በምክክሩ ወቅት በሀሳብ ልዩነት “አድማ የመቱ” ነበሩ

Date:

ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ በ22ኛው ቀን ውሎው በስልታዊ ቡድን ደረጃ ሲካሄድ የቆየውን ምክክር አጠናቋል። ይህ የምክክር ሂደት ባለፈው ሳምንት እንዲጠናቀቅ ዕቅድ ተይዞለት የነበረ ቢሆንም፤ በተለያዩ የሥራ ቡድኖች ሲካሄዱ የነበሩ የምክክር ሂደቶች መጠናቀቅ ባለመቻላቸው ምክንያት ተጨማሪ ሦስት ቀናትን ወስዷል። በስልታዊ ቡድኖች ደረጃ ሲካሄዱ የነበሩ የምክክር ሂደቶች መጠናቀቃቸውን ተከትሎም የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አራት ኮሚሽነሮች ለተመካካሪዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

  ሐምሌ 08 ቀን 2018 ዓ.ም ከተካሄደው የምክክር ጉባኤው የመክፈቻ ሥነ ሥርዓተ በኋላ ለመጀመሪያ  ጊዜ በተካሄደውና ሁሉም ተመካካሪዎች እንደተገኙበት በተነገረለት ማብራሪያ ላይ ንግግር ያደረጉት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ፤ በኮሚሽነሮች፣ አወያዮች እና ቃለ ጉባኤ ያዦች ላይ  ቅሬታዎች መቅረባቸውን እንደተናገሩ ከምንጫችን ሰምተናል።

በምክክር ሂደቱ ለአንድ ወገን ያደሉ ኮሚሽነሮች፣ አወያዮችና ቃለጉባኤ ያዦች አሉ የሚል ቅሬታ ቀርቦልናል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ኮሚሽኑ መሰል አካሄዶችን ያርማል ሲሉ መናገራቸውን ምንጮች ነግረውናል። መሰሉ ሁኔታ “የሚጠበቅ” ነው ሲሉም፤ ተመካካሪዎች በሁኔታው እንዳይደናገጡ ማሳሰባቸውን ሰምተናል።

ኮሚሽኑ ከተሰጣቸው ኃላፊነት ውጭ የሚንቀሳቀሱ አወያዮች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ መግለጡን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፤ ኮሚሽነሮች ከተመካካሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይትም በቃለ ጉባኤ ያዦች ላይም መሰሉ እርምጃ እንደሚወሰድ አሳውቀዋል። በተወያዮች ቅሬታ የቀረበባቸው ኮሚሽነሮች እነማን እንደሆኑ ግን ኮሚሽኑ አላሳወቀም።

የስልታዊ ቡድን ምክክራቸውን በጊዜው ያላጠናቀቁ ቡድኖች

ኮሚሽኑ የስልታዊ ቡድን ምክክርን ለሶስት ቀናት እንዲያራዝም ምክንያት የሆኑት ስልታዊ ቡድኖች በዋናነት፤ በ”ሀገር ግንባታ”፣ በ”መንግስት አደረጃጀትና”፣ “በአዲስ አበባ እና ድሬ ዳዋ ከተሞች” ጉዳይ የተመካከሩ ቡኖች መሆናቸውን ምንጮች ነግረውናል። በተለይም በሁለቱ ከተሞች ጉዳይ የተመካከሩት ሁለቱ ስልታዊ ቡድኖች፤ የምክክር ሂደቱን እስከማቋረጥ የደረሰ ሂደት ማሳለፋቸውን የገለጡልን ምንጮች፤ የምክረ ሀሳብ ሰነድ ለማዘጋጀት የተደረገው ጥረት ተደጋጋሚ ምክክር እንዲደረግ ማስገደዱን ገልጠዋል። በዚህ የምክክር ሂደት በሚቀርቡ ምክረ ሀሳቦች ዙሪያ ስምምነት ላይ መድረስ አስገዳጅ ጉዳይ ባይሆንም፤ በአዲስ አበባ ከተማ ሕጋዊ ቁመና ጉዳይ የተንጸባረቁ ሀሳቦች “ጠንካራ” መሆን የምክክር ሂደቱን “አስቸጋሪ” ማድረጋቸውን ምንጮች ገልጠዋል።

ኮሚሽኑ ማሳሰቢያ የሰጠበት “አድማ”

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር አምባዬ ኦጋቶ (ዶ/ር) ለተመካካሪዎች በሰጡት ማብራሪያ፤ ኮሚሽኑ ለሁለት ጊዜያት ያህል በተመካካሪዎች የተካሄዱ “አድማዎች”ን ማስተዋሉን መግለጣቸውን ምንጮች ነግረውናል። “የምክክር ሂደቱ ሁሉም ተመካካሪዎች ሀሳባቸውን የሚገልጡበት ነው፤ አድማ መምታት አያስፈልገውም” ሲሉ መናገራቸውንም ሰምተናል።

ኮሚሽነሩ በንግግራቸው በየትኞቹ ቡድኖች አድማ እንደተመታ ባይገልጡም፤ ጉዳዩ ኮሚሽኑን ያሳሰበ መሆኑን መናገራቸውን ምንጮች ጠቁመዋል። በሀገር ግንባታ እና በሁለቱ ከተሞች አጀንዳዎች ዙሪያ በተመካከሩ ስልታዊ ቡድኖች ላይ መሰሉ እንቅስቃሴ መስተዋሉን የጠቆሙን ምንጮች፤ “ብሔራዊ ቋንቋ ይኑር ወይስ አይኑር?” የሚለው ጉዳይ እንዲሁም የአዲስ አበባ ሕጋዊ አቋም ጉዳይ ተመካካሪዎች የምክክር ሂደቱን አቋርጠው ለመውጣት ያደረሱ ምክንያቶች መሆናቸውን ገልጠዋል።

ይሁንና አድማ መትተው ከምክክሩ ራሳቸውን አግልለው የቀሩ ተመካካሪዎች ወይም የተመካካሪዎች ቡድኖች አለመኖራቸውን ሰምተናል።  ያነጋገርናቸው ተመካካሪዎች፤ በምክክሩ ሂደት ተመሳሳይ አቋም የሚያንጸባርቁና በቡድን የሚወስኑ አደረጃጀቶች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ጠቁመዋል።

በክልል፣ በሃይማኖት፣ በፓርቲና በሌሎች ማንነቶች ምክንያት የተሳሰሩና፤ በምክክር ሂደቱ ተመሳሳይ አቋም በማራመድ ላይ የሚገኙ ቡድኖች ከምክክሩ ጅማሮ አንስቶ እንደሚስተዋሉ የገለጡልን ምንጮቻችን፤ የመሰል ቡድኖች ቁጥር መበራከቱን ጠቁመዋል። በክልል፣ በብሔር፣ በፓርቲ እና በሃይማኖት የተደራጁ እንቅስቃሴዎችን ያስተዋሉ ተመካካሪዎች፤ ሌሎች ቡድኖችን እየመሰረቱና ተመሳሳዩን አካሄድ እየተከተሉ መሆናቸውን የገለጡልን ምንጮች፤ ኮሚሽኑ እስካሁን በመሰል እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ያለው ነገር አለመኖሩን ጠቁመዋል።

ምክክሩ በሚካሄድበት አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል እንዲሁም ተመካካሪዎች ባረፉባቸው የማደሪያ ቦታዎች “ቡድናዊ” እንቅስቃሴዎች በስፋት እንደሚስተዋሉም ከምንጫችን ሰምተናል።

    የቀጠለው የብልጽግና ፓርቲ ስብሰባ

ብልጽግና ፓርቲ ሐምሌ 19 ቀን፣ 2018 ዓ.ም በምክክሩ እየተሳተፉ የሚገኙ አባላቱን ሀገራዊ የምክክር ጉባኤው እየተካሄደ በሚገኝበት አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ሰብስቦ ማነጋገሩን መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፤ ፓርቲው የስብሰባ ቦታ ቀይሮ አባላቱን በምክክሩ ዙሪያ ዳግም ማነጋገሩን ምንጮች ነግረውናል። ቀዳሚው ስብሰባ በክልልና በከተማ አስተዳደር ደረጃ የተካሄደ ሲሆን፤ ቅዳሜ ሐምሌ 25 ቀን በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ አዳራሽ እና በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ አዳራሽ የተካሄዱ ስብሰባዎች ደግሞ ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የፓርቲው አባላት አንድ ላይ የተሰበሰቡባቸው መሆናቸውን ሰምተናል።

በስብሰባዎቹ በአንድ አጀንዳ ዙሪያ እየተመካከሩ የሚገኙ የፓርቲው አባላት በአንድ አዳራሽ መሰብሰባቸውን የገለጡልን ምንጮች፤ ፓርቲው በተለያዩ አጀንዳዎች ዙሪያ የያዛቸውን አቋሞች በድጋሚ ያሳወቀበት፣ አባላት ማከናወን ያለባቸውን እንቅስቃሴ አስመልክቶም አቅጣጫ የሰጠበት መሆኑን ነግረውናል።

የፓርቲው አባላት በአዲስ አበባ ከተማ ሕጋዊ ቁመና ጉዳይ በፓርቲው አባላት መካከል የተስተዋለውን የአቋም ልዩነት አስመልክቶ በቅዳሜው ስብሰባ ውይይት መደረጉንም የሰማን ሲሆን፤ የኦሮሚያ ክልል አመራሮችን ጨምሮ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ አካል ትሁን” የሚለውን አማራጭ ያንጸባረቁ የፓርቲው አባላት፤ “አቋማችሁን አስተካክሉ” የሚል ማሳሰቢያ በድጋሚ እንደደረሳቸው ተገልጧል።

 አዲስ ተመካካሪዎች

ሦስት ሳምንት ባስቆጠረው የምክክር ጉባኤ፤ አዲስ ተመካካሪዎች ምክክሩን እየተቀላቀሉ መሆናቸውን ምንጮች ነግረውናል። ኮሚሽኑ 4 ሺሕ የሚደርሱ ተመካካሪዎችን እንደሚያሳታፍ ቀደም ብሎ ገልጾ የነበረ ቢሆንም፤ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ ከቀናት በፊት በሰጡት መግለጫ የተመካካሪዎች ቁጥር አስቀድሞ የተጠቀሰውን ቁጥር ያህል አለመድረሱን ገልጠዋል።

ከምንጮቿ ባገኘችው መረጃ መሰረት ደግሞ አሁንም አዲስ ተመካካሪዎች ምክክሩን እየተቀላቀሉ ይገኛሉ። በጥቃቅን ቡድንና በንዑስ ቡድን ደረጃ የተካሄዱ የምክክር ሂደቶች ላይ ያልተሳተፉ፣ ነገር ግን በስልታዊ ቡድኖች ደረጃ በተካሄዱ ምክክሮች ላይ መሳተፍ የጀመሩ ተመካካሪዎች መኖራቸውን የገለጡልን ምንጮች፤ ኮሚሽኑ የተመካካሪዎች መታወቂያ ሕትመት አለማጠናቀቁን ነግረውናል።

ምክክሩን በአዲስ ተመካካሪነት ከተቀላቀሉ ሰዎች መካከል፣ በምክክሩ ለመሳተፍ የተለያዩ ጥረቶችን ሲያካሂዱ የነበሩና የኮሚሽነሮችን ደጅ ሲጠኑ የሰነበቱ ግለሰቦች እንደሚገኙበት የጠቀሱ ምንጮች፤ ኮሚሽኑ አዲስ ተመካካሪዎችን ወደ ምክክር ያስገባበት አሠራር ግልጽ አለመደረጉን ገልጠዋል። 

ምክክሩን በአዲስ ተመካካሪነት ከተቀላቀሉ ግለሰቦች ባሻገር በስልታዊ ቡድን ደረጃ ከሚደረጉ የምክክር ሂደቶች ጀምሮ ወደ ሌላ አጀንዳ ተዘዋውረው እንዲመካከሩ የተደረጉ ተመካካሪዎች መኖራቸውን ምንጮች ነግረውናል። በጥቃቅን እና በንዑስ ቡድን ደረጃ የተካሄዱ ምክክሮችን ሲያካሂዱበት ከነበረው አጀንዳ ተነስተውና መታወቂያቸው ተቀይሮ ወደ ሌላ አጀንዳ የተዛወሩ ተመካካሪዎች፤ “መታወቂያቸው ተቀይሮ ወደ ሌሎች አጀንዳዎች እንዲቀየሩ ተጠይቆላቸው” የነበሩና የመታወቂያ ሕትመት የዘገየባቸው መሆናቸውን ኮሚሽኑ መግለጡን ምንጮች ነግረውናል።

ይሁንና እነዚህ ተመካካሪዎች ከመጀመሪያው የምክክር ሂደት ጀምሮ ባልተሳተፉበትና ሀሳብ ባልሰጡበት አጀንዳ ላይ፤ አስተያየት ብሎም ድምጽ መስጠት የለባቸውም በሚል ቅሬታ መቅረቡን ሰምተናል። 

የርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድኖች ምክክር

ከሐምሌ 30 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የሚካሄደው የርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድኖች ምክክር ለሦስት ቀናት ያህል የሚቆይ መሆኑን ኮሚሽኑ ለተመካካሪዎች ያቀረበው “የሥራ ቡድን የምክክር ስልት” ሰነድ የሚያመላክት ቢሆንም፤ ሂደቱ ረዘም ያለ ጊዜ ሊፈጅ እንደሚችል ኮሚሽነሮች ፍንጭ ሰጥተዋል። እስካሁን የተካሄዱ የምክክር ሂደቶችም ከተቀመጠላቸው የበለጠና የተራዘመ ጊዜ የወሰዱ ሲሆን፤ በርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድኖች ደረጃ የሚካሄደው ምክክር የውሳኔ ድምጽ የሚሰጥበት ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ምንጮች ገልጠዋል።

ኮሚሽኑ ለተመካካሪዎች በሰጠው ማብራሪያ መሰረትም ሀሙስ ሐምሌ 30 ቀን፤ የአንድ ርዕሰ ጉዳይ ተመካካሪ ቡድን አባል የሆኑት ሁለት ስልታዊ ቡድኖች የምክረ ሀሳብ ቃለ ጉባኤያቸውን 500 አባላት ላሉት የርዕሰ ጉዳይ ጉባኤ ያቀርባሉ።

ይህ ሂደት ግማሽ ቀን ይፈጃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ኮሚሽኑ ገልጧል። ቃለ ጉባኤዎች ለጉባኤው አባላት ከተነበቡ በኋላ፤ ከሁለቱ ስልታዊ ቡድኖች የተውጣጡ 30 የአጠናቃሪ ቡድን አባላት የመጨረሻ የሚሉትን ምክረ ሀሳብ እንዲያጠናቅሩ ይደረጋል። 

ይህ የማጠናቀር ሂደት በምሁራን ፓናል አባላት የሚደገፍ መሆኑን የተመለከትነው ሰነድ ያመላክታል። ይህ ምክረ ሀሳብ የማጠናቀር ሂደት እስከ አንድ ቀን ከግማሽ የሚደርስ ጊዜ ይፈጃል የሚል ዕቅድ የተያዘለት ሲሆን፤ የተጠናቀረው ምክረ ሀሳብ ለጉባኤው ቀርቦ ውሳኔ እንደሚሰጥበት ይጠበቃል። 

wazemaradio

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የቀድሞው ጠ/ሚኒስትር በዓለም የምግብ ምርምር ድርጅት ሹመት ተሰጣቸው

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር እና የአግራ (AGRA) የቦርድ ሰብሳቢ...

አቶ ሳሙኤል ታፈሰ በካናዳ ሀገር ሊሸለሙ ነው

የሰንሻይን ኢንቨስትመንት ግሩፕ መስራችና ሊቀመንበር አቶ ሳሙኤል ታፈሰ በንግዱ...

በፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል ያለዉ ግጭት እንዳሳሰበው የአውሮፓ ሰላም ፋውንዴሽን ገለፀ

የአውሮፓ ሰላም ፋውንዴሽን  በኢትዮጵያ ፌደራላዊ  መንግሥት እና በህዝባዊ ወያኔ...

የብሔራዊ ትያትር ሕንፃ ግራጫ ቀለም የጥበብ ማዕከል መገለጫ አይሆንም

ከሥር ከላይ በስተግራ የምታየው ፎቶ 1 የታሪካዊዉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ...