የፌዴራል መንግስት እና ህወሓት የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈራረሙ ከሶስት ዓመታት በላይ ቢያልፍም፣ የትግራይ ክልል አሁንም ከባድ የፀጥታ እና ማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ እንደሚገኝ አንድ በቅርቡ በቀረበው የግጭት ትንተና ሪፖርት አመልክቷል።
እንደ ሪፖርቱ ከሆነ ፣ በተለይም የቀድሞ ተዋጊዎችንና ሥራ አጥ ወጣቶችን ጨምሮ በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች ባጋጠማቸው የኢኮኖሚ ውድቀት እና የኑሮ መሠረታዊ ድጋፍ እጦት ምክንያት ተስፋ ቆርጠዋል።
ይህ ደግሞ ወጣቶቹ ወደ ህገ-ወጥ የወርቅ ማዕድን ማውጣት እና ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ህጋዊ ያልሆነ ስደት እንዲያመሩ ዋና ምክንያት ሆኗል።
ከባድ የስራ አጥነትና ተስፋ መቁረጥ በከተማ ማዕከላት እንደ መቐለና አዲግራት ጭምር የወንበዴዎች ቡድን ጥቃቶችን፣ የታጠቁ ዘረፋዎችን እና የበቀል ግድያዎችን እያባባሰ መሆኑ በሪፖርቱ ተመላክቷል።
የፍትሕና የፀጥታ ተቋማት መዳከም ወንጀል ያለ ከልካይ እንዲስፋፋ ዕድል የሰጠ ሲሆን፣ ህገ-ወጥ ወርቅ ማዕድን ማውጣት በአርሶ አደሮች መካከል ግጭቶችን እየፈጠረ ነው።
በተጨማሪም፣ በኢሮብና ጉሎመከዳ ወረዳዎች የሚገኙ ወጣቶች በሰዎች አዘዋዋሪዎች ብዝበዛ እየደረሰባቸው ለስደት የሚጋለጡ ሲሆን፣ ራማ የመሳሰሉ የድንበር ከተሞች ለህገ-ወጥ የጦር መሳሪያና የሰዎች ዝውውር መሸጋገሪያ ሆነዋል።
ሪፖርቱ ከሰብዓዊ ዕርዳታ ባሻገር በወጣቶች ላይ ስልታዊ ኢንቨስትመንት፣ የሙያ ሥልጠና እና ለሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር የግድ መሆኑን አሳስቧል።
Capital news
