የአሜሪካ ኮንግረስ አባል የሆኑት ስኮት ፔሪ፣ ሶማሊላንድን እንደ ገለልተኛና ሉዓላዊ ሀገር በይፋ እውቅና የሚሰጥ ረቂቅ ህግ ማስተዋወቃቸው ተዘገበ፡፡ ረቂቅ ህጉ “የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ የነጻነት ህግ” የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡
ይህ እርምጃ የአሜሪካ የውጭ ፖሊሲ፣ ስልታዊ ጠቀሜታው እያደገ በመጣው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ካለ አዲስ፣ ሰላማዊና ራሱን በራሱ ከሚያስተዳድር አጋር ጋር እንዲጣጣም ያለመ መሆኑ ተገልጿል።
የኮንግረስ አባሉ በሰጡት መግለጫ፤ “ሶማሊላንድ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት አሜሪካ ልትደግፈው የሚገባ አይነት አስተዳደር፣ መረጋጋትና የትብብር መንፈስ አሳይታለች” ብለዋል።
አክለውም፤ “የውጭ ተቀናቃኞች በአፍሪካና በዓለም ዙሪያ እየተስፋፉ ባለበት በዚህ ወቅት፣ እሴቶቻችንን ከሚጋሩና ለደህንነታችን አስተዋጽኦ ከሚያደርጉ አስተማማኝ አጋሮች ጋር ያለንን ግንኙነት ማጠናከር የሀገራችን ፍላጎት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።
የሶማሊያ መንግስት በሶማሊላንድ ላይ የሚያቀርበው “መሰረተ ቢስ የይገባኛል ጥያቄ”፣ አሜሪካ ዲሞክራሲያዊ ምርጫዎችን ከምታካሂደው እንዲሁም የባህር ላይ ወንበዴነትንና ጽንፈኝነትን በንቃት ከምትዋጋው ሶማሊላንድ ጋር ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳትፈጥር እንቅፋት ሆኗል ብሏል፤ የኮንግረስ አባሉ መግለጫ፡፡
