ኢትዮጵያ በዓመት ከሚያስፈልጋት 1.1 ሚሊዮን ዩኒት ደም ውስጥ 476 ሺሕ ዩኒት ያህሉን ብቻ እየሰበሰበች መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት (EBTBS) ከዓለም አቀፉ የጤና ተቋም አቦት (Abbott) ጋር በመተባበር የደም ዕጥረትን ለመቅረፍና ወጣቶችን በበጎ ፈቃድ ደም ለመለገስ ለማነሳሳት ያለመውን “The Human Chain” የተሰኘ አገር አቀፍ ዘመቻ ዛሬ በይፋ አስጀምሯል።
ዘመቻው በአዲስ አበባ፣ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት ፊት ለፊት በሚገኘው የመነሻ ምድር (Land of Origin) ሐውልት አካባቢ በደም ልገሳ ሥነ-ሥርዓት የተጀመረ ሲሆን፣ ስለ ደም ልገሳ ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን በማስወገድ ቋሚ የበጎ ፈቃድ ደም ለጋሾችን ለማፍራት ያለመ ነው።
በዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት መሠረት ኢትዮጵያ በዓመት 1.1 ሚሊዮን ዩኒት ደም ያስፈልጋታል። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት እየተሰበሰበ ያለው 476 ሺሕ ዩኒት ገደማ፣ ከጠቅላላ ፍላጎቱ 43.1 በመቶው ብቻ ነው።
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው እንዳብራሩት፣ ከሚሰበሰበው ደም 99 በመቶው በበጎ ፈቃደኞች የሚለገስ መሆኑ አበረታች ቢሆንም፣ ከሚያስፈልገው የደም መጠን ግማሽ ያህሉን እንኳን ማሟላት አልተቻለም።
መስፈርቱን የሚያሟሉ ወጣቶች በዓመት ሦስት ጊዜ ደም በመለገስ የደም እጥረቱን ለመቅረፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚችሉም ዋና ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።
