ታጣቂ ኃይሎች ብቻቸውን የሚፈጽሙት ሳይሆን በመንግሥት ውስጥ ያሉ ኃላፊዎችም ጭምር …

Date:

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ከምሥረታው አንስቶ ባለፉት 7 ዓመታት መንግሥት ዋናው ኃላፊነቱ የሆነውን የዜጎችን ሰላምና ደኽንነት እንዲያስጠብቅ በተደጋጋሚ የጠየቀባቸው መግለጫዎች በሌሎች ጉዳዮች ላይ ካወጣቸው አጠቃላይ መግለጫዎች ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ።

እነዚህ መግለጫዎች ዜጎች ለከፍተኛ የደህንነት ስጋት እየተጋለጡ እንደሆነ እና የሥጋት  ቦታዎቹም ተመሣሣይ እንደሆኑ የሚጠቁሙ ናቸው። የጥቃቱ ሰለባ ዜጎች፣ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች እና የግል መገናኛ ብዙኃን ለተከታታይ ዘመናት ይሄንኑ የንፁሀን ግድያ ሲዘግቡ፣ የመፍትሔ አቅጣጫም ሲያመላክቱ ቆይተዋል።

ኢዜማ እንደ አንድ ተፎካካሪ ፓርቲ እና ውሱን የመንግሥት ኃላፊነት ቦታዎች ላይ እንደሚያገለግል አካል ይኽንን መሠል ችግሮች የመከሰታቸውን  ምክንያቶች  ምን እንደሆኑ አጥንቶ መፍትሔ የሚላቸውን ሐሣቦች ባለፉት ዓመታት ሲጠቁም ቆይቷል። ሆኖም ኃላፊነት ያለበት የመንግሥት አካል የዜጎችን ሕይወት መታደግ ባለመቻሉ ምክንያት የዜጎች ነፍስ በተቀጠፈ ቁጥር መራር ቁጭት እንደሚፈጥርበት ለመግለጽ ይወዳል።

የመንግሥት የዜጎችን ደህንነት በቅጡ አለመከላከል ያልተፈታ ቅኔ ቢሆንም፤ እነዚህ የዜጎችን ሕይወት እየቀጠፉ የሚገኙ የደህንነት ችግሮች ታጣቂ ኃይሎች ብቻቸውን የሚፈጽሙት ሳይሆን በመንግሥት ውስጥ ያሉ ኃላፊዎችም ጭምር የሚሣተፉበት መሆኑ የበለጠ ጉዳዩን የሚያመረቅዝ ቁስል ያደርገዋል።

በዚህም ላይ በሕዝብ ግብር የሚተዳደሩት መገናኛ ብዙኃን ለሞታቸው ምክንያቱ ምንድነው የሚለውን እና እንደ ሚዲያ ተቋም የሚመለከተውን አካል ለምን ብሎ መጠየቅ ቢቀር እንኳ መሞታቸውን ለመንገር እና ኃዘናቸውን ለመግለፅ ዳተኛ መሆናቸውን ስንመለከት የደረስንበት የሞራል ዝቅጠት ምን ያህል እንደወረደ ያሳየናል።

ለአብነትም የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬት (EBC) ባለፈው ሳምንት ሰኞ ዕለት በአርሲ ስለተገደሉ ዜጎች ዝምታን የመረጠ ሲሆን ጥቃቱ በተፈፀመበት ሳምንት አርሲን ጠቅሶ የሠራው ዘገባ የነገሌ አርሲ እግርኳስ ቡድንን የጨዋታ ውጤት ነበር፤ በአርሲ ባለፉት ዓመታት ተመሳሳይ የዜጎችን ሕይወት የቀጠፈ ጥቃት የነበረ ቢሆንም የመንግሥት ኃላፊዎች በአንድ መንገድ ተግባቦት (One way communication) መግለጫዎች ሲሰጡ ብቻ ከመዘገብ ያለፈ ሚና ሲወጡ አይታዩም።

እነዚህ የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን ተቋማት ከሀገር ውጭ በሌሎች የውጭ ዜጎች ላይ የሚደርሱ ሞት እና አደጋዎችን ተከታትለው  እየሰሩ በኢትዮጵያዊያን ዜጎች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመዘገብ ዳተኝነት ማሳየታቸው ለዜጎቻችን ያላቸውን ንቀት እንዲሁም ከሞራልና ከሙያዊ ግዴታ በወጣ መልኩ የመንግሥት የፕሮፖጋንዳ መሣሪያ ብቻ ሆነው ማገልገልን እንደመረጡ ያለሀፍረት አሳይተዋል።

ይሕ በእንዲህ እንዳለ በቅርብ ቀናት በተደጋጋሚ በአርሲ የተለያዩ አከባቢዎች ማንነትን መሠረት አድርገው የተፈፀሙ ጥቃቶች፣ በጋምቤላ  እና ሞያሌ የተከሰቱ የእርስ በእርስ ግጭቶች ለዜጎች ሕይወት ማለፍ፣ መፈናቀል እንዲሁም ንብረት መውደም ምክንያት የሆኑ ሲሆን ለእነዚህም ዋነኛ ተጠያቂው አካል የዜጎችን ሰላምና ደህንነት የማስከበር ኃላፊነት ያለበት መንግሥት መሆኑን እየገለፅን፤

1) የመንግሥት ኃላፊዎች በተደጋጋሚ ለሚፈጠሩ ችግሮች ጊዜያዊ አጀንዳዎችን ምክንያት ከማድረግ እንዲቆጠቡ!

የመንግሥት ባለሥልጣናት ችግሮቹ ላለፉት ዓመታት በተደጋጋሚ ሲፈፀሙ እንዳልነበረ በሚመስል መልኩ ወቅታዊ ጉዳዮችን ተጠቅሞ እራስን ከተጠያቂነት ነፃ ማድረግ ፍፁም ተቀባይነት የሌለው ኢ-ሞራላዊ ተግባር ነው። ከሰሞኑ በአርሲ ለተፈፀመው ጥቃት በኦሮሚያ ክልል ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት የተሠጠው መግለጫም  ለዚህ ጥሩ ማሣያ ነው። ይህ ዓይነት የመንግሥት ተግባር  ዜጎች መንግሥት ላይ የበለጠ አመኔታን እንዲያጡ ከማድረግ የዘለለ ጥቅም የሌለው መሆኑን ተረድቶ ለማኅበረሰቡ የሚደርሱ መረጃዎች እውነታ ላይ የተመሠረቱ እና በእርግጥም ለችግሮቹ ምክንያት የሆኑትን የለየ እንዲሁም መፍትሔ የሆኑ የተፈፀሙ፣ ሊፈፀሙ የታሰቡ እና በምን ያህል ጊዜ ይኽንን ነገር ለማስተካከል እንደታሠበ መግለጽ ተገቢ መሆኑን ተረድተው ከዚህ ዓይነት ተግባራቸው እንዲቆጠቡ፤

2) የተጠና ችግሩን የሚመጥን መፍትሔ ይሰጥ

መንግሥት ለዚህ ዓይነት ተደጋጋሚ ጥቃት ምክንያት የሆኑትን ችግሮች የደህንነት መረጃዎችን መሠረት ባደረገ ቅድመ ጥንቃቄና መከላከል እንዲሁም የአጭር ጊዜ እና ዘለቄታዊ መፍትሔ በመስጠት ዳግም ጥቃቶች እንዳይከሰቱ እንዲያደርግ። የጥቃት ስጋት ያለባቸውን አካባቢዎች እና የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በቶሎ በማይደርሱባቸው አከባቢዎች ማኅበረሰቡን በማደራጀት ራሱን እንዲከላከል በመረጃና በሎጀስቲክስ እንዲያግዝ፤

3) እውነተኛ ተጠያቂነትን ይስፈን

ይህ ዓይነት ተደጋጋሚ ጥቃት ሲከሰት ከኃላፊነታቸው ያጎደሉ ወይም ሥልጣናቸውን አለአግባብ ተጠቅመው ዜጎችን ለጥቃት ያጋለጡት የመንግሥት ኃላፊዎችን ተጠያቂ እንዲያደርግ እና በይፋ ለሕዝብ እንዲያሣውቅ፤ ይህንን ከማድረግ ይልቅ የሥልጣን ሽግሽጎችን ማድረግ ባለሥልጣናቱ የሚያጠፏቸውን የጥፋት ዓይነት ከመለዋወጥ የዘለለ መፍትሔ የሌለው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።

4) ተቋማት ኃላፊነታቸውን በቅጡ ይወጡ

4.1 የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የደረሰውን ጥቃት በገለልተኝነት በማጣራት ለቆማችሁለት የሰብዓዊ መብት መከበር ሚናችሁን እንድትወጡ፤

4.2 የሕዝብ መገናኛ ብዙኃን የሚዲያ ምንነትን በሚመጥን መልኩ መንግሥትን ተጠያቂ በማድረግ ዜጎች ላይ ተመሣሣይ ጥቃት እንዳይፈፀም ድምፅ እንድትሆኑ ስንል ጥሪ እናቀርባለን።

በእነዚህ በማንነት ላይ በተቃጡ ጥቃቶች እና የእርስ በእርስ ግጭቶች ሕይወታቸውን ላጡ ዜጎች የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን እየገለጽን፤ ለቤተሰቦቻቸውና ለሕዝቡ መፅናናትን እንመኛለን።

የአንድ ዜጋ ደኅንነት ያልተከበረባት ሀገር የሁሉም ዜጎች ክብር ስለማይጠበቅባት፤ ለዜጎች ሰብዓዊ ክብር ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጋራ እንዲቆም አደራ እንላለን።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ( #ኢዜማ )
ጥቅምት 17/2019 ዓ.ም.

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ከቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የተሰጠ የኀዘን መግለጫ

በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በአርሲ ዞን ጥቅምት 10 እና...

 የ2026 የባሎንዶር ሽልማት አሸናፊዎች ይፋ ሆኑ!

በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከፓሪስ ውጪ በለንደን በተካሄደው ታላቅ የሽልማት...

አይበገሬው ፍቃዱ —-  ( ከጋዜጠኛ ሁሴን ከድር )

ትናንት ( ቅዳሜ ጥቅምት 14 2019 ዓ.ም ) የቀድሞ...

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለ10 ምሁራን የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጥቷል

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ቦርድ ጥቅምት 12 ቀን 2019...