ከ22 ዓመታት በኋላ የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫን ያነሳው አርሰናል፣ ትኩረቱን በክረምቱ የዝውውር መስኮት ላይ በማድረግ የቡድኑን ስብስብ ይበልጥ ለማጠናከር አቅዷል።
ምንም እንኳን በቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ በፒኤስጂ (PSG) ቢሸነፉም መድፈኞቹ ከአሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ጋር በመሆን የክረምቱን የዝውውር እቅድ ነድፈዋል።
ባለፈው የውድድር ዓመት በዝውውር ላይ የወጣው 250 ሚሊዮን ፓውንድ እና ለተጫዋቾች የተከፈለው የሻምፒዮናነት ጉርሻ (Bonus) ክለቡ የፋይናንስ ሚዛኑን እንዲጠብቅ ያደርገዋል ። በመሆኑም አዳዲስ ተጫዋቾችን ለማስፈርም ተጫዋቾችን መሸጥ ግድ ይለዋል።
አርሰናል ሶስት ተጫዋቾችን በእጩነት ይዟል። እነሱም የአስቶን ቪላው ሞርጋን ሮጀርስ የቦርንማውዙን ታዳጊ ጁኒየር ክሩፒ እና የባርሴሎና ኢላማ የሆነው የአትሌቲኮ ማድሪዱ ጁሊያን አልቫሬዝ ናቸው።
ለእነዚህ ዝውውሮች ገቢ ለማግኘት ክለቡ ለገብርኤል ጅሰስ፣ ገብርኤል ማርቲኔሊ፣ ፋቢዮ ቪዬራ እና ሪስ ኔልሰን የሚቀርቡ ጥያቄዎችን ለማስተናገድ ዝግጁ ነው። ያኩብ ኪቪዮር ቀድሞውኑ ለፖርቶ በ14.7 ሚሊዮን ፓውንድ የተሸጠ ሲሆን፣ ክርስቲያን ኖርጋርድ እና ቤን ዋይትም ሊሸጡ እንደሚችሉ ተነግሯል። አካዳሚ አሳዳጊው ኤታን ንዋኔሪም ለንጹህ ትርፍ ሲባል የመሸጥ ዕድል አለው።
በተጨማሪም ክለቡ ከተከላካዩ ዩሪየን ቲምበር ጋር አዲስ ውል ለማጠናቀቅ የተቃረበ ሲሆን ከዋናው አማካይ ዲክላን ራይስ ጋርም የውል ማራዘሚያ ንግግር ለመጀመር ፍላጎት እንዳለው ምልክት አሳይቷል።
. (አሐዱ ሬዲዮ)
