ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ትላንት ዘሀበሻ ዘገባ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ የማእከላዊ ትግራይ ዞን ፖሊስ ዛሬ እንደገለፀው የተለቀቁት በአዲቋላ ራማ በኩል ነው፡፡
የፖሊስ ኮሚሽነሩ ኮማንደር ፀጋይ አስፍሀ በሰጡት መግለጫ ከተለቀቁት ውስጥ አብዛኛዎቹ ተወልደው ያደጉት በኤርትራ መሆኑን ገልፀው እድሜያቸውም ከ45 አመት በታች መሆኑን አስረድተዋል፡፡ የተወሰኑት ከኤርትራዊያን ጋር ተጋብተው ሀብትና ንብረት ያፈሩ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የኤርትራ መንግስት በርካታ የትግራይ ተወላጆችን አግቶ መውሰዱ በስፋት ሲገለፅ የቆየ ሲሆን ኮማንደር ፀጋይ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት 272 የትግራይ ተወላጆች በኤርትራ እስር ቤት እንደሚገኙ ከተለቀቁት ሰዎች ሰምተዋል፡፡
የተለቀቁት በአሁኑ ወቅት በራማ እንደሚገኙና በቅርቡ ወደቤተሰቦቻቸው እንደሚቀላቀሉ ያስታወቁት ኮማንደሩ ጨምረውም ‹‹የኤርትራ መንግስት እነዚህን ታጋቾች የለቀቀው የትግራይ ባለስልጣናትን ሳያማክር በራሱ ፍላጎት ነው›› ብለዋል፡፡ እነዚህ ታጋቾች መለቀቃቸውን በተመለከተ እስካሁን የኤርትራ መንግስት ያለው ነገር የለም፡፡
