የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ለመውሰድ 36 ሺሕ 711 ተማሪዎች መመዝገባቸውን የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ለአሐዱ ገልጿል።
በቢሮው የትምህርት ምዘና እና ብሄራዊ ፈተናዎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ዶ/ር አረጋዊ ዘፈሩ፤ በ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች መልቀቂያ ፈተና በወረቀትና በበይነ መረብ /በኦን ላይን/ የሚሰጥ መሆኑን ተናግረዋል።
ዶ/ር አረጋዊ ለአሐዱ እንደገለጹት በበየነ መረብ/ በኦን ላይን/ የሚፈተኑ ተማሪዎች 10 ሺሕ 119 ሲሆኑ በወረቀት የሚፈተኑት ደግሞ 26 ሺሕ 592 ናቸው፡፡
ከአጠቃላይ ተፈታኞች ቁጥር ውስጥም ከ50 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
የዘንድሮው የ12ኛ ክፍል ፈተና ተፈታኞች ቁጥር ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር መቀነሱን የገለጹት የት/ት ሃላፊው፤ ይህም ተማሪዎች በተለያዩ ችግሮች ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው በመቅረታቸው የተፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል።
“በተለይም አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች በመፍረሳቸውና እድሳት ስላልተደረገላቸው፣ በቂ የመፃህፍት አቅርቦት አለመኖር፣ ርሀብ፣ ስደት እንዲሁም፤ የሥነ ልቦና ጫና እና መሰል ችግሮች በክልሉ መኖር የተማሪዎች ቁጥር እንዲቀንስ ምክንያቶቹ ናቸው” ሲሉም ገልጸዋል።
“በኦን ላይን ለሚፈተኑ ተማሪዎች ፕሮግራም አውጥተን እንዲለማመዱ ቢደረግም በቂ የሆነ የኮምፒውተር አቅርቦት የለም” ያሉት ዶ/ር አረጋዊ፤ በክልሉ የሚገኙ ተፈታኝ ተማሪዎች በዩኒቨርስቲዎች እና በትምህርት ቤቶች እየሄዱ ልምምድ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
በኢትዮጵያ የ2017 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ መልቀቂያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች ከ608 ሺሕ በላይ መሆናቸውና የፈተና ዝግጅቱ ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን፤ የትምህርት ምዘና እና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር እሸቱ ከበደ መግለፃቸው ይታወሳል።
(አሐዱ ሬድዮ)
