‹‹በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ ነጋዴዎችን የሚያቅፍ መዋቅር ፈጥረናል››

Date:

ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ

(የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት ዋና ፀሐፊ)

ባሳለፍነው ዕትም ከኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ም/ቤት ዋና ፀሐፊ ዶ/ር ቀነኒሳ ለሚ ጋር በግልና ሙያዊ ሕይወታቸው ዙርያ ሰፋ ያለ ቆይታ ማድረጋችን ይታወሳል፡፡ በሁለተኛውና የመጨረሻው ክፍልም በዋና ፀሐፊነት እያለገሉ ባሉት ም/ቤት አሁናዊ እንቅስቃሴና በቀጣይ በታቀዱ ተግባራት ዙርያ የሚከተለውን ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ!

ግዮን፡- የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እንደተቋም የገቢ ምንጩ ምንድነው?

ዶ/ር ቀነኒሳ፡- አንዱ ተግዳሮት የኾነብን ነገር ገቢ ነው፡፡ ማንኛውም ሥራ ገንዘብ ይፈልጋል፡፡ በመርኅ ደረጃ የየትኛውም ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ገቢ አባሉ ነው፡፡ አባሉ የአባልነት ክፍያ ይከፍላል፡፡ የእኛ አባላት የክልል ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶችና የዘርፍ ማኅበራት ናቸው። የእነዚህ አባላት ደግሞ ቢዝነሶች ናቸው፡፡ ስለዚህ ገቢው የሚገኘው ነጋዴው የክልል ቻምበሮች እና የዘርፍ ማኅበራት አባል ለመሆን በሚከፍለው ገንዘብና እነሱ ደግሞ የእናት ምክር ቤቱ አባል ለመኾን በሚፈፀመው ክፍያ ነበር፡፡ እኛም አባል በመኾናችን ለአፍሪካና ለዓለም አቀፍ ቻምበር እንከፍላለን፡፡ 

አሁን ግን ከአባላት የሚጠበቀው ገቢ እየተገኘ አይደለም፡፡ የገቢ ምንጭ እንደ ከፍተኛ ተግዳሮት የተነሳ ሲሆን ቦርድም መመሪያ እያዘጋጀ ነው፡፡ አባላት ለኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የሚጠበቅባቸውን የአባልነት መዋጮ መክፈል አለባቸው የሚለውን እያዘጋጀን ነው፡፡ እስካሁን በጣም ትንሽ ቻምበሮች ናቸው ራሳቸውን ችለው የአባልነት መዋጮ እየከፈሉ ያሉት፡፡ ስለዚህ ይህ አሠራር መቀየር ይኖርበታል። ለአሁኑ ግን የተለያዩ አገልግሎቶችን እየሰጠን እንገኛለን፡፡ ከምንሰጣቸው አገልግሎቶች አንዱ የተለያዩ ሠርተፍኬቶችን ለተገልጋዮች መሥጠት ነው፡፡

ለነጋዴዎች የተለያዩ የቻምበራይዜሽን ደብዳቤዎች እናዘጋጃለን፡፡ አገልግሎቶቹን የምንሰጠው ከመንግሥት ውክልና ወስደን ነው፡፡ አሁን ያለው ሥራችንን የምንሠራው፣ ለሠራተኞችም ደሞዝ የምንከፍለው በዚህ መልኩ ከምናገኘው ገንዘብ ነው፡፡ ሕንጻችንም ጥቂት የሚከራዩ ክፍች ስላሉት የተወሰነ ወጫችንን በእሱ እየሸፈንን እንገኛለን፡፡ ነገር ግን ትልቁ ገቢ መገኘት ያለበት ከአባላት  በመኾኑ እርሱ ላይ እየሠራን ነው፡፡ ከልማት አጋሮቻችንም ለአባሎቻችን አቅም ግንባታ ሥራ የተወሰነ ገንዘብ እናገኛለን። በተጨማሪም የንግድ ትርዒቶችን ስናካሄድ ከተሳታፊ ነጋዴዎች የሚገኝ የተወሰነ ገንዘብ ይኖራል።

ግዮን፡- በቅርቡ መጋቢት ላይ የምታዘጋጁት ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት እንዳለ ሰምተናል፡፡ ስለዚህ ጉዳይ ትንሽ ቢሉን? የነጋዴዎች በዚህ ንግድ ትርዒት መሳተፉ ያለው ጠቀሜታስ እንዴት ይገለጻል?

ዶ/ር ቀነኒሳ፡- የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እቅድ የኾነውና እንደ ሀገርም በጣም ትልቅ ኹነት ነው ብለን እየተዘጋጀንበት ያለነው ከፊታችን መጋቢት 4 እስከ 8 ወይም በነጮቹ አቆጣጠር ከማርች 13 እስከ 17 የሚካሄደው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት ነው፡፡ የትርዒቱ መሪ ሐሳብ ‹‹የኢትዮጵያን ይግዙ›› የሚል ነው፡፡ የዓለም አቀፍ ቢዝነሶች አገልግሎቶቻቸውንና ምርቶቻቸውን የሚያስተዋውቁበት፣ በሀገር ውስጥ ያሉ ነጋዴዎች ከሌላው ዓለም ነጋዴ የሚተዋወቁበት፣ ገበያ የሚያገኙበትና ወደፊትም የንግድ ትስስር የሚፈጥሩበት ኩነት ነው የንግድ ትርዒቱ፡፡ ይህ ኹነት በጣም ትልቅና ዓለም አቀፍ ኤቨንት ነው፡፡ እኛም በከፍተኛ ሁኔታ እያስተዋወቅን እንገኛለን፡፡ በርካታ ድርጅቶችም ትርዒቱን ስፖንሰር በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም የጥናትና ምርምርና የፈጠራ ሥራዎቻችውን ሊያስተዋዉቁበት የሚችሉበት መድረክ ነው፡፡ ባንኮችና ሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ደግሞ ፋይናንስ ሊደረግ የሚችልን ሐሳብ እና ስታርት አፕ ለመለየት ይሳተፋሉ፡፡ ለምሳሌ፦ በባንኩ ኢንዱስትሪ የውጭ ባንኮች ሊገቡ ነው፡፡ ስለዚህ ኢንቨስት የሚያደርጉትን ሐሳብ ይወስዳሉ፡፡ በአጠቃላይ የሀገራችን ቢዝነስ ባለቤቶች ከትላልቅ እስከ ትናንሽ ነጋዴዎች በመገናኘት ወደፊት ትስስራቸውን የሚያጠናክሩበት ስለኾነ ቦታ ያልያዛችሁ እንዳያመልጣችሁና እንዳያልፋችሁ የሚል መልዕክትም ማስተላለፍ እወዳለሁ፡፡ ስፖንሰር ማድረግ የሚፈልጉ አካላትም ስፖንሰር በማድረግ ምርትና አገልግሎታቸዉን እንዲያስተዋዉቁ ጥሪዬን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡

ግዮን፡- ከዚህ ቀደም ከነበሩ የንግድ ትርዒቶች ይኼኛው በምን ይለያል? የውጭ ዘርፉን ባለሀብቶችን ተሳታፊ ለማድረግስ ምን ያህል ጥራችኋል?

ዶ/ር ቀነኒሳ፡- ይኼኛው የንግድ ትርዒት እስካሁን ከተከናወኑ ትርዒቶች በብዙ መልኩ ይለያል፡፡ በመጀመሪያ የውጭ ሀገር ተቋማት ወደ ሀገራችን ገብተው ቢዝነስ የሚያከናውኑበት ብቻ ሳይኾን የመንግሥት ፖሊስ የተሻሻለበት ጊዜ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲውን አሻሽሎ የኢትዮጵያን ገበያ ለዓለም ገበያ ክፍት አድርጓል፡፡ ከዚህ አኳያ ሌላ ጊዜ ሲመጡ ምናልባት ይዘው የመጡትን ዕቃ ሸጠው ለመሄድ ብቻ ይኾናል፡፡ አሁን ግን ባንኮችን ጨምሮ የኢትዮጵያ ገበያ ክፍት ስለኾነ ተቋማቱ በተጨማሪ በቋሚነት ኢንቨስት የሚያደርጉበትም አጋጣሚ ተፈጥሯል።

ሌላው ልዩነት ደግሞ በዚህ ትርዒት ላይ የሚሳተፉት ተቋማት ከምንጊዜውም በላይ በጣም በርካታ ናቸው፡፡ ለመረጃው ተደራሽነታችን ደግሞ ከኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በበርካታ ኤምባሲዎችና ሚሲዮኖች በኩል መረጃው እንዲያልፍ እያደረግን ነው፡፡ ኤምባሲዎች ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ እያደረግን ነው፡፡ በሌላ በኩል ይህን ትርዒት የምናዘጋጀው ብቻችንን ሳይኾን ከኢትዮጵያ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመኾን ነው፡፡ በመንግሥት በኩልም እስካሁን ይህን ያህል ልዩ ትኩረት የተሰጠበት ባዛር አልተካሄደም፡፡ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽንና በርካታ ተቋማትም አብረውን እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ከፍተኛ መንግሥታዊ ተቋማት በኮሚቴ ደረጃ አንድ ላይ ተዋቅረው በማስተባበር ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ቀደም በዚህ ልክ መንግሥታዊ ተቋማት የተሳተፉባቸው ትርዒቶች ተካሄደው ባለማወቃቸው ይኼኛው ልዩ ይኾናል፡፡

ግዩን፡- ነጋዴ የንግድና ዘርፉ ማኅበራት ምክር ቤት አባል የመኾን ግዴታ አለበት? አባል በመኾኑ የሚጠቀመው ነገር ምንድነው? አባል እንዲኾን በእናንተ በኩል የሚሠራስ ነገር አለ?

ዶ/ር ቀነኒሳ፡- በአባልነት ሂደት ውስጥ ሁለት ዓይነት ሥርዓቶች አሉ፡፡ አንደኛ ሀገራት አስገዳጅ የአባላት ምልመላን የሚከተሉበት ሥርዓት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ የአባላት ምልመላ ሥርዓት ነው። ኢትዮጵያ ፈቃደኛ አባልነትን ከሚከተሉ ሀገራት ውስጥ አንዷ ነች፡፡ አንድ ነጋዴ የንግድ ምክር ቤቱ አባል የሚኾነው በፈቃዱና ፍላጎቱን መሠረት አድርጎ እንጂ የሚያስገድደው አካል የለም፡፡ አባል ከሆነ ግን ብዙ የሚጠቀማቸው ነገሮች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ፦ አንድ ነጋዴ የትኛውም ንግድ ውስጥ እሠራለሁ ብሎ መነሳት ያለበት በሚኖርበት አካባቢ ብቻ አይደለም፡፡ ምሕዳሩን እንደሚያሰፋ አስቦ ነው የሚሠራው፡፡ በዚህ ውስጥ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተሰጠው ንግድና ኢንቨስትመንትን ከሌሎች የውጭ አገር ቻምበሮች እና ነጋዴዎች ጋር ኾኖ የማሳለጥ በዐዋጅ የተደገፈ መብት ያለው መሆኑ ለአባሉ ይጠቅመዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ መብትና ጥቅሙን ለማስጠበቅ ከምክር ቤቱ ጋር መሥራቱ ያዋጣል፡፡ ለምሳሌ፦ እኛ የግልግል ማዕከል አለን፡፡ ከምንሰጣቸው አገልግሎቶች ውስጥ አንዱ የሕግና ግልግል አገልግሎት ነው፡፡ አባሎች ከተጎዱ ምክር ቤቱ የትኛውም ፍርድ ቤት ሄዶ መከራከርና ጥብቅና መቆም ይችላል፡፡ ስለዚህ ነጋዴዎች ነገ ለማደግ እስካለሙ ድረስ ለአባልነት የሚያስገድዳቸው ሕግ ባይኖርም አባል ሆነው መገኘት በጣም ይጠቅማቸዋል፡፡

ግዮን፡- ንግድ ምክር ቤቱ ድሮ መጽሔቶችና ጋዜጦች ነበሩት፡፡ አሁን ግን እነዚያ የሕትመት ሥራዎች አይታዩም፡፡ በምን ዓይነት መንገድ ነው ከአባሎቻችሁ ጋር ግንኙነት የምታደርጉትና ሀሳባችሁን የምታሰርፁት?

ዶ/ር ቀነኒሳ፡- የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት እንቅስቃሴውን በዲጂታል የኮሙኒኬሽን አግባቦች መረጃዎችን በወቅቱ ተደራሽ ያደርጋል፡፡ ነገር ግን ይኸኛው አሠራር ብቻውን የግንኙነት ስትራቴጂ ተደርጎ መታየት የለበትም፡፡ ስለዚህ በሁሉም መንገድ ከአባላትም ይሁን ከአጋሮች ጋር የመገናኛ መንገዶች መጠቀም አለብን፡፡ አሁን ላይ በአዲስ እናደራጃለን ብለን አሁንም አየር ላይ ካሉት የቅጥር ማስታወቂያዎች ውስጥ አንዱ የሕዝብ ግንኙንትና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ነው፡፡ ስለዚህ ይህን ሂደት በደንብ አደራጅተን ትክክለኛውን ሰው በትክክለኛው ቦታ አድርገን በተለያየ የመገናኛ ዘዴ መድረስ አለብን ብለን እናስባለን፡፡

ግዮን፡- በውጭው ዓለም ካሉ የንግድ ማኅበራት ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት ምን ጥረት እያደረጋችሁ ነው?

ዶ/ር ቀነኒሳ፡- እኔ ወደዚህ ኃላፊነት ከመጣሁ አራት ወራት ሆኖኛል፡፡ ሁለት ሀገራት ሄጃለሁ፡፡ በተለይ በቢዝነስ ዴሊጌሽን ደቡብ አፍሪካ ሄደን ያየነው በደቡብ አፍሪካ ኢኮኖሚ ውስጥ ወደ 2.9 ቢሊዮን ዶላር የሚንቀሳቀሰው በኢትዮጵያውያን መኾኑን ነው፡፡ ከዚህ ውስጥ ዘጠና ፐርሰንቱ ሕገወጥ በኾነ የገበያ ሥርዓት ውስጥ ያለ ነው፡፡ ስለዚህ ማንም እንደፈለገ ያነሳቸዋል፡፡ ነገር ግን ለደቡብ አፍሪካ ኢኮኖሚ 2.9 ቢሊዮን ዶላር አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው፡፡ ስለዚህ አሁን እየመከርንበት ያለው ጉዳይ ኢትዮጵያ በተለያዩ ሀገራት የቻምበር ቅርንጫፍ እንድትከፍት ማድረግ ነው፡፡ ያን ለማድረግ ዐዋጃችን ይፈቅድልናል፡፡ በዚህም ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደቡብ አፍሪካ ላይ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ቅርንጫፍ እንዲኖር ደብዳቤ ጽፈናል፡፡

ቅርንጫፍ ከፍተን እዚያ ያሉ ኢትዮጵያውያንን አደራጅተን ጥቅማቸውን እናስከብራለን፡፡ በሌላ በኩል እዚያ ያሉ ዜጎቻችን ከሀገራቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት እናጠናክራለን፡፡ እያደጉ ሲሄዱ ደግሞ ወደሀገር ቤት ምንዛሬ በመላክ ወገናቸውን ይረዳሉ፡፡ ይህን ጉዳይ በተመለከተ በተግባር ሥራ ጀምረናል፡፡ ከሀገሪቱ ቻምበርም ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመናል፡፡ እኛ ሀገር የዱባይ፣ የቻይና እና የተለያዩ ሀገራት ቻንበሮች እንዳሉ የእኛም በሌላው ዓለም ይኖራል፡፡ እዚህ ካሉ የሌላ ሀገር ቻምበሮችም ጋር ጥሩ ግንኙነት አለን፡፡

ግዮን፡- ምክር ቤቱን ከማጠናከር አኳያ አዲሱ ቦርድ እየወሰደ ስላለው እርምጃ ቢነግሩን?

ዶ/ር ቀነኒሳ፡- ምክር ቤቱን የማጠናከር ሂደት ላይ ተቋማችን እንደተቋም የሚሠራው ሥራ አለ፡፡ በቅርቡ የምክር ቤታችን አባላት የኾኑ የክልል ቻምበሮች አሉ፡፡ እነዚያ ክልሎች ላይ አዳዲስ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባላት እየተፈጠሩ ነው። ስለዚህ የተደራጀና ጠንካራ ቻምበር እንዲኖረን እየሠራን ነው፡፡ ኃላፊነታችንን ለመወጣት የዳይሬክተሮች ቦርድ አንደኛ ዓመት ስብሰባ ላይ እነዚህን አባላት ለማጠናከር የሰጠነው የገንዘብ ድጋፍ አለ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ቻምበሩን ማሻሻል የሚቻለው ገንዘብ ሰጥቶ ሳይሆን እውቀትን ሰጥቶ ነው፡፡ ስለዚህ ሥልጠናዎች እንሰጣለን፡፡ እንዴት ገንዘብ ማምጣት እንዳለባቸው፣ እንዴት ከንግድ ምክር ቤቱ ጋር እንደሚሠሩ፣ እንዴት የአድቮከሲ ሥራ እንደሚሠሩ፣ እንዴት የግንኙነት ሥራ እንደሚሠሩ እያሰለጠንን ነው፡፡ እነዚህን ሥልጠናዎች ያደራጀነው በማዕከል ብቻ አይደለም። ሁሉንም ክልሎች በሚነካ መልኩ ክላስተር አድርገን እየሰጠን ነው፡፡ ስለዚህ እኔ እንደመምህር ሰው ሊሰጠኝ የሚገባው ማቴሪያል አይደለም ፤ ሰው ሊሰጠኝ የሚገባው አዕምሮዬን የሚቀይር እውቀት ነው ብየ ነው የማምነው፡፡ ይህን ስጦታ በጣም ትልቅ ስጦታ አድርጌ ነው የምቀበለው፡፡ እኔም ደስ የሚለኝ የማውቀውን እውቀት ለሌሎች ብሰጥ ነው፡፡ በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትም ያንን አስቦ እውቀትን እየሰጠ ይገኛል፡፡ ለወደፊትም ይህ መሰል ሥልጠናዎች ለሌሎች እንሰጣለን፡፡

ሌላው ሥልጠናዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አዳዲስ ቢሮዎችን እያደራጀን ነው፡፡ ከዚህ በፊት ያልነበረ የአባላት ጉዳይ ዳይሬክቶሬት አደራጅተናል፡፡ ዳይሬክተሩ የሚገመገመው አባላቱን በማደራጀት፣ በመርዳት፣ ከአባላት ወደ ምክር ቤቱ ሊገባ የሚገባውን የአባልነት መዋጮንና ሌሎችን ጉዳዮች በመከታተል ነው፡፡ ከአባላት ደግሞ የሴቶች፣ የወጣቶችና የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ መሠረታዊ ነው፡፡ በየትኛውም የንግድ ሥርዓት ውስጥ እነዚህ ትኩረት የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡ ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞችን በልዩ ሁኔታ የሚከታተል በአባላት ጉዳይ ሥር አንድ ራሱን የቻለ ቢሮ አቋቁመናል፡፡  ቢሮው የሚገመገመውም ምን ያህል ሴቶችን እንዳደራጀና ምን ያህል አካል ጉዳተኞችን የሚያግዝ ፕሮጀክት ሐሳብ አፈለቀ? ምን ያህል ወጣቶች ተጠቃሚ ኾኑ? በሚለው ዙሪያ ነው። በተለይ ደግሞ በጥቃቅንና አነስተኛ ንግድ የተደራጁ ነጋዴዎችን የሚያቅፍ መዋቅር ፈጥረናል፡፡ ከገንዘብ እስከ ቢሮ አደረጃጀት እንዲሁም ሥልጠናዎች ድረስ ለአባላቱ ልዩ ትኩረት ሰጥተን እየሠራን እንገኛለን፡፡ አዳዲስም ይሁን ነባር የቻምበር አባሎቻችን መጠናከር አለባቸው ብለን በልዩ ትኩረት እየሠራን ነው፡፡

ግዮን፡- ምክር ቤቱ ማኅበራዊ ኃላፊንቱን በመወጣት ረገድ ምን እየሠራ ነው?

ዶ/ር ቀነኒሳ፡- የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት፣ እንደማንኛውም ኃላፊነት እንደሚሰማው ተቋም እንዲሁም እንደ ንግዱ ማኅበረሰብ ተወካይነቱም በተለያዩ ጊዜያት በተለያዩ አካባቢዎች ትንሽም ብትሆን የገንዘብ ድጋፎችን ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ፦ ባለፈው ዓመት በጎፋ ዞን በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች በአካል ሄደን ወደ 300 ሺህ ብር የሚደርስ የገንዘብ እርዳታ አድርገናል፡፡ በአረንጓዴ ልማት (ግሪን ሌጋሲ) ዙሪያም በርካታ ሥራዎችን እየሠራን እንገኛለን። በከተማችን ባለንበት ማኅበረሰብ ውስጥ ለምሳሌ፦ ለጤና ኢንሹራንሶች ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የጤና መድህን ገዝተን ስንሰጥ ቆይተናል፡፡ ለታላቁ ሕዳሴ ግድባችንም ቦንድ ገዝተን አስተዋፆአችንን አበርክተናል፡፡ በአጠቃላይ ተቋማችን ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡

ግዮን፡- ስለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ሥም ከልብ እናመሠግናለን፡፡

ዶ/ር ቀነኒሳ፡- እኔም በጣም አመሰግናለሁ፣ እግዚአብሔር ይስጥልን!

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

“ሺ ጂምፒንግ ምርጥ መሪ ነው!”- ትራምፕ

አሜሪካና ቻይና ተፎካካሪ ሳይሆኑ አጋርነት ያላቸው ሀገራት ናቸው አሉ...

የአሜሪካ የፀሐይ ብርሃን ኃይል አምራቾች በኢትዮጵያ ላይ የንግድ ምርመራ እንዲደረግ ጠየቁ

በአሜሪካ የሚገኙ የፀሐይ ብርሃን ኃይል አምራቾች፣ የቻይና ኩባንያዎች የአሜሪካን...

ምርጫ ለሰላም ግንባታ

ግዮን መጽሔት :-ለኢትዮጵያ ሰላም ምርጫ አማራጭ የሌለው መንገድ ነው።...