በታንዛኒያ በየቀኑ እስከ 500 የሚደርሱ አህዮች የሚታረዱባቸው እርድ ቤቶች እንዳሉ ሲገለጽ እነዚህን የእርድ ማዕከላት በይፋ በመዝጋት አህዮችን እና ውሾችን ለንግድ ማረድ በይፋ ከልክላለች።
ይህ እርምጃ ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ምሳሌ ይሆናል ተብሏል። የእንስሳት መብት ተሟጋቾችም የታንዛኒያን ውሳኔ አድንቀዋል።
የአህያ ቆዳ ለቻይናው ባህላዊ መድኃኒት ኢጂያኦ/Ejiao ግብዓት በመሆኑ ምክንያት በከፍተኛ ሁኔታ ተፈላጊነቱ እየጨመረ በመምጣቱ የአፍሪካ አህዮች በስፋት ለእርድ ሲቀርቡ፤ ቻይናዊያኑም ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ ሀገራት የእርድ ፋብሪካቸውን ከፍተው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ።
በታንዛኒያ፣ ባለሥልጣናቱ የአህያ ቁጥር ከአሥር ዓመት በፊት ከነበረው በ60 በመቶ ቀንሷል ሲሉ ውሳኔውን ማሳለፋቸውን ገልጸዋል።
በገጠሪቱ አፍሪካ አህዮች የቤት እንስሳት ብቻ አይደሉም። የበርካታ አፍሪካዊያን ሸክም የሚያቀሉ፤ ማኅበራዊ ፋይዳቸው የጎላ እንስሳት ጭምር ናቸው።
የታንዛኒያ አዲሱ ፖሊሲ እርድን የሚከለክል ብቻ ሳይሆን አህዮችን ለሰው ልጅ ፍጆታ ወይም ምግብነት ከተፈቀዱ እንስሳት ዝርዝር ውስጥ ያስወጥቷል።
መንግስት ዳግም የእንስሳት ደህንነት ቁጥጥር ባለሙያዎችን በማሰማራትም በዚህ ዙሪያ ግንዛቤዎችን በመስጠት እየሰራ ነው። ሆኖም ፈተናዎች አሁንም አሉ።
እ.ኤ.አ. በ 2024 የተካሄደው የመስክ ጥናት በታንዛኒያ የሀገር ውስጥ የአህያ ሥጋ ንግድ በስፋት ተስተውሏል። አሁንም የአህያ ቆዳዎች ብዙውን ጊዜ በህገ-ወጥ መንገድ ወደ ድንበር ክልሎች ይጓጓዛሉ።
በ 37ኛው የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔ ላይ ይህ ጉዳይ በአጀንዳነት ተነስቶ፤ በአህዮች ላይ ጥገኛ የሆኑ ማኅበረሰቦችን ህልውና ለመጠበቅ በአህጉሪቱ የሚገኙትን 33 ሚሊዮን አህዮችን ከመሰረቅ፣ ከህገወጥ ዝውውር እና ከእርድ ለመጠበቅ ያለመ ስምምነት ተደርጎ ነበር።
በአፍሪካ ከፍተኛ የአህያ ቁጥር እንዳላት በሚነገርላት ኢትዮጵያ ይህ ጉዳይ በተደጋጋሚ ሲነሳ ሲተው ቆይቷል። መረጃዎቾ እንደሚጠቁሙት በኢትዮጵያም ያለው የአህያ እርድ ከ2016 እስከ 2022 ባለው ጊዜ ከ300,000 በላይ አህዮች ቆዳቸው ተገፏል።
በኢትዮጵያ የአህያ ቁጥር እየተመናመነ ነው ሲሉ በዘርፉ ትኩረት አድርገው የሚሰሩ ተሟጋቾች ቢያነሱም መንግስት በበኩሉ ለእርድ የሚቀርቡት አህዮች ያረጁ፣ የአካል ጉዳት ያለባቸው ናቸው ሲል ከዘርፉ የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ይበልጣል ሲል ምላሽ መስጠቱ ይታወሳል።
Source : The Citizen
@TikvahethMagazine
