ዶ/ር ሰይፈሥላሴ አያሌው
(የእናት ፓርቲ ፕሬዝዳንት)
ዶ/ር ሰይፈሥላሴ አያሌው የእናት ፓርቲ ፕሬዚደንት ናቸው። አገር አቀፍ ፓርቲያቸው የተመሠረተው በስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ ዋዜማ ቢኾንም፣ በምርጫው ግን ከብልፅግና ኢዜማ ፓርቲዎች ቀጥሎ 600 ዕጩ ተወዳዳሪዎችን በማቅረብ ሦስተኛው ትልቁ ፓርቲ መኾን የቻለ ነበር። እናት ፓርቲ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚከናወኑ እና በሚፈጸሙ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ኹነቶችም ዙርያ ለሕዝብ እና ለመንግሥት ተገቢውን መግለጫና ጥያቄ በማቅረብ ኃላፊነቱን ለመወጣት በመጣር ላይ የሚገኝ ድርጅት ነው፡፡ በዛሬው ቆይታችንም ከፍ ብለን የጠቀስናቸውን የፓርቲውን ፕሬዝዳንት በአጠቃላዩ የሀገራችን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ዙርያ የፓርቲያቸውን ትግል እና በግል ሕይወትና ሥራቸው ዙርያ ተከታዩን ቃለ ምልልስ አድርገንላቸዋል፡፡ መልካም ቆይታ!
ግዮን፡- ዶ/ር ሰይፈሥላሴ ማን ናቸው የሚለውን ለአንባብያን በመግለጽ ብንጀምር?
ዶ/ር ሰይፈሥላሴ፡- ዶ/ር ሰይፈሥላሴ አያሌው እባላለሁ፡፡ የእናት ፓርቲ ፕሬዝዳንት ነኝ፡፡ በትምህርት ዝግጅቴ ኦኮኖሚክስ አጥንቻሁ፡፡ በኢኮኖሚክስ የማስተርስ ድግሪ አለኝ፡፡ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነኝ፡፡ ያለፉትን 30 ዓመታት በሥራ ላይ ተሰማርቼ እገኛለሁ፡፡ በቀድሞ ሶቪየት ኅብረት ሞስኮ ነው የተማርኩት፤ ዶክትሬት ዲግሪዬን የጨረስኩት በ27 ዓመቴ ነው፡፡ ትምህርቴን ጨርሼ ከመጣሁ በኋላ ለአንድ ዓመት ተኩል ሥራ ፈትቼ ነበር፡፡ የዛሬ 30 ዓመት PhD ያላቸው ሰዎች በጣም ውስን ነበሩ፤ ወቅቱ ህወሓት ሥልጣን የተቆጣጠረበት ጊዜ በመኾኑ የሥራ ቅጥር አልነበረም፡፡ በዚያም ምክንያት ያለስራ ቆየሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ግን ረዘም ላሉ ዓመታት በከፍተኛ የመንግሥት ተቋማት አገልግያለሁ፡፡ በአንድ የግል ትልቅ ድርጅት ውስጥም ምክትል ፕሬዝዳንት ሆኜ ለሦስት ዓመታት ሰርቻለሁ፡፡
ከዚያ በመቀጠል 2003 ዓ.ም ላይ የራሴን ድርጅት አቋቁሜያለሁ፡፡ ድርጅቴ በዋናነት ትኩረት አድርጎ የሚሠራው የኢትዮጵያ ናቪጌሽን ሳተላይት ሲስተም ላይ ነው፡፡ ድርጅታችን ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይኾን አፍሪካ ውስጥም በመሥራት ብቸኛው ድርጅት ነው፡፡ “መሪ” የሚባል የኢትዮጵያ ናቪጌሽን ሳተላይት ሲስተም አበልጽገናል፡፡ ከዓመታት በፊትም ሥራ ላይ አውለናል፡፡ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ደግሞ በአፕሊኬሸን መልክ የሠራነው ሲስተም በጣም በዘመነ መልኩ ነው፡፡ የሀገራችንን ነባራዊ ሁኔታ ግንዛቤ ውስጥ አስገብተን ችግሮችን በመፍታት ላይ የሚሠራ ድርጅት ነው፡፡
ግዮን፡- ወደፖለቲካው የተቀላቀሉት የእናት ፓርቲ ምሥረታን ተከትሎ ነው? ወይስ ከዚያ በፊትም ተሳትፎ ነበርዎት?
ዶ/ር ሰይፈሥላሴ፡- ከእናት ፓርቲ በፊት ምንም ዓይነት የፖለቲካ ተሳትፎ አልነበረኝም፡፡ የየትኛውም የፖለቲካ ፓርቲም አባል አልነበርኩም፡፡
ግዮን፡- እናት ፓርቲን ለመመሥረት ምን አነሳሳዎት?
ዶ/ር ሰይፈሥላሴ፡- ከእናት ፓርቲ መሥራቾች ውስጥ አንዱ ነኝ፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ያራመደችው የጎሳ ፖለቲካ ነው፡፡ የህወሓት መንግሥት ሀገራችንን በእኛና በእነሱ ከፋፍሎ እጅግ ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ በነገራችን ላይ ኢትዮጵያውያን በእኛና በእነሱ የተከፋፈልነው ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡ ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ ህወሓት ሥልጣን እስከያዘበት 1983 ድረስ የጨቋኝ ተጨቋኝ መደብ ክፍፍል ነበር፡፡ በዚህም በመደብ ተከፋፍለን አንዳችን ካንዳችን ስንጠፋፋ ቆይተናል፡፡ በሌላ በኩል በነጭና ቀይ ሽብር ክፍፍልም እንዲሁ ተጋድለናል፡፡ እነዚህ ክፍፍሎች በደርግ ዘመን ከፍተኛ ዋጋ አስከፍለውናል፡፡ በምንም ዓይነት መልኩ ልንተካቸው የማንችላቸው ውድ እንቁ ዜጎቻችንን አጥተናቸዋል፡፡
በንጉሡ ዘመን የነበሩ ባለሟሎች ሚኒስትሮች ጨምሮ ቁጥር ስፍር የሌላቸውን ወገኖች አጥተናቸዋል፡፡ በመገዳደል አዙሪት ውስጥ 17 ዓመት ዘልቀናል፡፡ ህወሓት ሥልጣን ከያዘ በኋላ ደግሞ የጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት መልኩን ቀይሮ ሊቀጥል ችሏል፡፡ ያኔ የመደብ ጭቆና የነበረው በህወሓት ጊዜ ደግሞ የብሔር ጭቆና የሚል ስያሜ ተሰጠው፡፡ ‹‹ጨቋኝ ጎሳ ፣ ጨቋኝ ብሔር›› በሚል ለ34 ዓመታት ኢትዮጵያውያን በመከፋፈል አባዜ ውስጥ ቆየን፡፡ እኔም ይህን የመጠፋፋት አባዜ ማቆም አለብን በሚል ወደ ፖለቲካው ዓለም ገባሁ፡፡ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጎሳን ልዩ መሠረት ያደረጉ በመኾናቸው ከዚህ የተለየ ፓርቲ መመሥረት እንደሚያስፈልግም ተገነዘብሁ፡፡
ግዮን፡- ፓርቲያችሁ ከተመሠረተ ስንት ዓመት ሞላው? ለምንስ እናት ፓርቲ ተባለ?
ዶ/ር ሰይፈሥላሴ፡- እናት ፓርቲ የተመሠረተው 6ኛው ምርጫ ሲጀመር አንድ ዓመት ተኩል ሲቀረው ነው፡፡ እንደ አጋጣሚ የኮቪድ 19 ከመምጣቱ አስቀድሞ ነበር የመሥራች ጉባኤ አድርግን ስያሜውን ያወጣነው፡፡ መነሻችንም ከተለያዩ ነገሮች አንጻር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን እናት ነች ፤ ከ80 በላይ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች እናት ነች፡፡ ከ120 ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ ዜጎች እናት ናት፡፡ የተለያየ እምነት የሚከተሉ ዜጎችም እንዲሁ እናት ናት፡፡ ልጆች የተለያየ ባሕል ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ይህንን ሁሉ ባሕሪ አቻችላ የምታኖር እናት ነች ፤ ኢትዮጵያ፡፡ ከዚህ በመነሳት ነው ፓርቲያችን ‹‹እናት›› ብለን የሰየምነው፡፡
ግዮን፡- ፓርቲያችሁ ከተቋቋመ ከዓመታት በኋላ ዛሬ ላይ ማሳካት ከፈለጋቸው ዓላማዎች አንጻር ምን ደረጃ ላይ ደርሷል ሊባል ይችላል?
ዶ/ር ሰይፈሥላሴ፡- የፓርቲ ፖለቲካ በአንድ ጀምበር የሚሠራ ነገር አይደለም፡፡ የፓርቲ ፖለቲካ የራሱ አካሄድ አለው፡፡ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለመለወጥ ዓላማ ይዘን ነው የምንቀሳቀሰው፡፡ ከዚህ አንጻር ብዙ ስኬታማ ሥራ ሠርተናል፡፡ በዚህ ወቅት እንደ ፓርቲ ችግሮችን ተቋቁሞ መቆም በራሱ አንድ ስኬት ነው፡፡ ስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የተካሄደው ፓርቲያችን እውቅና አግኝቶ ስድስት ወር ሳይሞላው ነው፡፡ በኮቪድ19 ወቅት መሰብሰብ አይቻልም ነበር ፤ ስለዚህ እኛ ከአባሎቻችን ጋር በበይነ መረብ እንገናኝ ነበር፡፡ እውቅና እንዳገኘን እጩዎቻችን ምዝገባ ጀመረን ፤ በከፍተኛ ሁኔታ ተንቀሳቅሰን ከገዢው ብልጽግና ፓርቲና ኢዜማ ቀጥሎ ሦስተኛ ደረጃ የያዝን በርካታ እጩዎችን ያስመዘገብን ፓርቲ ነን፡፡ ይህ ለእኛ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ በምርጫ ሂደቱ ውስጥም ከፍተኛ ድምጽ ነበረን፡፡ ከአባሎቻችን ጋር በበይነ መረብ እንገናኝ ነበር፡፡ እውቅና እንዳገኘን የእጩዎቻችንን ምዝገባ ጀመርን፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ ተንቀሳቅሰን ከገዢው ብልጽግና ፓርቲና ኢዜማ ቀጥሎ በርካከታ እጩዎችን ያስመዘገብን ፓርቲ ለመኾን ቻልን፡፡ ይህ ለእኛ ትልቅ ስኬት ነው፡፡ በምርጫውም ከፍተኛ ድምጽ ነበርን፡፡
ሥርዓቱ የአብላጫ ምርጫ ስለሆነ ነው እንጂ ብዙ ቁጥር ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እጩ ይኖረን ነበር፡፡ የሀገራችን የምርጫ ሥርዓት ግን ይህን አይፈቅድም፡፡ እኛም ይህ ባለመሆኑ አናዝንም፡፡ ምክንያቱም እኛ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ ገና ጅምሩና ውልደቱ ላይ ነው ያለነው፡፡ ረጅም ጊዜ የፖለቲካ ሜዳው ላይ ከቆዩ ፓርቲዎች እኩል ተአምራዊ ለውጥ አንጠብቅም ነበር፡፡ ነገር ግን የገባንበት ፖለቲካ፣ ትግል ሰላማዊ በመሆኑ ጥሩ ነገር አስተምሮን አልፏል፡፡
ግዮን፡- ፓርቲያችሁ ለክልልም ይሁን ለፌደራል ምክር ቤት አንድም ተመራጭ አልነበረውም ማለት ነው?
ዶ/ር ሰይፈሥላሴ፡- ምርጫው የተጭበረበረባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ እዚያ ቦታ የተካሄደው ምርጫ እንዲደገም ቢወሰንም አካባቢው ጦርነት ውስጥ በመሆኑ ያን ማድረግ አልተቻለም፡፡ በጥቅሉ የተወካዮች ምክር ቤት የገባ አባል የለንም፡፡ ለምክር ቤት ያለፈ አባል ባይኖረንም አጣነው ወይም ጎደለን የምንለው ነገር የለም፡፡ እንደ ፖለቲካ ፓርቲ በሕዝብ ዘንድ ጥሩ ተቀባይነት ያለው ፓርቲ ማቋቋም ችለናል፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ እናት ፓርቲ በሕዝቡ ዘንድ ትልቅ ቅቡልነት ያለውና የሕዝብ ድምጽ የሆነ ፓርቲ ነው፡፡
ግዮን፡- ከምርጫው በኋላ ገዢው ፓርቲ ለተለያዩ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ሥልጣን ሰጥቶ ነበር፡፡ እናንተስ በመንግሥት ሥልጣን ላይ ያለ አመራር ወይም አባል አላችሁ? የሥልጣን ጥያቄ ቀርቦላችሁ ነበር?
ዶ/ር ሰይፈሥላሴ፡- መንግሥት ሥልጣን ሊሰጠን ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ መንግሥት ይህን ጥያቄ ባቀረበበት ጊዜ ያልተለመደናአዲስ በመሆኑ ግር ብሎን ነበር፡፡ የመጣንበት ፖለቲካ የእኛና የእነሱ በመሆኑ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበርንም፡፡ ቀደም ብሎም ፓርቲያችን እንዲህ ዓይነቱ ጥያቄን ተወያይቶበታል፡፡ በውይይታችን መሠረትም የመንግሥት ሚኒስተር ዴኤታ ኾነው የሚያገለግሉ የፓርቲያችን አመራር አሉ፡፡
ግዮን፡- መንግሥት ፓርቲዎችን ከተቃዋሚ ይልቅ ተፎካካሪ ብሎ መጥራት ይፈልጋል፡፡ እናንተ መጠሪያው አግባብ ነው ትላላችሁ?
ዶ/ር ሰይፈሥላሴ፡- ተፎካካሪ የሚለው ቃል አዲስ እሳቤ ነው፡፡ በመሠረታዊነት እኛ ከመንግሥት ፖሊሲ ጋር ቢስማማ ኖሮ የራሳችን የፖለቲካ ድርጅት አያስፈልገንም ነበር፡፡ ከብልጽግና ጋር ተዳብለን መቀጠል እንችል ነበር፡፡ በዋናነት መፎካከር ሳይሆን የምንቃወመው ነገር አለ፡፡ ኢትዮጵያ የምትከተለውን ፖለቲካ በመሠረታዊነት እንቃወማለን፡፡ እየተፎካከርን ሳይሆን እየተቃወምን ነው፡፡ ፕሮገራማችንም ማኒፌስቷችንም ፖሊሲዎቻችንም ከመንግሥት ተቃራኒ ናቸው፡፡ ይሄ መንግሥት ላለፉት 30 ዓመታት የጎሳ ፖለቲካ ነው የሚያራምደው፡፡ እኛ ደግሞ ከዚህ በተቃራኒ ነው የምናስበው፡፡ ለኢትዮጵያ፣ የጎሳ ፖለቲካ ጥፋት፣ ሞትና ስደት ነው ብለን እናምናለን፡፡ ስለዚህ ፈጽሞ ፉክክር ሳይሆን ተቃወሞ ነው ያለን፡፡
ግዮን፡- የምክክር ኮሚሽኑ ላይ አንሳተፍም ያላችሁት ለምንድን ነው?
ዶ/ር ሰይፈሥላሴ፡- ኢትዮጵያ ላለፉት 50 ዓመታት የጨቋኝ ተጨቋኝ ሐሰተኛ ትርክት ሲራመድባት የነበረች ሀገር ናት፡፡ እነዚህን ነገሮች ማጥራት ያስፈልጋል፡፡ ልዩነታችንን ያከበረ የጋራ ስምምነት መፍጠር ይኖርብናል፡፡ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በመንግሥት በኩል ወደሥራ ከመግባቱ በፊት በተቃዋሚ ፓርቲዎች ለረጅም ጊዜ እንዲካሄድ ሲጠየቅበት የነበረ ጉዳይ ነው፡፡ ለምሳሌ ከእኛ ፓርቲ ጋር በትብብር የሚሰራው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ከ23 ዓመት በፊት ሀገራዊ ምክክር እንደሚያስፈልግ ሲጠይቅ ነበር፡፡ ስለዚህ ጥያቄው ቅንነት የተላበሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉ በየጊዜው ሲጠይቁት የነበረ ጉዳይ ነው፡፡
ከምርጫው አስቀድሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፎረም ነበረን፡፡ ይህን ጉዳይ በተመለከተም የአጭርና ረጅም ጊዜ እቅድ ይዘን ስንነጋገርበት ነበር፡፡ የአጭር ጊዜ እቅዳችን እንዴት አድርገን ምርጫውን ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንደምናስኬደው ነበር፡፡ ኢትዮጵያ የምርጫ ታሪኳ በጣም ችግር ያለበት ነው፡፡ ስለዚህ ምርጫን ተከትሎ የአንድ ዜጋ ሕይወት ማለፍ የለበትም የሚል እምነት አለን፡፡ በረጅም ጊዜ እቅዳችን ደግሞ ከምርጫው በኋላ እንዴት ዐይነት ሀገራዊ ምክክር አድርገን ሀገራችንን ካለችበት ሁኔታ እናወጣለን የሚለው ነበር፡፡ የእኛ ተቋም ኢትዮጵያ ከገባችበት ቅርቃር መውጫ መንገዱ ምክክር ብቻ ነው የሚል ነው፡፡
ይህንን ስንል ግን የይስሙላ ምክክር ማለታችን አልነበረም፡፡ እንዲደረግ የምንፈልገው ምክክር ቅንነትን የተላበሰ በሁሉም ዘንድ አመኔታ ያለው፣ ሁሉንም አሳታፊ የሆነውን ነው፡፡ አሁን ያለውን የምክክር ኮሚሽን ስናይ ከእሱ በፊት ‹‹የእርቀ ሰላም ኮሚሽን፣ የወሰንና ማንነት ኮሚሽን›› የሚባሉና ሦስት ዓመት የሠሩ ተቋማት ነበር፡፡ በእርግጥ ምን እንደሠሩ ለሕዝብ ግልጽ አልተደረገም፡፡ አንዳንዴ የሀገራችን ተቋማት ሲፈጠሩም ሆነ ሲከስሙ አይታወቁም፡፡ ለምን ተቋቋሙ? ምን ሰርተው ከሰሙ? የሚለው ሳይታወቅ ከተቋቋሙ በኋላ ይፈርሳሉ፡፡
በአጠቃላይ ብሔራዊ መግባባቱን ከሃያና ሠላሳ ዓመታት በፊት አድርገነው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ከእኛ ጋር የዘለቀው የእርስ በእርስ ግጭትና ቀውስ አይኖርም ነበር፡፡ አሁን ያለው የምክክር ኮሚሽን ላይ እንደ እናት ፓርቲ ከመነሻው ጀምሮ አካሄዱ ላይ የራሳችን ጥያቄ ነበረን፡፡ ኮሚሽኑ ላይ ከመቋቋሚያ አዋጁ ጀምሮ ጥያቄ ነበረን፡፡ ሆኖም ግን እንደምንም ጠጋግነን አብረን እንጓዝ ብለው ከኮሚሽኑ ጋር አብረው ከሠሩት ፓርቲዎች ውስጥ እናት ፓርቲ አንደኛው ነበር፡፡ ያም ኾኖ ግን ከማቋቋሚያ ዐዋጁ በተጨማሪ የኮሚሽኖች ምርጫም ላይ የራሳችን ጥያቄ ነበረን፡፡ ጥያቄያችንንም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቅርበን ነበር፡፡ ነገር ግን ምንም መልስ አልነበረንም፡፡ ጥያቄያችን ሕዝብ የጠቆማቸው ሰዎች ይፋ መደረግ አለባቸው የሚል ነበር፡፡ እያንዳንዱ እጩ ኮሚሽነር በስንት ሰው እንደተጠቆመ ለሕዝብ መገለፅ ነበረበት፡፡ ግልጽነት መኖር ነበረበት፡፡ እጩ አቀራረብም ላይ ቅሬታ ነበረን፡፡ በእጩ መረጣ ሂደት ውስጥ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዳይሳተፉ ተደርጓል፡፡ በጥሪ ሂደታቸው ሁሉንም አላካተቱም፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ እውቅና እስካላቸው ድረስ ሁሉም እኩል ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ የተወካዮች ምክር ቤት በመጨረሻ ሁሉም ፓርቲዎች እንዲሳተፉ አደረገ፡፡ ነገር ግን ሁሉም እድል አላገኙም ነበር፡፡ እኛ ሀገራዊ ምክክሩን ምክንያት ፈጥረን ትተን መውጣት አልፈለግንም፡፡ ነገር ግን ሀገሪቱ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ እና በእርስ በእርስ ጦርነት እየታመሰች በርካቶች የሕሊና እስረኞች ኾነው፣ የይስሙላ ምክክር እንዲደረግ አንፈልግም፡፡ ምክክሩ የሚከናወነውም በኢትዮጵያ ገበሬ መሐል ሳይኾን በሊኂቁ በኩል ነው፡፡
እኛ እንደ እናት ፓርቲ ለምክክር ሊቀርቡ የሚገባቸውን አጀንዳዎች ሰጠን፡፡ በየክልሎችም አጀንዳ ልታየው ተከናወነ፡፡ አሁን ላይ አማራ ክልል ሙሉ ለሙሉ ጦርነት ላይ ባለበት ሁኔታ ኮሚሽኑ የአጀንዳ ልየታ እያካሄደ ነው፡፡ ፓርቲያችንን ተወካይ ላኩ ብሎ ቢጠይቅም በዚህ የጦርነት ሁኔታ ውስጥ ምንም ሊከናወን ስለማይችል አባሎቻችንን አላክንም፡፡ በዚህም እራሳችንን ከሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ አግልለናል፡፡ የሀገሪቱን 2/3ኛ ሕዝብ ያላካተተ ሀገራዊ ምክክር ተቀባይነት የለውም፡፡
ግዮን፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቱ ያለበት ሁኔታስ ምንድንው?
ዶ/ር ሰይፈሥላሴ፡- የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ፓርቲዎች እርስ በእርስ እንዲነጋገሩበት የተፈጠረ የመቀራረቢያ መድረካችን ነው፡፡ ነገር ግን ፓርቲዎች በነፃነት እየተንቀሳቀሱ ነው ማለት አይቻልም፡፡ እኛ በሐሳብ የምናምን ሰላማዊ ታጋዮች ብንኾንም በመንግሥት በኩል ቀናነት አይታይም፡፡ በተለያየ ጊዜ አባሎቻችን ይታሠራሉ፡፡ ቅርብ ጊዜ በአርባ ምንጭ 3 አመራሮቻችንን ባልታወቀ ምክንያት አስረውብን ነበር፡፡ በስንት ጩኽትና ከዚያም ባለፈ ደብዳቤ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጽፈን ነው የተፈቱልን፡፡ የጠቅላላ ጉባኤ አመራራችንም ለሰባት ወራት ታስረውብናል፡፡ ካለ ሕግ በአዋሽ አርባ ታስረው አካልን ነፃ የማውጣት ክስ ከፍተን ነው የተፈታልን፡፡ አሁን ላይ ግን የታሠሩ አባላት የሉንም፡፡
ግዮን፡- የአባላት ብዛታችሁ ምን ያህል ነው፡፡ ምን ያህል ከተሞችስ ውስጥ ጽ/ቤት አላችሁ?
ዶ/ር ሰይፈሥላሴ፡- በመላው ኢትዮጵያ እንንቀሳቀሳለን፡፡ የአባሎቻችን ቁጥር ይህን ያህል ማለት ባይችልም በሚሊዮን የሚቆጠር አባል አለን፡፡ በርካታ ከተሞችም ውስጥ በርካታ ቢሮዎች አሉን፡፡
ግዮን፡- አሁን ያሉ ፓርቲዎች ከመግለጫ የዘለለ ነገር አያደርጉም በማለት የሚነቅፉ ወገኖች አሉ፡፡ የእናንተ መልስ ምንድነው?
ዶ/ር ሰይፈሥላሴ፡- ሀገራችን ትክክለኛ ሁኔታ ውስጥ ስላልኾነች የተለያዩ ችግሮች ሲከሰቱ የተለያዩ መግለጫዎችን እናወጣለን፡፡ ከዚያ ባለፈም የተለያዩ ምክረሐሳቦችን ለመንግሥት በመስጠት ለመታገል እንሞክራለን፡፡ ስብሰባና ሰልፍ ለማድረግ ግን የግድ ፈቃድ ያስፈልገናል፡፡ እንደሚታወቀው ባለፈው ጊዜ ‹‹ጦርነት ይብቃ›› የሚል ሰልፍ ለማከናወን የሞክሩ ታላላቅ ሰዎች ለእስር ተዳርገዋል፡፡
ግዮን፡- እንደ ፖለቲካ ፓርቲነታችሁ ከኤምባሲዎችና ከዲፕሎማቶች ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?
ዶ/ር ሰይፈሥላሴ፡- እንደ ሀገር አቀፍ ፓርቲነታችን እኛ ጥረት እናደርጋለን፡፡ ነገር ግን ሁሉም ኤምባሲ የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት ያንኳኳል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉ ኤምባሲዎች በሙሉ ያውቁናል፡፡ በሚፈልጉ ወቅትም ያነጋግሩናል፡፡ እኛም በምንፈልግበት ጊዜ ቢሯቸው ድረስ አንኳኩተን የገባንበት ጊዜ አለ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ስለሀገራችን ያለንን የራሳችንን እይታ እንገልጽላቸዋለን፡፡ በኤምባሲው ውስጥ ከሚሰሩ የፖለቲካ ዲፕሎማቶችም ጋር የቅርብ ግንኙነት አለን፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ ከተለያዩ ሀገራት ልዑካን ሲመጡና የፖለቲካ ፓርቲዎችን እይታ በሚፈልጉበት ጊዜ ኤምባሲዎቻቸው ደውለውልን እንገናኛለን፡፡
ግዮን፡- እናት ፓርቲ አሁን ከተቀናጃቸው ፓርቲዎች በተጨማሪ ከሌሎች ፓርቲዎችም ጋር በጋራ የሚሠራበት ሁኔታ አለ?
ዶ/ር ሰይፈሥላሴ፡- አዎ አለ፤ ከመኢአድ ጋር ብቻ አይደለም እየሠራን ያለነው፡፡ እናት ፓርቲ ብቻውን ሮጦ ሀገርን ከዝቅጠት ያወጣል የሚል እምነት የለንም፡፡ ፓርቲያችን አሁን ባለበት ሁኔታ ትልቅ ቅቡልነት አለው፡፡ ፓርቲያችንም የዜጎች ድምፅ ለመኾን ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል፡፡ ይህም ኾኖ የምናምነው ‹‹አንድነት ኃይል ነው›› ብለን ስለኾነ ከሌሎች ጋር ለመሥራት እንጥራለን፡፡ ከምርጫ በፊትም እንደተቋቋምን ከሌሎች ፓርቲዎችም ጋር በጋራ ለመሥራት ሞክረናል፡፡ በዚህም ለሁሉም ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ‹‹በጋራ እንሥራ›› የሚል ደብዳቤ ጽፈን ጠይቀናል፡፡ ብዙዎች በየግል መሮጥን መርዋል፡፡ ኾኖም ሁለቱ ግን ፈቃደኛ ኾነው ከእኛ ጋር ሦስት በመኾን የመግባቢያ ሰነድ ፈርመን በጋራ እየሠራን ነበር፡፡ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም ለማራመድ ተስማምተን ስንሠራ ነበር፡፡ ቆይቶ ግን ይህን ያዩ ሌሎች ሁለት ፓርቲዎችም ማመልከቻ አስገብተው በጋራ ስንሠራ ቆየን፡፡ አሁን ለጊዜው ግን አንዱ ፓርቲ ከምርጫ ቦርድ ጋር ባለው ችግር ምክንያት ከእኛ ጋር የለም፡፡ አሁን አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ እየሠራን ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በየግላቸው ታግለው አሸናፊ ለመኾን ይቸገራሉ፡፡ የተቃዋሚዎች መከፋፈል የሚጠቅመው ለመንግሥት ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ መበታተን ለገዢው ፓርቲ ምቹ ሁኔታን ይፈጥርለታል፡፡
ግዮን፡- ለመጪው ምርጫ ያላችሁ ዝግጁነት ምን ይመስላል?
ዶ/ር ሰይፈሥላሴ፡- ሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወደ አንድ የምንመጣበት መንገድ ላይ እየሠራን እንገኛለን፡፡ በየግላችን ወደ ምርጫ አንሄድም ብለን እናምናለን፡፡ በቀጣዩ ምርጫ የዘውግ ፖለቲካ የማያራምዱ ኢትዮጵያዊ እይታ ያላቸው ፓርቲዎችንም ወደ ራሳችን አምጥተን ጠንካራ ተፎካካሪ ኾነን ለመወጣት እንሠራለን ብዬ አምናለሁ፡፡ ጠንካራ ግንባር ፈጥረን በቀጣዩ ምርጫ ትልቅ ውጤት እናስመዘግባለን ብዬ አስባለሁ፡፡
ግዮን፡- የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን እንዴት ተመለከቱት?
ዶ/ር ሰይፈሥላሴ፡- የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በሁለት መልኩ የሚታይ ነው፡፡ የመጀመሪያው ሀገራችን አሁን አጣብቂኝ ውስጥ ትገኛለች፡፡ የወጭ ገቢ ንግዷ ተዛብቷል፡፡ ማክሮ ኢኮኖሚው ከወጪ ገቢ ንግድ በተጨማሪ የዋጋ ግሽበትን የሚመለከት ነው፡፡ ሥራ አጥነትንም ይመለከታል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ጉዳዮች ሀገር ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብታለች፡፡ የኑሮ ውድነት፣ ሥራ አጥነቱና የዋጋ ግሽበቱ ሀገር መሸከም ከምትችለው በላይ ኾኗል፡፡ ከዚህ ችግር የሚያወጣ ነገር መኖር መቻል አለበት፡፡ የዓለም ገንዘብ ድርጅት የመጨረሻ አበዳሪያችን ኾኗል፡፡ ይህ በመኾኑ ደግሞ ብድር የምንወስደው በቅድመ ሁኔታ ኾኗል፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተጣጣመና ችግራችንን ከመፍታት አኳያ የመጣ ሳይኾን የመጨረሻ አበዳሪ የተባለው አካል ባመጣው ቅድመ ሁኔታ የመጣ ግዴታ ይመስለኛል፡፡ ይሄ ደግሞ ለሀገራችን ችግር መፍትሔ መኾን አይችልም፡፡ ስለዚህ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የመውጫ መንገድ ያስፈልገዋል፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ መቀጠል አይችልም፡፡
ግዮን፡- መንግሥት የተለያዩ ማሻሻያዎችን ሲያወጣ የፖለቲካ ፖርቲዎች የመወያየት ልምድ የላቸውም፡፡ ይኼ ነገር መለመድ የለበትም ይላሉ?
ዶ/ር ሰይፈሥላሴ፡- መለመድ አለበት፡፡ በመጀመያ በዐዋጅና ፖሊሲ ማሻሻያዎች ላይ ለመወያየት የጠለቀ የሕግ እውቀት ያስፈልጋል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥትን ለማስቆም የሚቀርበው ሐሳብ ለሪከርድ ካልተቀመጠ በቀር የመንግሥትን አቋም እንደማያስለውጥ ግልፅ ነው፡፡ የአዋጅቻችን አፀዳደቅ እራሱ ይህን የሚያሳይ ነው፡፡ ይኼ ዛሬ የመጣ ሳይኾን ቀድሞም የነበረ ነው፡፡ ፓርላማው በአንድ ፓርቲ ሰዎች የተሞላ ነው፡፡ ዘጠና ዘጠኝ ፐርሰንት አንድ ፓርቲ የያዘው ፓርላማ ነው ያለን፡፡ ስለዚህ የመጣው ነገር ሁሉ ብዙ የልዩነት ሐሳብን ሳያስተናግድ ይጸድቃል፡፡
ግዮን፡- መወያያ ርዕስ ኾኖ መቅረቡ በራሱ ጥሩ አይደለም ይላሉ?
ዶ/ር ሰይፈሥላሴ፡- እውነት ነው፤ መወያያ መኾን ይኖርበታል፡፡ ነገር ግን ተስፋ በመቁረጥና ውጤት ማምጣት ስላልተቻለ ነው ያልተሠራበት፡፡ የእኛ ተቋም የተገኘበት ቦታ ኹሉ የሚታይ ሥራ ካላከናወነ ሪከርድ ብቻውን ዋጋ የለውም ብሎ ያምናል፡፡ ነገር ግን የሚመጣውን ነገር ሁሉ አይቶና ፈትሾ ታግሎ ማለፍ እንደሚገባም እናምናለን፡፡ ፓርቲያችን ጊዜውን ባልተገባ ሁኔታ እንዳያባክን እንጠነቀቃለን፡፡ ‹‹ነበሩ›› ወይም ‹‹ተሳትፈዋል›› ለመባል ብቻ ስንል የምናደርገው ነገር የለም፡፡
ግዮን፡- አሁን ላይ በሀገራችን እየተከናወን ያለውን የኮሪደር ልማት ፓርቲያችሁ እንዴት ያየዋል?
ዶ/ር ሰይፈሥላሴ፡- እኛ ማንኛውንም ነገር የምንመለከተው ከሕግ አግባብ አኳያ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ፓርቲያችን እየተሄደበት ያለው አግባብ ትክክል አይደለም ብሎ ያምናል፡፡ የመንገድ ዳርቻዎች አሸብርቀው ሊኾን ይችላል፡፡ የተዋበ ነገር ማንም ሰው አይጠላም፡፡ ነገር ግን በምን አግባብ ነው የኾነው የሚለውን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ ባዶ ቦታ ላይ ይህን ዓይነት ነገር ቢሠራ ማንንም ስለማይነካ ይበል የሚያሰኝ ይኾናል፡፡ በኢኮኖሚክስ ‹‹ኦፖርቺኒቲ›› የሚባል ነገር አለ፡፡ ‹‹ገንዘቤን ምን ብሠራበት ይሻላል›› የሚባል ነገር አለ፡፡ ገንዘብ ውስን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቀርቶ አሜሪካ በትልቅ ብድር ነው የምትኖረው፡፡ በብድር የምትኖረው የራሷን ነገር ሙሉ በሙሉ መሸፈን ስለማትችል ነው፡፡
እኛ ደግሞ ያለን ሀብት ውስን ሀብት ነው፡፡ ይህን ውስን ሀብት የትኛው ነገር ላይ ባውለው ይበልጥ እንደ ሀገር ትርፋማ ያደርገናል የሚለውን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ይኼን ማሰብ የሚቻለው ግን የተባለው የውበት ሥራ የሚከናወነው ባዶ መሬት ላይ ቢኾን ነበር፡፡ እኛ ግን ባዶ ሜዳ ላይ አይደለም ይኼን እየሠራን ያለነው፡፡ ለኮሪደር ልማት መሥሪያ ሲባል የሚፈናቀሉ ሰዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች የሀገራችን ዜጎች ናቸው፡፡ ሕገ-መንግሥታዊ ጥበቃ አላቸው፡፡ ንብረታቸው ሕገ-መንግሥታዊ ጥበቃ አለው፡፡ ለሀገር ጥቅም ሲባል ሕገ-መንግሥት ጥሶ ቤት ማፍረስ፣ ሰው ማፈናቀል አይችልም፡፡ እኛ ምንም እንኳን ተቃዋሚ ፓርቲ ብንኾንም ለሀገራችን ሕግ እንገዛለን፡፡ በሕገ መንግሥቱ የመመራት ግዴታ እኛም ላይ ይወድቃል፡፡ መንግሥት ደግሞ ከእኛና ከዜጎች የበለጠ ሕገ-መንግሥቱን የመጠበቅና የማስፈጸም ኃላፊነት አለበት፡፡ ያወጣውን ሕግ ሊያከብር ይገባል፡፡
ለኮሪደር ልማቱ የመጀመሪያ ፈረሳ የተደረገው ፒያሳ ላይ ነበር፡፡ ፒያሳ መፍረስ የነበረበት በዐዋጁ መሠረት ነበር፡፡ አንድ ነገር ላይ እርምጃ ሲወሰድ ቢያንስ ከዓመት በፊት ለሕዝብ መናገር ያስፈልጋል፡፡ ሕዝብን ማወያየት ይገባል፡፡ ሕዝቡም በሐሳቡ መስማማት ይኖርበታል፡፡ ለማስፈፀሚያ የሚኾን በቂ በጀትም ያስፈልጋል፡፡ ሁሉም ነገር ካለቀ በኋላ ነው ወደሥራ መግባት የሚያስፈልገው፡፡ ነገር ግን የኾነው ሌላ ነው፡፡ ሰዎች በሁለትና ሦስት ቀናት ውስጥ ቤታቸውን እንዲያፈርሱ ተደርገዋል፡፡ እኛም እንደተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት የእነዚህ ዜጎች መብት ይመለከተናል፡፡ የዜጎቹ ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸው እየተጣሰ ነው፡፡ ይኼንን የማስከበር ኃላፊነት ነው በግንባር ቀደምነት የመንግሥት ኃላፊነት፡፡ መንግሥት በዘፈቀደ የዜጎችን መብት መሸራረፍ የለበትም፡፡ መንግሥት ራሱ ላወጣው ሕግ የማይገዛ ከኾነ የሕግ የበላይነት ጥያቄ ወስጥ ይገባል፡፡ ከዚህ አኳያ እየሄደበት ያለውና የተሠራው ሥራ ትክክል አይደለም ብለን ስንሞግት ነበር፡፡ ዛሬም እንሞግታለን፡፡
ግዮን፡- ከግል ድርጅትዎ አንፃር ለሀገር ያበረከቱት ነገር ምንድ ነው?
ዶ/ር ሰይፈሥላሴ፡- ‹‹ሳይተላይት ናቪጌሽን ሲስተም››ን በአፍሪካ ውስጥ በብቸኝነት ያበለጸግን ነው፡፡ በነገራችን ላይ በሥራ ላይ በቆየሁበት ጊዜ ውስጥ 1/3ኛ የሥራ ሕይወቴን ያሳለፍኩት በዚህ ላይ ነው፡፡ ለሀገሬ እንደ ባለሙያ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጌያለሁ ብዬ አምናለሁ፡፡ ከቦታ ቦታ የምናደርገውን እንቅስቃሴ ከማዘመን አኳያ ድርጅታችን ከፍ ያለ ሥራ ሠርቷል፡፡ ሥራው በጣም አድካሚና ከፍ ያለ ሀብት የሚጠይቅ ነው፡፡ በአጭር ጊዜ ትርፍ የሚገኝበት አይደለም፡፡ እንደ ሀገር ግን ኢትዮጵያ የሚገባትን እንድታገኝ አድርገናል፡፡ አብዛኛው ሰው ከቦታ ቦታ ለመንቀሳቀስ የሚጠቀመው ጎግል ማፕን ነው፡፡ የእኛ መተግበሪያ ግን አገልግሎት ላይ ካሉ የዘርፉ መተግበሪያዎች ሁሉ እጅግ የላቀ ነው፡፡ በአማርኛና በእንግሊዝኛ የሚሠራ የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ያገናዘበ መተግበሪያ ነው፡፡ መተግበሪያውን የኮምፒውተር ባለሙያዎች 100% ቢሮ ውስጥ ቁጭ ብለው የሚሠሩት ነው፡፡ የእኛ መተግበሪያ መረጃውን ከቦታው ለማሰባሰብ ከ100 ሺህ በላይ ኪሎ ሜትር በመኪና የመንዳት ሥራ አከናውኗል፡፡ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ነው ሥራችንን ያከናወንነው፡፡ ሀገራችን ውስጥ ከጎለበቱ መተግበሪያዎች በጣም የተሻለው መተግበሪያ የኛ ነው ብዬ መናገር እችላለሁ፡፡
ማንኛውም ስማርት ስልክ ያለው ሰው የሚጠቀምበት ነው፡፡ አሁን ላይ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በጋራ እየሠራን ነው፡፡ ኢትዮ-ቴሌኮም ትልቅ አጋራችን ነው፡፡ መተግበሪያው ለዜጎች እንዲደርስ የምናደርገው በቴሌዎች ሲስተም ነው፡፡ ማንኛውም ሰው የሚጠቀመው ነው፡፡ መተግበሪያችን ያለ ዳታ የሚሠራ ነው፡፡ አፑ ከተጫነ በኋላ በክፍያ የሚሠራ መተግበሪያ ነው፡፡ 8253 የሚባል አጭር ቁጥር አለን፣ በዚያ በመመዝገብ ለሦስት ቀን መጠቀም ይቻላል፡፡ ደንበኛው መተግበሪያውን በየቀኑ ሁለት ሁለት ብር እየከፈለ መጠቀም ይችላል፡፡ መተግበሪያው መቶሺህ መዳረሻዎች ያሉት ነው፡፡ ሆቴሎች፣ እንግዳ ማረፊያዎች፣ የሕክምና ተቋማት፣… ሁሉንም መረጃዎች በአንድ ላይ የያዘ ቋት ነው፡፡
ግዮን፡- በመጨረሻም ማስተላለፉ የሚፈልጉት መልዕክት ካለ?
ዶ/ር ሰይፈሥላሴ፡- ኢትዮጵያ ላለፉት 50 ዓመታት ከባድ ጊዜን አሳልፋለች፡፡ ሰዎች በማንነታቸው ተጠቅተዋል ፤ በየዘመኑ የመከራ ስቃይ ወርዶባቸዋል፡፡ የብልጽግና መንግሥት ከመጣ በኋላ እንኳን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለመከራ ተዳርገዋል፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ለዘላለም መከራ አልተፈጠረችም፡፡ ስለዚህ ይህን የመከራ ዘመኗን ለማሳጠር ሁሉም አካል የሚጠበቅበትን ማደረግ ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ችግር ተጠያቂዎቹ ሁላችንም በመኾናችን በጋራ ኃላፊነት ወስደን ካለችበት አረንቋ ልናወጣት ይገባል፡፡ ስለዚህ መጠቋቆሙን አቁመን ወደ መታደጉ መግባት ይኖርብናል፡፡ የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ጥረት ብቻ ሀገራችንን ከችግር ሊያወጣት አይችልም፡፡ ሁላችንም የየራሳችንን ሥራ እንሥራ ማለት እወዳለሁ፡፡ ምክንያም ችግሩ ያለው አዲስ አበባም ውስጥ ከአዲስ አበባ ውጭም ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ጅማ በሄዱበት ጊዜ 15 ሺህ ቤቶች ያለ ካሣ ወደው ፈቅደው እንዳፈረሱ ተናግረዋል፡፡ ሰው ቢፈቅድ እንኳን ሕጉ የሚፈቅድላቸውን መስጠት ያስፈልግ ነበር፡፡ ሰው ከፈለገ የተሰጠውን የካሳ ገንዘብ መልሶ ለመንግሥት ገቢ ያድርግ፡፡ መንግሥት ግን ማድረግ የሚጠበቅበት መፈፀም ነበር፡፡
ግዮን፡- ስለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ሥም ከልብ እናመሠግናለን፡፡
ግዮን መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር 222 የካቲት 8 2017 ዓ.ም
