በድጋሚ በተደረገው የወላይታ ዞን ሕዝበ ውሳኔ ላይ፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ሂደቱን በድጋሚ “እንዲሰረዝ” የሚያስገድዱ ተግባራት በዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ሲፈጸሙ እንደነበር የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ ተናገሩ። የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ በህዝበ ውሳኔው ዕለት፤ ምርጫ ቦርድ “ሌላ ውሳኔ እንደሰጠ” አድርገው መልዕክት ሲያስተላልፉ እንደነበርም አቶ ውብሸት ገልጸዋል። የምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ይህንን ያሉት፤ ረቡዕ ሰኔ 28 ቀን 2015 ዓ.ም በተካሄደ የፌዴሬሽን ምክር ቤት መደበኛ ጉባኤ ላይ ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ ነው። የፌዴሬሽን ምክር ቤት በዕለቱ በነበረው ውሎ ከተመለከታቸው አጀንዳዎች ውስጥ፤ የ“ደቡብ ኢትዮጵያ” ክልልን ለመመስረት የተደረጉትን ህዝበ ውሳኔዎች በተመለከተ ምርጫ ቦርድ የሚያቀርበውን አጠቃላይ ሪፖርት ማዳመጥ አንዱ ነበር።
በነባሩ ደቡብ ክልል ውስጥ በሚገኙ ስድስት ዞኖች እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ላይ ባለፈው ጥር ወር እንዲሁም በወላይታ ዞን በድጋሚ ሰኔ ወር ላይ የተደረጉትን ህዝበ ውሳኔዎች አፈጻጸም የተመለከተ ሪፖርት በአቶ ውብሸት በንባብ ቀርቧል። ምርጫ ቦርድ ህዝበ ውሳኔውን ለማካሄድ ያለፋቸው ሂደቶች፣ የተገኘው ውጤት እንዲሁም ያጋጠሙት ችግሮች በዚሁ ሪፖርት በዝርዝር ተካትቷል። በ26 ገጾች በተዘጋጀው በዚሁ ሪፖርት ውስጥ በችግርነት ከተጠቀሱ ጉዳዮች ውስጥ፤ በወላይታ ዞን ተከስተው ነበር የተባሉ የህግ ጥሰቶች ይገኙበታል። በወላይታ ዞን ባለፈው ጥር ወር የተካሄደው ህዝበ ውሳኔ እንዲሰረዝ ምክንያት የሆኑ የህግ ጥሰቶችን አጽንኦት ሰጥተው ያነሱት ምክትል ሰብሳቢው፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ 94 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ተናግረዋል። ከእነዚህ ውስጥ 76 ያህሉ ምርጫ አስፈጻሚዎች መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ ውብሸት፤ አስራ ስምንቱ ደግሞ የቀበሌ አመራሮች እንደሆኑ አመልክተዋል።
ምርጫ ቦርድ ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም በወላይታ ዞን በድጋሚ ህዝበ ውሳኔ ሲያካሄድም ችግሮች እንዳጋጠሙት አቶ ውብሸት በዛሬው ሪፖርታቸው ጠቁመዋል። በህዝበ ውሳኔ ዕለት ድምጽ ለመስጠት የወጡ መራጮች የያዟቸው መታወቂያዎች፤ ከስድስት ወራት ባነሰ ጊዜ የተሰጡ መሆናቸው በሪፖርቱ እንደ አንድ ችግር ተጠቅሷል። ዕድሜያቸው ያልደረሰ ህጻናት የምርጫ ሰልፍ ላይ መገኘታቸው በተጨማሪ ችግርነት ተነስቷል። “የቀበሌ አመራሮች ‘ለእርግብ አማራጭ ድምጽ ጨምሩ’ በማለት የምርጫ አስፈጻሚዎቹ ላይ ጫና ማሳደራቸው” በሰኔው ህዝበ ውሳኔ ላይ የታየ ሌላው ችግር መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል። ምርጫ ቦርድ በእነዚህ ችግሮች ምክንያት የ25 ምርጫ ጣቢያዎች ውጤት እንዲሰረዝ እና ከአጠቃላይ ውጤቱ ጋር እንዳይዳመር ማድረጉን ምክትል ሰብሳቢው አቶ ውብሸት አስታውቀዋል።
ከዚህ የምርጫ ቦርድ ሪፖርት በኋላ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት በሪፖርቱ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ እድል አግኝተዋል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ከሆኑት የደቡብ ክልል አመራሮች ለቀረቡ አስተያየቶች እና ጥያቄዎች፤ የምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል። የህግ ጥሰቶችን በተመለከተ ከደቡብ ክልል አመራሮች የተሰጠው ምላሽ “በቂ” መሆኑን አቶ ውብሸት ገልጸዋል። የወላይታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አክሊሉ ላነሱት ጉዳይ ግን “በግዴታ” ምላሽ እንደሚሰጡ ለምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል። ዋና አስተዳዳሪው ምርጫ ቦርድ በተመለከተ ያቀረቡት ውንጀላ ተመዝግቦ የሚቀመጥ መሆን፤ ምላሽ ለመስጠት እንዳስገደዳቸውም አስረድተዋል።
በተያያዘ ዜና ምክር ቤቱ ከዚህ የምርቻ ቦርድ ሪፖርት በኋላ፣ “የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል” የኢፌዲሪ 12ኛ ክልል ሆኖ እንዲደራጅ በሙሉ ድምጽ ወሰኗል። የነባሩ የደቡብ ክልል፤ በህዝበ ውሳኔ መሰረት ለሚመሰረተው ለአዲሱ ክልል የስልጣን ርክክብ እንዲያደርግ እና ሂደቱንም እንዲያስፈጽም ባካሄደው መደበኛ ጉባኤ ውሳኔ አሳልፏል። በነባሩ ክልል የቀሩ መዋቅሮች፤ ራሳቸውን መልሰው በማደራጀት ባሉበት እንዲቀጥሉም ውሳኔ ተላልፏል። በፌዴሬሽን ምክር ቤት በጸደቀው የሕዝበ ውሳኔ ውጤት መሠረት አዲስ ክልል በጋራ የሚያቋቋሙት፤ በነባሩ የደቡብ ክልል የሚገኙት የጌዲኦ፣ የወላይታ፣ የጋሞ፣ ጎፋ፣ የኮንሶ፣ የደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲሁም የቡርጂ፣ የአማሮ፣ ደራሼ፣ ባስኬቶ እና የአሌ ልዩ ወረዳዎች ናቸው። እነዚህ መዋቅሮች በየምክር ቤቶቻቸው ባደረጉት ስብሰባ ያሳለፉትን በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ፤ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ያቀረቡት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ ነበር።
