የአፍሪካ መሪዎች በዚህ ሳምንት በአቢጃን እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ ልማት ባንክ ቡድን የ2025 ዓመታዊ ስብሰባዎች ላይ አህጉሪቱ የራሷን ካፒታል እንድታንቀሳቅስ እና የክልላዊ ውህደትን እንድታፋጥን ጠንካራ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህ ጥሪ የቀረበው፣ 47 የአፍሪካ አገራትን የሚነኩ አዳዲስ የአሜሪካ ታሪፎችን ጨምሮ በሚለዋወጠው ዓለም አቀፍ የንግድ ሁኔታዎች ምክንያት መሆኑ ተጠቁሟል።
በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ የአሥር ዓመቱን የሥራ ዘመናቸውን የሚያጠናቅቁት የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት አኪንዉሚ አዴሲና፣ ባደረጉት የስንብት ንግግር፣ “ይህ ከውጭ ዕርዳታ ቁርጥራጮች የምንጠብቅበት ጊዜ አይደለም” በማለት ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
አዴሲና አክለውም፣ “አፍሪካ የራሷን ሀብት – ሰብዓዊ፣ ፋይናንስ፣ ተፈጥሮአዊ – መክፈትና ሁሉን አቀፍ ዕድገትን የሚያበረታቱ ውስጣዊ የእሴት ሰንሰለቶችን መገንባት አለባት” ሲሉ አሳስበዋል።
