ኢትዮጵያ ወደ ገበያ ተኮር የምንዛሪ ተመን ሥርዓት ከተሸጋገረች ከአንድ ዓመት በኋላ፣ የአገር ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ገበያ በአስደንጋጭ ሁኔታ መከፋፈሉንና የግብይት ወጪዎች በእጅጉ መጨመራቸውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክስ ማኅበር ገለጸ።
የንግድ ባንኮች ለአንድ የአሜሪካ ዶላር የሚገዙበትና የሚሸጡበት ተመን ላይ ያለው ልዩነት እስከ 15 ብር ድረስ ከፍ ማለቱ፣ በገበያው ውስጥ ጤናማ ውድድር እና የተቀናጀ አሠራር አለመኖሩን የሚያመላክት ትልቅ ፈተና እንደሆነ ተገልጿል።
የኢኮኖሚክስ ማኅበሩ ባወጣው ሪፖርት መሠረት በ2018 የበጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ብር ከአሜሪካ ዶላር አንፃር በ8.1 በመቶ በማሽቆልቆል ከ135.5 ወደ 146.4 ብር ደርሷል፤ በታኅሣሥ 2018 ዓ.ም ደግሞ ከ154 ብር በላይ ሆኗል።
እንደ ሪፖርቱ ከሆነ በባንኮች የመግዣና የመሸጫ ዋጋዎች መካከል ያለው ልዩነት ባለፈው ሩብ ዓመት ከ3.1% ወደ 6.8% የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ከፍ ብሏል።
ይህ መስፋፋት የዘርፉ ተዋናዮች አደጋን የመፍራት ዝንባሌ፣ የተገደበ የባንኮች መካከል የንግድ ልውውጥ እና መሰረታዊ የገበያ ውዝግብ መጨመሩን የሚያመለክት መሆኑ ተጠቁሟል።
