዎች የሚሳተፉበት ልዩ መርሐ ግብር ማዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል።
ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በተለይም መዲናዋን ከማስተዋወቅ አንጻር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑ ተገልጿል።
