ሩሲያ በዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ በተፈጸመችው ተከታታይ የባለስቲክ ሚሳዔል ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል፤ ቢያንስ 14 ሰዎች መቁሰላቸውን የዩክሬን ባለሥልጣናት አስታወቁ።
- ምሽቱን በተሰነዘረው ጥቃት በክልሉ የሚገኙ በርካታ ቦታዎች ተመትተዋል። የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ፤ የሩሲያ በሙሉ ወረራ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ “ኪዬቭ ላይ ከተፈጸሙት እጅግ ግዙፍ የባለስቲክ ጥቃቶች አንዱ” ሲሉ ገልጸውታል።
- የዩክሬን ጦር በበኩሉ የአገሪቱ የአየር መከላከያ ስርዓት ከተሰነዘሩት 41 ሚሳዔሎች ውስጥ 18 ያህሉት መትቶ መጣሉን አስታውቋል። ስርዓቱ 108 ድሮኖችን መጥለፉንም ገልጿል።በሌላ በኩል ዩክሬንም ሩሲያ ላይ ጥቃት መፈጸሟን ቀጥላለች።
- የዩክሬን ጦር እንደሚናገረው፤ በጥቁር ባሕር የሚገኙ ሁለት የሩሲያ ነዳጅ ጫኝ መርከቦች በድሮን ተመትተዋል።የሩሲያ ደቡብ ምዕራባዊ ስታቭሮፖል ክልል ገዥ በበኩላቸው፤ የኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ በተፈጸመው የድሮን ጥቃት እሳት መነሳቱን ተናግረዋል።
- የዩክሬን አየር ኃይል እንደገለጸው በመዲናዋ ኪዬቭ የተሰነዘሩት ጥቃቶች ኢስካንደር እና ሃይፐርሶኒክ ዚርኮን ሚሳዔሎች እንዲሁም 125 ድሮኖችን ጨምሮ በተለያዩ የሩሲያ የጦር መሣሪያ ሥርዓቶች የተፈጸሙ ናቸው።
- በከተማዋ የሚገኙ አንድ ሱፐርማርኬት እና የተማሪዎች ማደሪያን ጨምሮ የመኖሪያ እና የመኖሪያ ያልሆኑ ሕንፃዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው ከንቲባው ቪታሊ ክሊትስችኮ ተናግረዋል።
- እነዚህ ጥቃቶች ተፈጸሙት፤ ዩክሬን ንብረትነታቸው በሩሲያ ትልቁ የኦንላይን መደብር የሆነው ‘ዋይልድቤሪስ’ የሆኑ ሁለት መጋዘኖች ከተመቱ በኋላ ነው። በዚህ ጥቃት ስምንት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ከፍተኛ እሳትም ተነስቷል።
