ነፃነት ከዳቦ ይበልጣል!

Date:

የአርበኞች አደራና የትውልዱ ዕዳ!

ከሣልሳዊት ባይነሳኝ

ግዮን መጽሔት :- ከዓለም ድንቅ ድሎች አንዱ ከሆነውና የጥቁር ሕዝቦች ኩራት ከሆነው የዓድዋ ድል ማግስት፣ እነሆ አንድ መቶ ሠላሳ ዓመታትን አስቆጠርን፡፡ ይህን ያህል ረጅም ዘመን ቢነጕድም፣ ዛሬም ድረስ የነፃነትን ትርጕም በሚገባ ተረድቶ ለክብሩ የመቆም ጉዳይ በትውልዱ ዘንድ አሳሳቢ ሥጋት ሆኖ ይታያል፡፡ በቅርቡ የተከበረው 85ኛው የአርበኞች የድል በዓልም፣ ይህንኑ የታሪክ አደራና የትውልድ ዕዳ ዳግም እንድንመረምር በር ከፋች ነበር፡፡

​በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ፋውንዴሽንና በወመዘክር አስተባባሪነት በተሰናዳው በዚሁ የድል በዓል መርሃ-ግብር ላይ የታሪክ ባለአደራዎች ባስተላለፉት መልዕክት፣ ዋናው ዓላማ የድል ታሪክንና ማንነትን ለተተኪው ትውልድ ማሸጋገር እንደሆነ ተመላክቷል፡፡ ኾኖም ለውድ ነፃነታችን የተከፈለውን መስዋዕትነት በትክክለኛው ሚዛን ባለማስቀመጣችን፣ ዛሬ በኑሮ ውድነት ሰበብ ‹‹በተገዛን ይሻለን ነበር›› የሚሉ የውርደት ድምፆች በየጥጋጥጉ ይሰማሉ፡፡

​በዳቦ ዋጋ ላይ አሥር ሳንቲም በተጨመረ ቁጥር፣ ውድ ሕይወታቸውን ገብረው ነፃ ሀገር ላቆዩልን አባቶች ክብር ሳይሰጥ፣ ሀገራቸውን መዘባበቻ የሚያደርጉ ወገኖች መታየታቸው እጅግ ያሳፍራል፡፡ ይህ ትውልድ ሊገነዘበው የሚገባ መሠረታዊ እውነት ቢኖር ነፃነት ከዳቦ እንደሚበልጥና በቅኝ በመገዛት ብቻ የሚሞላ ሆድ እንደሌለ ነው፡፡ እንደ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳንና ማሊ ያሉ ጎረቤት ሀገራት ተገዝተውም ከኢትዮጵያ በከፋ ድህነት ውስጥ መውደቃቸው ለዚህ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡ በመሆኑም የዘንድሮው የ85ኛው የአርበኞች የድል በዓል፣ ነፃነት በዳቦ የማይተመን የሕይወት ዋጋ የተከፈለበት መሆኑን ዳግም የምናስብበት ሊሆን ይገባል፡፡ 

***

​ሥልጣኔን በመሠረተ ልማትና በሕንፃ ግንባታ ብቻ ለሚመዝኑ ወገኖች፣ የቅኝ ግዛት ትርክት ትልቅ የማንነት ስብራት ነው፡፡ አንዳንዶች በባርነት ቀንበር ጎብጠውና ከሰው ተራ ወጥተው ሳለ፣ በጠላቶቻቸው የተገነቡ ያማሩ መንገዶችንና የድንጋይ ክምር ፎቆችን በማየታቸው ብቻ ‹‹በተገዛን ይሻለን ነበር›› እስከማለት ይደርሳሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ግን ከነፃነት ጀርባ ያለውን የሞት ሞትና ውርደት ካለመረዳት የሚመነጭ ነው፡፡ በባርነት መሬት ላይ የቆመ ሕንፃ እንኳን ቢሆን፣ ባለሀገሩ አባትና አያቶቹ ተረግጠው በወደቁበት መሬት ላይ የቆመ በመሆኑ፣ ያንን ንብረት የማስተዳደር ሞራላዊም ሆነ ሕጋዊ የበላይነት አይኖረውም፡፡

​ይህ በቅኝ ግዛት የተተከለ የሥነ-ልቦና ስብራት ዛሬም ድረስ በብዙ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ በግልጽ ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ ነጮች ከ72 በመቶ በላይ የሚሆነውን የመሬት ይዞታ ተቆጣጥረው ይገኛሉ፡፡ ዜጎቿ ዛሬም ድረስ ከገዥዎቻቸው ጋር እኩል ለመሰለፍና ለመነገድ የሚሳቀቁበት፣ ገዥዎቻቸውን ቀና ብለው የማየት ወኔ የሌላቸውና ግፋቸውን በሌሎች ስደተኞች ላይ የሚወጡበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል፡፡

እንደ ኬንያ ባሉ ሀገራትም ሀብቱ ዛሬም ድረስ በቀድሞ ገዥዎቻቸው እጅ የሚገላበጥ ሲሆን፣ የአገር በቀል ባለሀብቶች ቁጥር ግን እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ውርደት የሚያሳየው፣ ቅኝ ግዛት በሕዝቦች ውስጥ ጥሎት የሚያልፈው ጠባሳ የሆድ መሙላት ጥያቄ ሳይሆን፣ የማንነትና የሉዓላዊነት ክስረት መሆኑን ነው፡፡ 

ጀግኖች አርበኞቻችን ኃብቷ ያልተነካ ድንግል ሀገርን ከነክብሯ፣ ቋንቋዋን፣ ባሕሏንና እምነቷን ሁሉ ከወርቅ በከበረ ደምና አጥንታቸው አትመው አስረከቡን፡፡ እኛ ግን ነዳጇን አውጥተንና ወርቋን ቆፍረን በላባችን መኖር ሲሳነን የነፃነትን ዋጋ በዳቦ መተመን ቀለለን፡፡ ዛሬ በየቦታው ‹‹ነፃ ላውጣህ›› የሚለው የብሔረሰብ ፖለቲካ ሁሉ፣ የፋሽስት ጣሊያንን የከፋፍለህ ግዛ ዕቅድና መርዛማ ፕሮግራም አንግቦ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡

​ታሪክ እንደሚያሳየው፣ ጣሊያን ኢትዮጵያን በቋንቋ መሠረት በስድስት ቀጣናዎች በመከፋፈል ሀገራዊ አንድነቷን ለማላላት ሞክራ ነበር፡፡ የሚያሳዝነው ግን፣ ዛሬም ድረስ በዚሁ የፋሽስት ፕሮግራም እየተመራን እርስ በእርሳችን እንናከሳለን፡፡ ለሀገራቸው ነፃነት የወደቁት አርበኞች ግን በቋንቋና በሃይማኖት ተቧድነው አልነበረም፡፡ እመቤት ሆይ አርበኛ ከበደች ሥዩም ከትግራይ ተነስተው ሸዋ ላይ ሲዋጉ ‹‹ከትግራይ ለአማራ›› በሚል ጠባብ ስሜት ሳይሆን ለጋራ ሀገራቸው ነበር፡፡

​አርበኛው ደጅ አዝማች ዑመር ሠመተርም፣ ጠላት በሃይማኖት ሽፋን ሊከፋፍላቸው መሞከሩን በመረዳት ሕዝቡን አስተባብረዋል፡፡ ጣሊያን መስጂድ የሚገነባው ስለወደደን ሳይሆን፣ ክርስቲያኑንና ሙስሊሙን አጣልቶ አንዱን ካጠፋ በኋላ ሌላውን ለማሳደድ እንደሆነ ቀድመው ተገንዝበው ነበር፡፡ አርበኞቻችን ስድስት ጥይት በሰውነታቸው ውስጥ ተቀብለውም ቢሆን፣ የሀገራቸውን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ በማየታቸው ብቻ ረክተው ያለፉ ጀግኖች ናቸው፡፡ ዛሬም የጠላትን የክፍፍል ወጥመድ ሰብረን ለሀገራዊ ሉዓላዊነታችን የምንቆም ትውልዶችን እናፍቃለን፡፡ 

​ዛሬ ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትሻው ስሟንና ታሪኳን የሚመጥኑ፣ እንደ አርበኞች አባቶቻቸው ለክብሯ ዋስ ጠበቃ የሚሆኑላትን ልጆች ነው፡፡ የታሪክ ዕዳችንን መክፈል የምንችለው፣ በኑሮ ውድነት ሰበብ የነፃነትን ዋጋ በዳቦ ከሚመዝን ተለዋዋጭ ስሜት ተላቀን፣ ሀገራዊ ሉዓላዊነታችንን በጽኑ መሠረት ላይ ማቆም ስንችል ብቻ ነው፡፡

​እንደ ኢትዮጵያ ለነፃነት ሕይወት የተከፈለበት ምድር በዓለም ላይ ማግኘት እጅግ አዳጋች ነው፡፡ በመሆኑም፣ በየዘመኑ ‹‹ነፃ አውጭ ነኝ›› በሚል ስም የፋሽስቱን የክፍፍል መርዝ አንግበው የሚመጡ ወገኖችን ሤራ በመገንዘብ፣ አርበኞች በደማቸውና በአጥንታቸው ያቆዩልንን ቋንቋ፣ ባሕልና እምነት ጠብቆ ማስቀጠል የዚህ ትውልድ ቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል፡፡

​በመጨረሻም፣ ያኔ በዓለም ሕግ ፊት የተከለከለውን የመርዝ ጋዝ ተጠቅማ ሕዝባችንን የፈጀችው ፋሽስት ጣሊያን፣ ዛሬ ፋሽስቶቿ ባይኖሩም ለሀገራችን ተገቢውን ካሳ እንድትከፍል በዓለም አደባባይ ደማቸውን የሚበቀልና መብታቸውን የሚያስከብር ትውልድ መነሳት ይኖርበታል፡፡ የጀግኖች አርበኞቻችን መስዋዕትነት ትርጉም የሚኖረው፣ እኛ ከክፍፍል ወጥመድ ወጥተን ለነፃነታችን ዳግም ስንቆም ብቻ ነው፡፡

ጋዜጠኛ ሣልሳዊት ባይነሳኝ በዋልታና ፋና ቴሌቭዥኖች ላለፍት 8 ዓመታት በምርመራና ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ፕሮግራሞችን ስታደርስ ቆይታለች፡፡ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ማኅበራዊ የትስስር ገፆች ላይ ሀገራዊ ታሪኮችና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በግሏ በማንሳት ትውልዱ በተለይም ወጣቱ እንዲነጋገርባቸው በማድረግ ላይ የምትገኝ ባለሙያ ናት፡፡

ግዮን መጽሔት ቅጽ 8 ቁጥር  233 ግንቦት 2018 ዓ.ም

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በኢትዮጵያ የዲጂታል ኦቲዝም በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ ተገለፀ

ልጆች ረጅም ሰዓት በስልክና በቪዲዮ ጌሞች ላይ ማሳለፋቸው፣ መናገር...

ፑቲን እና ሺ ጂንፒንግ በቻይና ውይይት ያደርጋሉ 

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ወደ ቻይና የሚያደርጉትን መጪ ጉብኝት አስመልክቶ የክሬምሊን...

ከምዝገባ ካርድ ባሻገር፦ ለነገው ድምፅ የዛሬው ጥንቃቄ

ግዮን መጽሔት :- የምርጫ ካርድዎን በእጅዎ ይዘዋል? እንኳን ደስ...

በጤና አገልግሎት ማስታወቂያዎች ላይ የሕመምተኞችን ምስክርነት መጠቀም ተከለከለ

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ባወጣው አዲስ መመሪያ መሠረት በኢትዮጵያ ውስጥ...